በአውግቻው ቶላ-ለዋዜማ ራዲዮ

አንድ በዕድሜ ገፋ ያሉ አድማጭ ሸገር ሬዲዮ ደውለው “መንግሥት የሚሰማኝ ከሆነ ሐሳቤን በአጭር እንድገልጽ ይፈቀድልኝ!” አሉ፡፡

“እሺ ይቀጥሉ” አለ ጋዜጠኛ፡፡

ጉሮሯቸውን ከጠራረጉ በኋላ “እኔ እንኳ ብዙም የምለው የለኝም….በአጭሩ ሐሳቤን አጠቃልዬ ለመግለጽ ያህል ነው…::” አሉ እጅግ በበዛ ትህትና፡፡

“ይቀጥሉ አልኩ እኮ አባት…ይቀጥሉ” አለ ጋዜጠኛ፡፡

“….እሺ…እንግዲያውስ ከተፈቀደልኝ ልቀጥል… “ለአፍታ ትንፋሻቸውን ሰበሰቡና…

“ኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡ…”

###

እኔ ታዲያ እኚህን አባት ወድጃቸው ልሞት፡፡ አቦ እድሜ ይስጥዎት ፋዘር! አቦ የኢህአዴግን ግብአተ መሬት ለማየት ያብቃዎ ፋዘር!

እንዴ! ልክ ነዋ! ማንም ደራሲ የሸገርን የ25 ዓመት ዘመነ-ሕማማት እንዲህ እንደርስዎ ዉብ አድርጎ የገለፀ የለማ፡፡ ማንም!

ማንም ጋዜጠኛ…ማንም የሕዝብ እንደራሴ ነኝ የሚል…እንደርስዎ አልተረዳንማ፡፡ ማንም የሰብአዊ መብት ተሟጋች…ማንም ተቃዋሚ ፓርቲ እንደርስዎ ግሩም አድርጎ ብሶታችንን አልገለጸልንማ፣ ማንም! ወላ ሰማያዊ ፓርቲ…ወላ አየለ ጫሚሶ…የውነቴን ነው፡፡

አየለ ጫሚሶን ሳነሳ ምን ትዝ አለኝ… አውራው ፓርቲ “ከንግዲህ በብቃት እንጂ በታማኝነት ሚኒስትር አልሾምም” ማለቱን ተከትሎ ጋሽ አየለ ጫሚሶ “ከንግዲህ ጊዜው የኛ ነው ማለት ነው” ብለዋል የሚባለው እውነት ነው? ሃሃ…አሁንስ መጽሐፍ መጻፍ አማረኝ፡፡ “አየለ ጫሚሶ የሚመሯት ኢትዮጵያ እስክትመጣ አልወለድም” የሚል፡፡ አቤ ጉበኛ ወዶ አይደለም “አልወለድም” ያለው፡፡

አንዳንድ ሰዎች “ፍልፍሉ” ያስቀናል ይሉኛል፡፡ እኔ ግን እንደ አየለ ጫሚሶ የሚያስቀኝ የለም፡፡ ኢትዮጵያዊ Jon Stewart ጠፍቶ እንጂ የርሳቸው ነገር ስንትና ስንት ሾው ይወጣው ነበር፡፡ ሰው ግን እንዴት እንዲህ ሁሉ ነገሩ ለኮሜዲ የተመቸ ሆኖ ይፈጠራል?

###

እንዴት ናችሁ ግን የዋዜማ ቤተሰቦች!?

እኔ ያው ደህና ነኝ፡፡ የመሐል አገር ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው፡፡ ምን ቢከፋ ጦሙን አያድር፡፡

ከአመጽ ጋር ተያይዞ ነው የጠፋሁት ብዬ አልዋሻችሁም መቼስ፡፡ ሸገር ለዚያ ቀን ቅርብም ሩቅም ሳትሆን አትቀርም፡፡ ያም ኾኖ #ShegerProtest የሚል ነገር ቶሎ ማየት የናፈቃቸው ወገኖች ያ ባለመሆኑ ክፉኛ ተቀየማችሁ አሉ፡፡

የሸገር ሕዝብ ከሰሞኑ በከሀዲነት ሲወነጀል፣ በወኔቢስነት ሲብጠለጠል፣ በፈሪነት ሲታማ፣ በተንሸራታችነት ሲገመገም ነበር አሉ፡፡ ይሁና! Easier said than done ይላል ፈረንጅ፡፡ ለካንስ ኢህአዴግ ብቻ አይደለም የማያውቀን፡፡ ተቃዋሚዎችም ሕዝቤን አልተረዱትም፡፡

ቆይ ግን!

“ለምን የኔን ሆድ ሲቆርጠኝ እያየህ አንተ የቁርጠት መድኃኒት አልዋጥክም” ይባላል እንዴ ጎበዝ? ሲጀመር ሕመማችን የት ተገናኝቶ፤ ምልክቱም ለየቅል ነው፡፡ እርግጥ ነው ለ25 ዓመታት ራሳችን ላይ ወጥታ ያሰቃየችን ክፉ ወባ አንድ ናት፡፡ ወባዋ የምትነሳብን ግን በተለያየ ጊዜ ነው፡፡ መድኃኒት አወሳሰዳችንም መሆን ያለበት እንደ በሽታችን ጽናት፣ እንደ እድሜያችን ጥናት፣ እንደ የጊዜያችንና እንደየቀዬያችን መሆን አለበት እላለሁ፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም፡፡

ለምሳሌ በዘርማንዘር ጉዳይ እምብዛም ነን፡፡

ሲጀመር የብሔር ፖለቲካ የሚመስጠው አዲስ አበቤ ኢምንት ነው፡፡ አዲስ አበቤ ብሔሩን ከሚያውጅ ኤች አይ ቪ በደሙ እንዳለ ቢናገር ይቀለዋል፡፡ አጥብቀው ዘሩን ቢጠይቁት እንኳ “ሜል ጊብሰን ብሔሩ ምን ነበረ?” ብሎ አላግጦ ላሽ ይላል እንጂ…እንደነንትና…የጠራሁ፣ የነጠርኩ፣ ንጹሕ፣ ኩሩ፣ ወርቅ ቅብርጥሶ ብሔር አባል ነኝ ብሎ አይመጻደቅም፡፡ በሸገር ሰፈር እንጂ ብሔር የኩራት ምንጭ ኾኖ አያውቅም፡፡

አዲስ አበቤ “ማንቼ ነኝ” ይል ይሆናል እንጂ “መንዜ ነኝ” አይልም፡፡

እውነቴን እኮ ነው!

ለመታወቂያስ ቢሆን!

አፍንጫችንን እየያዙ አይደለም እንዴ ብሔራችን የሚያስነጥሱን፣ እንጂማ ባናነሳው እንመርጣለን እኮ፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ዓመት መታወቂያዬን ላሳድስ 12/ቀበሌ ሄጄ ከፊቴ ተሰልፋ ፎርም እየሞላች የነበረች፣ ተቆራጭ ኬክ የመሰለች ቆንጅዬ ልጅ ስልክ ደውላ…. ዳድ! ልንገርህማ…. ብሔር ብሔረሰባችን ምንድን ነበረ? ስትል ሰማኋት፡፡ እኔ ሳቄ አመለጠኝ፡፡ የቀበሌው ሠራተኞች ግን ሁሉም በደፈረሰ የካድሬ ዐይኖቻቸው አጉረጠረጡባት፡፡ ምን ያርጉ…ብዙዎቹ የቀበሌው ሠራተኞች ገጠሬ “ገጠር” ከሚለው ቦታ ነው የመጡት፡፡ ጭራሽ አልተረዷትም፡፡ በጭራሽ!

ዉድ የጦማሬ ወዳጆች!

እውነት እንነጋገር ከተባለ እውነተኛው የሸገር ሕዝብ ከብሔሩ ይልቅ ሰፈሩ ግድ የሚሰጠው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አዲስ አበቤ እኔ “የፈረንሳይ ልጅ ነኝ” ሲል አንድ ትግራዋይ “እኔ ተጋሩ ነኝ” እንደሚለው አይነት አምኖበትና ኮርቶበት ነው፡፡ አንድ የሸገር ወጣት “የኳስ ሜዳ ልጅ ነኝ” ሲል አንድ የሰሜን ሰው ደረቱን ነፍቶ “ኩሩ ጎንደሬ ነኝ” እንደሚለው አይነት በስሜት ተሞልቶ ነው፡፡ እቅጩን ለመናገር ብሔር ለሀቀኛ የሸገር ልጅ ከቤት ቁጥር ከፍ ያለ ዋጋ የለውም፡፡

ይህ ማለት ግን አዲስ አበቤ በኢህአዴግ አልተማረረም ማለት ነው እንዴ? አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን አዲስ አበቤ የራሱ የፖለቲካ አጀንዳ የለውም ማለት ነው እንዴ? አይደለም፡፡ እንዲያውም ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ…እንደ ሸገር ሕዝብ ማን ተበደለ?

በተለይ ከ97ቱ ጦሰኛ ምርጫ ወዲህ በ10 ክፍለከተማ ቆራርሰው ቅርጫ አድርገው ለተከታታይ 11 ዓመታት ይዘነጥሉን ገቡ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ሸገር ሕዝብ አፈር ድሜ ያስጋጠው ሕዝብ አለንዴ? ጢቢ ጢቢ እኮ ነው የተጫወቱብን፡፡

እንዲያውም ኢህአዴግ ለሸገር ሕዝብ “ታሪካዊ ጠላቱ” ነው እላለሁ፡፡

ከኮብልስቶን የተሠራ የሚመስል የማይሰማ የማይለማ ድንዙዝ አግአዚ ጦር ልኮ አይደለም እንዴ ቅልጥም ቅልጥማችንን ያስባለን፡፡ እነሆ ከዚያ ወዲህ ፍልጥ ካድሬ በጉያችን ተሰግስጎ እኔ ካላስተዳደርኩህ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ አንቆ ይዞናል፡፡ ሸገር ከያን ጊዜ ጀምሮ ትንፋሽእንዳጠራት አለች፡፡ ሸገር ከያን ዘመን ጀምሮ ካብራኳ ያልወጡ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሰዎች በከንቲባነት ይደቁሷታል፡፡ እስከዛሬ በቅኝ የገዙን ከንቲቦች ሾላ ገበያ ቢጥሏቸው ቢሯቸው እንኳ ተመልሰው መግባት የማይችሉ እርጥቦች ናቸው፡፡

ለምን ክፉ ደግ እንነጋገራለን ጎበዝ! ኢህአዴግ አይደለም እንዴ እትብታችን የተቀበረባትን አዱ ገነትን ከውብ መናገሻነት ወደ ቆሻሻ ማማነት የቀየረብን፡፡ ሕጻናት በኢህአዴግ ልጅነታቸው አልተቀሙም? ባለቀን ከንቲባዎቿ ፎቅ የእድገት የመጨረሻ መለኪያ ነው ብለው ያምናሉ። ሜዳዎቻችንን ቀሙን፤ ልጅነታችንን ቀሙን፤ ፎቅ ዘሩበት፡፡ ከፎቁ ጋር አብረው ዘረኝነትን ዘሩበት፡፡ ይኸው የዘሩትን እያጨዱ አሉ!

ታዲያ ከሸገር ሕዝብ በላይ የኢህአዴግን ጡጫ የቀመሰ ማን አለ? እኮ ማን?!

ዶክተር መረራ በአንድ ወቅት የሸገርን ምሬት በአጭሩ ሲገልጹ እንዲህ ማለታቸውን አስታውሳለሁ..

“የአዲስ አበባ ሕዝብ እኮ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ከሰማይ ወርዶ ከዚህ ወዲያ ለኢህአዴግ ተገዛ ቢለው በጄ የሚል ሕዝብ አይደለም”

አፌ ቁርጥ ይበልልዎ ዶክተር፡፡ እርስዎ ባለፉት ዓመታት ደጋግመው እንደተነበዩት የራበው ሕዝብ መሪዎቹን ሊበላ እጁን እየታጠበ፣ ቢላውን እየሳለ ይገኛል፡፡ እርስዎ ከገራገሩ የኦሮሞ ሕዝብ በአምቦ በኩል ብቅ ያሉ ጥቁር ነብይ ነዎት!

ዉድ የጦማሬ ወዳጆች!

ሸገር አሁን የምትግኝበትን የሙቀት መጠን ለማስረዳት መለኪያ ቴርሞ ሜትር የለኝም፡፡ ኾኖም ከ15 ቀን በፊት የሆነውን ባወጋችሁ ትኩሳቱ ይገባችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡

የቡሄ ለታ ነው፡፡

እዚህ በሰፈራችን ግንፍሌ ችቦ እንደ ደመራ አዋቅረን ጎረቤቱ ሁሉ ተሰባስቦ እችቦው ላይ ነዳጅ አርከፈከፍንና ልንለኩሰው ስንል ክብሪት ከየት ይምጣ፡፡ እሳት ከየት ይገኝ፡፡ ሕጻን፣ ልጅ፣ አዋቂ ሁሉ አልቀረም እኮ፡፡ ሁላችንም ደጅ ነው ያለነው፡፡ በኋላ እሳት ከጎረቤት ለማምጣት አንድ ልጅ-እግር ወደ እትዬ አስካለ ቤት ሮጠ፡፡ እሱ ክብሪት ይዞ እስኪመለስ እጅግ የምናከብራቸው፣ ሦስት መንግሥታትን አይተዋል የሚባሉትን የሰፈራችን ሽማግሌ ጋሽ ቦጋለን ከበን ጨዋታውን አደራነው፤ ቡሄ በሉ ጨፈርን፡፡ ክብሪት ሊያመጣ የሄደው ልጅ ግን ዘገየ፡፡ ጭፈራው እየተቀዛቀዘ ሲመጣ ጋሽ ቦጋለ ድምጻቸውን ጎላ አድርገው እንዲህ ተናገሩ፡፡

“ልጆቼ! በዚህ ኃይማኖታዊ በዓል ይህን መናገር አልነበረብኝም ይሆናል..፤ ግን እናገራለሁ….የአዲስ አበባ ሕዝብ ማለት ይህ የተቆለለ ችቦ ማለት ነው፡፡ ነዳጅ የተርከፈከፈበት ደረቅ ችቦ ማለት ነው፡፡ ክብሪት የተጫረ ቀን እሳት ኾኖ ገዢዎቹን ይፋጃል፤ ይህ ነው እኔን የሚታየኝ…በሉ ተባረኩ..ከዓመት ዓመት ያድርሰነ፡፡

ያን ምሽት “ከዓመት እስካመት…ድገምነ..ዓመት. ” ሳንል ተለየናቸው፡፡

ያን ምሽት ሌሊቱን እንዲሁ ስንገላበጥ አደርን፡፡ የንግግራቸው ወላፈን ፈጀን፡፡ እኒህ ክብሪት ያጡ አባት ክፉ ሐሳብ ለኩሰውብን እንዴት እንተኛ፡፡ በግሌ ነገ አስጨነቀኝ፡፡ የሸገርን ዕጣ ፈንታ አሻግሬ ማየት ሁሉ ፈራሁ፡፡

እኔምለው…

ብሶት ወለደኝ የሚለው የኢህአዴግ ሠራዊት ግን እየተቀጣጠለ ያለው እሳት እንዴት አይታየውም? እነዚህ ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጪዎች የ30 ዓመት ብሶት ወልዷቸው ሲያበቃ እንዴት ለብሶት ባዳ ኾኑ? እሳቱን ባያዩት እንኳ ጭሱን ማየት እንዴት ተሳናቸው?

ውድ ወገኖቼ!

አሁን ሸገር በምን ሁኔታ ላይ ናት ትሉኛላችሁ! ተስፋም ቆርጣችኋል አሉ ከፊሎቻችሁ! ያን ሁሉ አውቃለሁ፡፡

መቼ ለታ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ሕዝባዊ ተቃውሞ በሸገር ሕዝብ ከፊል ዳተኝነት መክሸፉ አንገታችሁን ሳያስደፋ አልቀረም፡፡ ያንንም አውቃለሁ፡፡ ሐዘን በታወጀ ማግስት የሸገር ሕዝብ አውዳመቱን በአስረሽ ምቺው ማክበሩ ግራ አጋብቷችኋል፤ ያንንም አውቃለሁ፡፡ ቂሊንጦ እስረኛ በጥይት ሲቆላ፣ በሳት ሲለበለብ የሸገር ሕዝብ የሲቲና የማንቼ 2 ለ 1 ዉጤት ሲያንገበግበው ታዝባችሁ ይሆናል፡፡ ያንንም አውቃለሁ፡፡ እመኑኝ ግን፡፡ ሸገር ትግሉን ትቀላቀላለች፡፡ መቼ የሚለውን ነው የማላውቀው፡፡ እንዴት የሚለውን ነው መመለስ የማልችለው፡፡

አንድ አብጠርጥሬ የማውቀውን ጉዳይ ቢኖር የሸገር ሕዝብ በአሁኑ ሰዓት ማፈኛው ተነቅሎ በእጅ የተያዘ ቦንብ መሆኑን ነው፡፡