Ethiopian Federal Police members ride through Addis Ababa, May 21, 2010. AP
Ethiopian Federal Police members ride through Addis Ababa, May 21, 2010. AP

ዋዜማ ራዲዮ-

12ስዓት የተጠናቀረ/የተከለስ

ከሜክሲኮ ጀሞ የታክሲ እጥረት ይታያል፡፡

የቤት መኪኖች በታክሲ የተቸገሩ እግረኞችን እየተባበሩ ነው፡፡

ረዣዥም የታክሲ ሰልፎች በመሐል ከተማ ቢኖሩም በቂ ታክሲዎች ግን የሉም፡፡

በአስኮ መስመር ከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ፈሷል፡፡

በአስኮ መስመር ካታ በሚባል ሰፈር፣ ኦሮሚያን ከአዲስ አበባ የሚለያት ሳንሱሲ ሰፈር ከዚያም አልፎ በተለምዶ ሸክላ የሚባል አካባቢ፣ ከሸክላ ሰፈር አልፎ ከርታ የሚባል ሰፈር እንዲሁም ቡራዩ ከዋና መንገዶች ገባ ብሎ መጠነኛ የወጣቶች ስብስብና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ታይተው ነበር፡፡ ኾኖም ማምሻውን ጋብ ብለዋል፡፡

በታጠቅ መስመር ጉጂና አሸዋ ሜዳ ነዋሪዎች የቃጠሎ ጭስ እንደተመለከቱ ለዋዜማ በስልክ ተናግረዋል፡፡ እየነደደ ያለው ምን እንደሆነ ግን ማወቅ አልቻሉም፡፡ ጉጂ ከዚህ ቀደም በተቀናጀው ማስተር ፕላን ምክንያት በተነሳው የኦሮሚያ አመጽ ምክንያት ተደጋጋሚ ግጭቶች ይቀሰቀሱበት የነበረ ሰፈር ነው፡፡ እነዚህ ሰፈሮች አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከመሐል ከተማ ረዥም ርቀት ተጉዘው የሚኖሩባቸው ሲሆን ከፊሎቹም በጨረቃ ቤትነት የተያዙ ናቸው፡፡

ከጦርኃይሎች ጀምሮ በቤቴል ዓለም ባንክ ድረስ ምንም አይነት የተቃውሞ ምልክቶች አይታዩም፡፡ የጸጥታ ኃይሎችም በአካባቢው የሉም፡፡ ኾኖም ሱፐርማርኬቶችም ሆኑ መለስተኛ ሱቆች ተዘግተዋል፡፡ አልፎ አልፎ ከሚታዩ መዝናኛ ቤቶች በስተቀር የንግድ እንቅስቃሴ የለም፡፡ በመዝናኛ ቤቶች የሚታየው የሰው ቁጥር እንደወትሮው አይደለም፡፡

መጠነኛ ረብሻ በታየባቸው የአየርጤና፣ አለምገናና ፉሪ ሰፈሮች ማምሻውን ወጣቶች ሊታፈሱ ይችላሉ የሚል ወሬ በመነዛቱ ወላጆች ልጆቻቸውን ዘመድ ቤት ለማሳደር እየሞከሩ እንደሆነ በስልክ መረጃ ካቀበሉን ቤተሰቦች መስማት ችለናል፡፡

ፉሪ አደባባይ ላይ በዛ ያሉ ፖሊሶች ቆመው ቢታዩም በዋና መንገድ ላይ እየተካሄደ ያለ ምንም አይነት ተቃውሞ የለም፡፡

ከፉሪ ጀሞ ሁለት አልፎ መስታወት ፋብሪካውን አካባቢ በግምት 500 ሜትር ርቀት ላይ ወደ የስ ዉሃ ፋብሪካ በሚወስደው ጎዳና ከመንታ መንገዱ አንደኛው በድንጋይ ተዘግቷል፡፡

ከአስኮ እስከ ሳንሱሲ ታክሲ ቢኖርም ከዚያ በኋላ ወደ ቡራዩ ትራንስፖርት የለም፡፡ ከፍተኛ የወታደር ቁጥር የሚታየው በዚህ መስመር ሲሆን መትረየስ ደግነው የሚሄዱና በፌዴራሎች የተሞሉ ፒክአፕ ተሸከርካሪዎች በብዛት ይታያሉ፡፡ ወታደሮቹ የቤት መኪኖችን በግዳጅ እያስቆሙ ታክሲ ያጡ እግረኞችን እንዲሸኙ ያስገድዳሉ፡፡

 

11: 30 ስዓት የተጠናቀረ

የኮንትራት ታክሲ ዋጋ ንሯል፡፡
ሕዝቡ ወደቤቱ በጊዜ ለመግባት ጥድፊያ ላይ ነው፡፡
መሐል ከተማው የትራፊክ እንቅስቃሴው ተዳክሟል፡፡ ከከተማ ወጣ ያሉ ሰፈሮች የሚወስዱ መንገዶች መጨናነቅ ይታያል፡፡
መርካቶ ነጋዴዎች ሱቃቸውን ዘግተው መሄድ የጀመሩት ከ11 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡
እስከነገ ድረስ ነገሮች መልክ ካልያዙ ኢንተርኔት በዋና ከተማው ሊቋረጥ ይችላል እየተባለ ነው፡፡
በአዲስ አበባ መውጫዎች የጸጥታ ችግር መከሰቱ ከተሰማ ወዲህ በአዲስ አበባ ሰዎች ወደቤታቸው በጊዜ ለመግባት ሽርጉድ ላይ ናቸው፡፡ አየር ጤና፣ ፉሪ፣ አለምገና፣ ቡራዩ መለስተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል፡፡ በተለይ ፉሪ ሁሉም የግል ባንኮች ከምሳ ሰዓት ጀምሮ ተዘግተዋል፡፡
በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች በጊዜ ካልወጣን በሚል ከአለቆቻቸው ጋር አተካራ ዉስጥ መግባታቸው ተሰምቷል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የታክሲ ሰልፍ ሲረዝምባቸው ኮንትራት ታክሲ ለ3 እና 4 ሆነው ሲኮናተሩ ተስተውሏል፡፡ ብዙ ሰዎች በስልክ የሚነጋገሩት በአዲስ አበባ የጸጥታ ችግር በየሰፈሩ መኖር አለመኖሩን ነው፡፡
አለምገና በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ወላጆች በፍጥነት ልጆቻቸውን መጥተው እንዲረከቧቸው ከትምህርት ቤቶች ስልክ ተደውሎላቸው ስለነበር ወላጆች በከፍተኛ ጭንቀት የትምሀርት ቤት በሮች ላይ ተኮልኩለው ታይተዋል፡፡ ፉሪ የኦሮሚያ ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ግራና ቀኝ ቆመው ይታያሉ፡፡ ባጃጅ የሚሰሩ አንዳንድ ወጣቶች ለምን እኛ እያመጽን እናንተ ትሰራላችሁ በሚል ሲያስቆሟቸው በአቅራቢያው የሚገኙ የኦሮሚያ የጸጥታ ኃይሎች ለማስቆም እንኳ ሙከራ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡
ሜክሲኮና መርካቶ ረብሻ ተነስቷል የሚል ወሬ መናፈስ የጀመረ ቢሆንም አካባቢዎቹ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡
ሦስት የጸጥታ ኃይል የጫኑ ካሚዮኖች ከማዘጋጃ ቤት እየወጡ በቸርችል ጎዳና ወደ ሚክሲኮ መንገድ ሲሆዱ ታይተዋል፡፡
አዳዲስ መረጃዎችን በቀጣይ ሰዓታት ይዘን እንቀርበለን