- በርካታ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ፖሊሶች ተሰማርተዋል፡፡
- የወጣት ሊግ አባላት ማንኛውንም የተለየ እንቅስቃሴን እንዲጠቁሙ የተነገራቸው ከአንድ ሳምንት በፊት ነው፡፡
ዋዜማ ራዲዮ- ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ቁጥራቸው ከ150 እስከ 200 የሚሆኑ የማዘጋጃ ቤት የጽዳት ሠራተኞች ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ የመስቀል አደባባይን የአስፋልት ወለልና ደረጃዎች፣ ከሴንጆሴፍ ግድግዳ ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ሙዚየም ጥግጥጉን ሲያጸዱ ነበር፡፡ ሴቶቹ ወደ ጽዳት ከመሰማራታቸው በፊት የሥራ ባጅ መታወቂያቸውን እንዲያሳዩ በአካባቢው የፌዴራል ፖሊሶች በቅድሚያ ከተደረገ በኋላ ነበር ወደ ሥራ የተሰማሩት፡፡
የመስቀል አደባባይን ከኤግዚብዥን ማእከል የሚያዋስነው ግድግዳን ታከው የሚተኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችና በልመና የሚተዳደሩ ዜጎች በሦስት ፖሊሶች አማካኝነት ተሰብስበው በአዲሱ የአዲስ አበባ ሙዚየም መግቢያ በር አካባቢ ከሰማዕታት ሐውልት ኮንክሪት ጣሪያ ሥር እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡
ከትናንት ረፋድ ጀምሮ ባግስ ኮንስትራክሽን ልዩ እንግዶች የሚታደሙበትን የመድረክና የድንኳን ሥራ መገንባት የጀመረ ሲሆን ነጫጭ ጨርቅ የለበሱ ወንበሮችና የድምጽ ማጉያ ተከላ ሥራውን ዛሬ ረፋድ ላይ እያገባደደ ተመልክተናል፡፡ ከድንኳን ግንባታው ጎን ለጎን ነጫጭ የላስቲክ ወንበሮችን የጫኑ የጭነት መኪናዎች በፖሊስ ፍተሸ እየተደረገባቸው ጭነታቸውን ሲያራግፉ ታይተዋል፡፡
እስከ ረፋዱ 4ሠዓት ከ30 ጀምሮ ጥቂት የፌዴራል ፖሊሶች ብቻ በአካባቢው ይዘዋወሩ የነበረ ሲሆን ሰዓቱ እየገፋ ሲመጣ ቁጥራቸው በዚያኑ መጠን ጨምሯል፡፡ ሰሌዳ ቁጥሩ 0463 የሆነ ብረት ለበስ አድማ በታኝ የፖሊስ መኪና ከሰማዕታት ሐውልት ሕንጻ ጎን የቆመ ሲሆን ወደ መስቀል አደባባይ የእግረኞች ሜዳ የሚያልፉ መኪኖች በሁለት ፖሊሶች ፍተሻ ሲደረግባቸው አይተናል፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት አካባቢ የኢቢሲ የቀጥታ ሥርጭት ቫን 5 የካሜራ ባለሞያዎችንና ጋዜጠኞችን እንደያዘ በአካባቢው የደረሰ ሲሆን በመኪናው የሚጎተተው ጄኔሬተር በፌዴራል ፖሊሶች መጠነኛ ፍተሻ ከተደረገበት በኋላ ቫኑ የኤግዚብዥኑን ደረጃ ታኮ ቆሟል፡፡ በቅርብ ርቀት አምስት የአምቡላንስ መኪኖች ፈንጠርጠር ብለው ቆመው ይታያሉ፡፡
የመለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ በመስቀል አደባባይ የተተከሉ የዋንጫ ቅርጽ ያላቸው ብረታ ብረቶችና ጌጣ ጌጦች እየተዘቀዘቁ በፖሊሶች ሲፈተሸ ነበር፡፡ ደመራውን በመሰላል በመታገዝ እያቆሙ ያሉ ካኪ ቱታ የለበሱ ወጣቶች እየተጋገዙ ችቦውን በማዋቀር ላይ የነበሩ ሲሆን ፈንጠር ብለው የቆሙ 5 የፌዴራል ፖሊሶችም በቅርብ ርቀት ቆመው ሂደቱን ሲመለከቱ ነበር፡፡ ሁሉም የሬዲዮ መገናኛ ይዘው የቆሙ የፌዴራል ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ናቸው፡፡
በዛሬው የደመራ በዓል ሁከት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት በማደሩ ከትናንት በስቲያ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ጠንካራ ፍተሻ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ሌሎች ቦታዎች ደግሞ በእግረኞች ላይ ብቻ ያተኮሩ ቀለል ያሉ ፍተሻዎች ሲካዴድ አምሽቷል፡፡
ኤሬቻ፣ ታላቁ ሩጫ፣ የጥምቀት በዓልና የኢድ ሶላቶች ከወቅቱ ፖለቲካዊ ትኩሳት ጋር ተያይዞ ያልተጠበቀ ፖለቲካዊ ሁከት እንዳይፈጥሩ ከፍ ያለ ስጋት በመንግሥት በኩል ያለ ሲሆን ይህንኑ የሚከታተል ልዩ ግብረኃይል የተቋቋመው ከባለፈው የኢድ አልአድሀ በዓል ቀደም ብሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በዓሉን በማስመልከት በነዋሪዎች በኩል ዝቅተኛ ሥጋት ያረበበ ቢሆንም የጸጥታ ኃይሎ ቁጥጥር ሲታይ ስጋትን ከፍ ማድረጉ አልቀረም፡፡ በርካታ የዉጭ እንግዶች ከሚታደሙባቸው በዓላት ቀዳሚው የመስቀል በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአሜሪካና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው በዚህ ኃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳይገኙ ያወጡት የቅድመ ጥንቃቄ መግለጫ የለም፡፡
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ከደምበል ቦሌ፣ ከፒያሳ ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት፣ ከሜክሲኮና ከባምቢስ መኪናዎች ወደ መስቀል አደባባይ እንዳያልፉ የተደረገ ሲሆን ከ830 ጀምሮ እግረኞች መስቀል አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት አስፋልቱን በዘጉ የፖሊስ አባላት ፍተሻ ሲደረግላቸው ነበር፡፡ ቸርችል ጎዳና ቴድሮስ አደባባይ ዙርያ በሁሉም አቅጣጫ የሚያልፉ እግረኞች ፍተሻ ሲደረግላቸው ለመመልከት ችለናል፡፡ በዓሉ ተከብሮ እስኪጠናቀቅ በከተማዋ አብዛኞዎቹ ጎዳናዎች የትራንስፖርት እጥረት ተከስቶ ነበር፡፡ ወደ መስቀል አደባባይ የሚያደርሱ መንገዶች በሁሉም አቅጣጫ መዘጋታቸው የተወሰኑ አደባባዮች ላይ የትራፊክ ጫፋ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ የትራንስፖርት እጥረቱን ተከትሎ ብዙ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለየያ አቅጣጫ በእግራቸው ሲጓዙ ይታያሉ፡፡ ከመስቀል አደባባይ ዙርያ ባሉ ዘለግ ያሉ ፎቆች አናት ላይ የፀጥታ ኃይሎች ቅኝት እያደረጉ ይታያሉ፡፡
በተያያ ዜና በየክፍለ ከተማው የሚገኙ በርካታ የአዲስ አበባ የወጣት ሊግ አባላት ከሳምንት በፊት በከፍለ ከተማ የድርጅት ኃላፊዎች ስብሰባ ተጠርተው የነበረ ሲሆን ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በከተማው ዉስጥ የሚደረግ ማንኛውም የተለየ እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ የወጣት ሊግ አባል ለዋዜማ ዘጋቢ እንደተናገረው ትንሽ ነው ትልቅ ነው ሳትሉ ጥቆማ ስጡን የሚል ጠንካራ መልዕክት እንደተነገራቸው አውስቷል፡፡ ወጣቶቹ በበዓላቱ በተቻለ መጠን ከመታደም እንዳይቦዝኑ የተነገራቸው ሲሆን በርካታ የሲቪል ፖሊሶች ከቀናት በፊት ስምሪት ላይ እንደሆኑ እንደተገለጸላቸው ተናግሯል፡፡
ለመንግሥት ቅርበት ያለው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዛሬ ረፋድ ላይ ባስነበበው ዜና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊዉን ዝግጅት ሁሉ ማጠናቀቁን ዘግቧል፡፡ ኅብረተሰቡም ለበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ የተለመደ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡