- ከትናንት ጀምሮ በአካባቢው የሚገኙ ይዞታዎች በጥድፊያ እየፈረሱ ነው፡፡
- ግንባታው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል
ዋዜማ ራዲዮ- በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 24 በሚባለው ሰፈር ከመገናኛ ወደ ኢምፔሪያል የሚወስደውን ቀለበት መንገድ ታኮ በሚገኝ 40ሺ ካሬ ሜትር ስኩዌር ላይ እንደሚገነባ እቅድ ተይዞለት የነበረው ግዙፉ የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አካዳሚ ትናንት በይፋ የግንባታ ሥራው ተጀምሯል፡፡
ግንባታው በአዲስ አበባ መስተዳደር ወጪ የሚሸፈን ሲሆን ከአንድ ቢሊዮን ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡ ዘጠኝ ሕንጻዎች እያንዳንዳቸው ከ19 ፎቅ እስከ 9 ፎቅ በደረጃ መልክ ዝቅ እያሉ የሚደረደሩበት ኪነ ሕንጻን የተላበሰውን ይህ አካዳሚ ሰፊ ቦታን በመጠየቁ በአካባቢው የሚገኙ ልዩ ልዩ የሕዝብ ይዞታዎችን መውረስና ማፍረስ አስፈልጎታል፡፡
በአካባቢው በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ኤጀንሲ የቦሌ ምድብ ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ የተወሰነ ሲሆን ለጊዜው ለእሳት አደጋው ተለዋጭ ቦታ እየተፈለገለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአካዳሚው አቅራቢያ ይገኝ የነበረው የአዲስ አበባ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የቦሌ ክፍለ ከተማ ማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት መምሪያ በአስቸኳይ ከቦታው እንዲነሳ ተደርጎ ቀድሞ ኮከብ ኮሌጅ ይባል የነበረ ቦታ በኪራይ ቢሮ እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ መምሪያ ይገለግልባቸው የነበሩ ቢሮዎች ትናንት ሙሉ ቀን በግብረ ኃይል እንዲፈርሱ ሲደረግ እንደነበር በስፍራው የተገኘው የዋዜማ ሪፖርተር ለመታዘብ ችሏል፡፡
ከሁለቱ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በተጨማሪም ለረዥም ጊዜ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የእግር ኳስ ሜዳ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው መለስተኛ ስቴዲየም ለህንጻው ግንባታ እንደሚውል ታውቋል፡፡ ከዘጠኙ ተደርዳሪ ሕንጻዎች ረዥሙና 19 ወለሎች የሚኖሩት የሕንጻው ክፍል የሚያርፈውም በዚሁ ስቴዲየም እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህ መለስተኛ ስቴዲየም አዲስ አበባ ከተረፏት ጥቂት የሰፈር የእግር ኳስ መጫወቻዎች አንዱና በመልካም ይዞታ ላይ የሚገኘው እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
በደርግ ጊዜ የጎልማሶች ትምህርት ቤት ሆኖ ያገለግል የነበረውና አሁን ለአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አካዳሚ ግንባታ የተመረጠው ቦታ ከመለስ ሕልፈት በፊት ከፊሉ ይዞታ የአዲስ አበባ ሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡
ግንባታውን የሚያከናውነው ዮቴክ ደረጃ አንድ ኮንትራክተር ሲሆን በአቶ ዮሐንስ ተኽላይ ባለቤትነት የሚመራ ነው፡፡ አቶ ዮሐንስ ተኽላይ በግንባታ ዘርፍ ከፍ ያለ ስም የነበረው የሳትኮን ተቋራጭ ድርጅት ባለቤት የሆኑት የአቶ ሳሙኤል ተኽላይ ወንድም ናቸው፡፡
ለዚህ ግንባታ ዝቅተኛ ዋጋ አቅርቦ የነበረው ዉ ዪ የተባለ የቻይና ኩባንያ እንደነበረና ኾኖም ተቀራራቢ ዋጋ ያቀረቡ የአገር ዉስጥ ተቋራጮች እንዲበረታቱ በሚያዘው መመሪያ መሠረት ግንባታው ለዮቴክ መሰጠቱ ተመልክቷል፡፡ ተክለብርሃን አምባዮ (TACON)ለግንባታው አንድ ቢሊዮን አራት መቶ ሚሊዮን ብር ዋጋ በማቅረቡ ተሸናፊ ሆኗል፡፡ በግንባታው ለመሳተፍ 37 የሚሆኑ አለማቀፍና አገር አቀፍ ተቋራጮች ሰነድ ገዝተው የነበረ ሲሆን ዋጋ ማቅረብ የቻሉት ግን ዮቴክን ጨምሮ አስራ አንዱ ብቻ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አካዳሚ መካከለኛና ከፍተኛ ካድሬዎችን እና የወረዳና ዞን አስተዳዳሪዎችን የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት የሚታወቅ ሲሆን እስከዛሬ ከ8ሺ በላይ ሰልጣኞቹን አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡ ከአጫጭር ስልጠናዎች ባሻገር “ልማታዊ አመራር” የሚል የትምህርት ካሪኩለም ቀርጾ በማስተርስ ዲግሪ “የልማታዊ አመራር ማስተርስ” የሚል ፕሮግራም ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይም በቀጣይ ሁለት አመት ዉስጥ በፒኤች ዲ “የልማታዊ አመራር” ትምህርት ለመጀመር እቅድ ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
መለስ ዜናዊ አካዳሚ በደቡብ ሕዝቦች፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች ቅርንጫፎች ሲኖሩት አዲስ አበባ ደግሞ ዋናው የመለስ ዜናዊ የፌዴራል አካዳሚና የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አካዳሚ መቀመጫ ናት፡፡ አምስቱ አካዳሚዎች በየክልሎቹ በጀት የሚንቀሳቀሱና ራሳቸውን የቻሉ ሲሆን የፌዴራሉ የመለስ ዜናዊ አካዳሚ ግን በቀጥታ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እንዲሆን ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ዜጎች በቀጥታ የስልክ ቴሌቶን፣ በዕጣ ዉድድር፣ ከሰራተኞች ደመወዝ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ እርዳታ መሰብሰቡ ይታወሳል፡፡
ይህ መገናኛ ከገቢዎችና ጉምሩክ ዋና መሥሪያ ቤት ጀርባ የሚገነባው ሕንጻ የፌዴራሉን መለስ ዜናዊ አካዳሚን እንደማይመለከትና በአዲስ አበባ መስተዳደር ሥር የሚተዳደር እንደሚሆን ታውቋል፡፡ እያንዳንዳቸው ከ9 እስከ 19 ወለል ከፍታ ያላቸው ዘጠኝ ሕንጻዎችን የያዘው የአካዳሚው ግንባታ በ3 ተከታታይ ዓመታት ለማጠናቀቅ ከዮቴክ ጋር ዉል የተፈጸመ ሲሆን አገልግሎት መስጠት ሲጀምር 4ሺህ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮችንና ካድሬዎችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም ይኖረዋል፡፡
የአካዳሚው የፌዴራል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ለገሰ ሲሆኑ በቅርቡ ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ተቀናሽ የተደረጉት አቶ ቴድሮስ ሀጎስ አዲሱ ለገሰን ተክተው በዳይሬክተርነት እየመሩት ይገኛሉ፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት ሳሉ ከሥልጣንዎ ሲለቁ በምን ሥራ ለመሠማራት ያስባሉ ተብለው በአንድ ወቅት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምናልባት በሊደርሺፕ አካዳሚ ዉስጥ አስተምር ይሆናል የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ በስማቸው በርካታ አካዳሚዎች መከፈታቸውም ይህንኑ ሐሳባቸውን መሠረት አድርጎ ብዙ መለሶችን ለመፍጠር በሚል ትልም እንደሆነ በመንግሥት ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡