ዋዜማ ራዲዮ- ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት እግሩን ተክሎ የቆመባቸው አራት የፀጥታ መዋቅሮቹ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና የክልል ልዩ ኃይል ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ክልላዊ መንግስታት በክልላቸው ከሰፈሩት ፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት ሌላ የራሳቸው ልዩ ፖሊስ ወይም ልዩ ኃይል አላቸው፡፡ በእነዚህ ፀጥታ ኃይሎች ቅንጅት ነው እንግዲህ መንግስት እዚህም እዚያም የሚነሱበትን ህዝባዊ ተቃውዎች በኃይል ሲጨፈልቅ እና በህዝቡ ላይ ያለውን ቁጥጥር ሲያጠናክር የኖረው፡፡
የክልል መንግስታት ከ2000 ዓ.ም ወዲህ ነበር ልዩ ኃይሎችን ያቋቋሙት፡፡ ህጋዊ መሰረታቸው ምን እንደሆነ ግን በግልፅ አይታወቅም፡፡ ተጠያቂነታቸው ለክልል ፕሬዝዳንቶች ሲሆን ከፌደራል ፖሊስ፣ መከላከያ ሰራዊት እና ክልል ፖሊስ ጋር ያላቸው ግንኙነት በህግ ምን እንደሚመስልም ግልፅ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስትም በክልሎች ስለሚንቀሳቀሰው ፌደራል ፖሊስ እንጂ ስለ ልዩ ኃይሎች አወቃቀር እና በፀጥታ ጥበቃ ስላላቸው ሚና እምብዛም ሲናገር አይሰማም፡፡ በመሆኑም የልዩ ኃይሎችን ዕዝ ሰንሰለት፣ ብዛት፣ መሳሪያ ዓይነት፣ በህግ የተደነገገ ሚና የመሳሰሉ መረጃዎችን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት ጋር ያላቸው የስራ ግንኙነት ግልፅ አይደለም፡፡ በተሻሻለው ፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይም ከልዩ ኃይሎች ጋር ስለሚኖረው የስራ ግንኙነት አልተጠቀሰም፡፡
በተለይ ባሁኑ ወቅት ደሞ የክልል ልዩ ኃይሎች እንደየሁኔታው የግጭት ተዋናይ ወይም የመንግስት ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ እየታየ ነው፡፡ ለመሆኑ ልዩ ኃይሎች በመንግስት ላይም ሆነ በሀገሪቱ ምን ሚና አላቸው? ምን ስጋትስ ሊፈጥሩ ይችላሉ? የሚሉ ጥያቄዎች መፍታታት ያባቸው አሁን እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ቻላቸው ታደሰ ዝርዝር ዘገባ አዘጋጅቷል እዚህ ያድምጡት፣ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ
ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ብዙዎቹ የሀገሪቱ ክልሎች በአስር ሺህዎች የሚገመት ልዩ ኃይል ወይ ልዩ ፖሊስ ባለቤት ሆነዋል፡፡ ልዩ ኃይሎች የተቋቋሙበት ህጋዊ መሰረት፣ ተጠያቂነታቸው፣ በሙያ ቀኖናቸው ፖሊስ ወይንስ ተዋጊ መሆን አለመሆናቸው፣ በህግ የተደነገገላቸው ዕዝ ሰንሰለት እና ከሌሎች ፀጥታ ኃይሎች ጋር ያላቸው ግንኙነት የመሳሰሉ ጉዳዮች ግን ግልፅ አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ሀገሪቱ መጠነ-ሰፊ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ምናልባት የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ፀጥታ መዋቅር ከመሰረቱ ከተፋለሰ በየክልሉ ያሉ ልዩ ኃይሎች ሚና ስጋት የሚፈጥረው፡፡ በርግጥም ልዩ ኃይሎቹ የዘርፈ-ብዙ ግጭቶች ዋነኛ ተዋናይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋት ማሳደር ከቶውንም ከተጨባጭ ሁኔታው መራቅ አይሆንም፡፡
በእንግዲህ ዓይነቱ ቀውስ ጊዜ ልዩ ኃይሎች ተሳታፊ የሚሆኑባቸውን የግጭት መስኮች በቢሆን ዕድል (scenarios) ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ አንደኛው የቢሆን ዕድል በልዩ ኃይል እና ህዝብ መካከል የሚፈጠረው መጠነ-ሰፊ ግጭት ነው፡፡ ይህ በተለይ በሱማሌ ክልል በተደጋጋሚ ሲታይ ኖሯል፡፡ በያዝነው ዓመትም ህዝባዊ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ወዲህም በየክልሉ ልዩ ኃይሎች ተዋናይ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በርግጥ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሊቀጥል የሚችለው ፌደራል መንግስቱ ከክልል መንግስታት ጋር ቅራኔ ውስጥ እስካልገባ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ያ የመሆን እጅጉን ዕድሉ ደሞ ጠባብ ነው፡፡
ሁለተኛው የቢሆን ዕድል በክልል ልዩ ኃይሎች እና ፌደራል ፖሊስ ወይም በልዩ ሃይል እና በአካባቢው በሰፈረ መከላከያ ሰራዊት መካከል የሚፈጠረው ግጭት ነው፡፡ ልዩ ኃይሎቹ በየክልሉ ገናና ከሆነው ብሄረሰብ የተመለመሉ መሆናቸው ደሞ ለዚህ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የዚህን ቢሆን ዕድል የሚያጠበው ግን ልዩ ኃይሎች ያላቸው ብዛት እና ትጥቅ ከሌሎች ፀጥታ ኃይሎች ጋር የማይመጣጠን መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እስካሁንም የታየ ችግር የለም፡፡
ሦስተኛው የቢሆን መላ ምት በክልል ልዩ ኃይል እና በክልል ፖሊስ መካከል የሚፈጠር ግጭት ነው፡፡ ለዚህ የቢሆን መላ ምት ጥሩ አብነት የሚሆነው በቅርቡ በጋምቤላ በአኝዋክ እና ኑዌር ብሄረሰቦች መካከል ግጭት ሲቀሰቀስ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የክልሉ ፖሊስ በጎሳ ጎራ ለይተው መታኮሳቸው ነው፡፡ ግጭቱን ተከትሎም ከ1500 ሰራዊት በላይ ያለው የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ፈትቶ ስልጠና ሲገባ የክልሉ ፀጥታ እንደተለመደው በፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ለመውደቅ ተገዷል፡፡ ቋንቋ እና ማንነትን መሰረት ባደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር ፀጥታ ኃይሎች ግጭትን በማስነሳት ወይም በማባባስ የሚኖራቸው ሚና ስጋት የሚፈጥረው ለዚህ ነው፡፡
ልዩ ኃይሎች በክልሎች ዋነኛ የፀጥታ ተዋናይ ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሞሃመድ ኡመር ሰላም ርቆት የኖረውን ክልል ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ያረጋጉት በቀጥታ የሚያዝዙትን ልዩ ፖሊስ በመጠቀም እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ራሳቸው የኦጋዴን ጎሳ አባል ሲሆኑ ልዩ ኃይሉንም ያዋቀሩት ከዚሁ ከኦጋዴን ጎሳ ነው፡፡ በተለይ ደሞ ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ምህረት ተደርጎላቸው የተመለሱ የኦጋዴን ጎሳ ታጣቂዎችን በብዛት መልምለዋል፡፡
ሰውዬው ገና የክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ በነበሩበት ጊዜ ነበር ልዩ ኃይሉን ለራሳቸው ሙሉ ታዛዥ እንዲሆን አድርገው ያዋቀሩት፡፡ በሱማሌ ክልል ፖለቲካ-ኦኮኖሚ መዋቅር ውስጥ ልዩ ኃይሉ በኮንትሮባንድ ንግድ ሳይቀር ተጠቃሚ እንዲሆን እንደተፈቀደለትም ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ከእንግሊዙ ልማት ድርጅት ዲኤፍአይዲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከሦስት ዓመታት በፊት የክልሉ ልዩ ኃይል ከ10,000 እስከ 14,000 የሚገት ታጣቂ ነበረው፡፡ በቅርቡ ደሞ 2000 ያህል አዲስ ምልምሎች መቀላቀላቸውን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
አሁን አሁን የአልሸባብ ሰርጎ ገቦች ወደ መሃል ሀገር እንዳይገቡ የብረት አጥር የሆነው ልዩ ኃይሉ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ በኩራት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ አቶ አብዲ ልዩ ፖሊሱን ካጠናከሩ ወዲህም ለክልላቸው ፀጥታ በፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት ላይ የነበራቸው ጥገኝነት መቀነሱን የዋዜማ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ልዩ ኃይሉ ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ታጣቂዎችም ጋር በከፊል መከላከያ ሰራዊትን ተክቶ ሲዋጋ ኖሯል፡፡ ይህም ልዩ ኃይሉ ከፖሊስነት ይልቅ መደበኛ ወታደራዊ ቅርፅ እና ባህሪ መጎናፀፉን አመላካቺ ነው፡፡ ስልጠናም ያገኘው በመከላከያ ሰራዊት መሆኑም የልዩ ኃይሉን የተዋጊነት ወታደራዊ ባህሪ ጠቋሚ ነው፡፡
አቶ አብዲ በልዩ ኃይሉ ላይ ያላቸው ጥብቅ ቁጥጥር መጠንከሩ ግን ክፉኛ የሚያሳስባቸው ወገኖች አሉ፡፡ ባንድ በኩል ባንድ ሀገር ከአንድ በላይ ጦር ሰራዊት የመገንባት አካሄድ ህገ መንግስቱን የሚፃረር ነው፡፡ በሌላ በኩል ለወደፊቱም ለፀጥታ አስጊ ነው፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግጭት ለልዩ ኃይሉ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑም አሳሳቢ ነው፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በልዩ ኃይሉ ላይ የሚያቀርቡት ተደጋጋሚ ውንጀላም ከዚሁ የተጠያቂነት እና ግልፅነት ማጣት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ዲኤፍአይዲ ለኢትዮጵያ ፍትህ እና ፀጥታ ኃይሎች ማሻሻያ ከመደበው ባጀት ውስጥ ለሱማሌው ልዩ ኃይል ስልጠና ከፍተኛ በጀት መመደቡ ውግዘት አስከትሎበት የነበረውም ለዚህ ነው፡፡ ሂውማን ራይትስ ዎች እንደሚለው ከሆነ ፌደራል መንግስቱ ልዩ ኃይሉን በበጀት ይደጉማል፡፡ ምክንያቱ ደሞ ፌደራል መንግስቱ በየጊዜው ከሚቀርብበት ሰብዓዊ መብት ጥሰት በመጠኑም ቢሆን እፎይታ ማግኘቱ ነው፡፡
የልዩ ኃይሉ መጠናከር በፖለቲካው ተቃራኒ አንድምታም አለው፡፡ ለአብነትም የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ከዓመት በፊት አብዛኛዎቹን ካቢኔ አባላቶቻቸውን ከስልጣን ሲያባርሩ ሰዎቹ ወደ አዲስ አበባ ሸሽተው ነበር፡፡ ያኔ ፌደራል መንግስቱ ፕሬዝዳንቱን ወደ አዲስ አበባ ለውይይት ሲጠራ ፕሬዝዳንቱ ግን አሻፈረኝ! ብለው መቅረታቸው በከፊልም ቢሆን በልዩ ኃይላቸው ያላቸውን መተማመን ጠቋሚ ነው- ይላሉ ምንጮች፡፡ የዋዜማ ምንጮች እንደሚሉት አቶ አብዲ እና ልዩ ኃይላቸው ከማዕከላዊ መንግስቱ ይልቅ ጥብቅ ግንኙነት የመሰረቱት በክልሉ የሰፈረውን መከላከያ ሰራዊት ከሚመሩ ከፍተኛ ጦር መኮንኖች ጋር ነው፡፡
ሌላኛው በስጋት ፈጣሪነቱ እየቀጠለ ያለው ፌደራል ፖሊስ ነው፡፡ ፌደራል ፖሊስ በተቋቋመበት አዋጅ መሰረት በክልሎች ጣልቃ የሚገባው በክልል መንግስታት ሲጠየቅ ወይም ክልላዊ መንግስታት ፀጥታን ማስከበር ሲሳናቸው ብቻ ቢሆንም በተግባር ግን ዛሬም ህገ መንግስቱ ተፈፃሚ ሲሆን አይታይም፡፡ የፌደራል ፖሊስም ሆነ መከላከያ ሰራዊት በክልሎች በምን ሰበብ ጣልቃ እንደሚገቡ ወይም ለምን ያህል ጊዜ የክልሎችን ፀጥታ ተቆጣጥረው እንደሚቆዩ መንግስት በይፋ ለህዝብ ሲገለፅ አይሰማም፡፡ ይህም ጣልቃ ገብነቶቹ ከፀጥታ ይልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ለዚህም ይመስላል መንግስት ዋነኛ መተማመኛውን ከክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል ይልቅ በፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት ላይ ሲያደርግ የሚስተዋለው፡፡
የፌደራል ፖሊስ ህገ መንግስታዊ ጥሰት እየጎላ የመጣው ግን ከአራቱ ትላልቅ ክልሎች አንዱ በሆነው አማራ ክልል ፌደራል ፖሊስ በቅርቡ የወሰደው ህገ ወጥ ርምጃ ነው፡፡ በክልሉ ግጭት ተቀስቅሶ የንፁሃን ዜጎች እና ፌደራል ፖሊስ አባላት ህይወት የጠፋው ፌደራል ፖሊስ ያለ ክልሉ መንግስት ዕውቅና እና ፍቃድ በድንገት የወልቃይት ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላትን ለመያዝ ባደረገው እንቅስቀሴ እንደሆነ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግለፁ ይታወሳል፡፡ ርግጥ ነው፣ ጉዳዩ ፖለቲካዊ አንድምታ ስላለው የክልሉ ኮሚንኬሽን ገዳዮች ቢሮ ሃላፊ ስህተቱ የተፈፀመው ከመናበብ እና ቅንጅት ጉድለት መሆኑን ገልፀው ለማስተባበል ተገደዋል፡፡ ዕውነታው ግን ህገ ወጡ ርምጃ የፀጥታ ኃይሎችን ዕዝ ሰንሰለት መዘበራረቅ እና ፀረ-ህገ መንግስታዊነት አግጥጦ ያሳየ ነበር፡፡ ፌደራል ፖሊስም ግጭት በማብረድ ፋንታ የግጭት መነሻ መሆኑን አሳይቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በተለይ በአናሳ ክልሎች ሲደጋገም ስለኖረ ለወደፊቱም ላለመከሰቱ አንዳች ዋስትና ማግኘት አይቻልም፡፡
የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ አባላት ወደ አማራ ክልል በሸሹ ጊዜም ሆነ ተቀማጭነታቸውን ሰሜን ጎንደር ያደረጉ ሌሎች አባላትን የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል/ልዩ ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብቶ እያሳደዳቸው እና ተኩስ እየከፈተባቸው መሆኑን ሲናገሩ ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግስት ሰሚ አላገኙም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ድንበር ተሻጋሪ ከባድ ቅሬታ አጣርተው ለህዝብ ማሰወቅ የነበረባቸው ፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር እና ፌደራል ፖሊስ ቢሆኑም አንዳቸውም አላደረጉትም፡፡ ውንጀላው የሚያሳየው የአማራ ክልል ሉዓላዊነት በፌደራል ፖሊስ ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል ልዩ ፖሊስም መጣሱን ነው፡፡ የሆነው ሆኖ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በግጭቱ ጊዜ ምን አቋም እና ሚና እንደነበረው ገና የተሟላ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡
በርግጥ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት የክልሎችን ርስበርስ ግንኙነት የሚዳኝ ግልፅ ህጋዊ ማዕቀፍ የለውም፡፡ በተለምዶ ግን በየትኛውም ፌደራላዊ ስርዓት ባንድ ክልል ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ወደ አጎራባች ክልል ከተሻገሩ የክልሉ ፀጥታ ኃይል ለአጎራባቹ አቻው ህጋዊ ጥያቄ ያቀርባል እንጂ በማን አለብኝነት ድንበር ጥሶ የኃይል ርምጃ ሊወስድ አይችልም፡፡ ይህ ሁሉ መዘበራረቅ የሚከሰተው የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ከፌደራል ፖሊስ ጋር በየጊዜው የጋራ ጉባዔ በሚያካሂዱባት ሀገር ውስጥ መሆኑ የፀጥታ ኃይሎችን አደገኛ አወቃቀር እና አሉታዊ ሚና ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ፀጥታ ኃይሎች ህገ መንግስቱን አክብረው ከማስከበር ይልቅ በገዥው ግንባር ውስጥ ላለው ያልተመጣጠነ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ሰለባ መሆናቸው ነው እንግዲህ ለዚህ ውጥንቅጥ የዳረጋቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰኔ ወር ባወጣው የምርመራ ሪፖርት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በቅማንት ህዝብ ላይ በደል በማድረሳቸው በህግ ሊጠየቁ ይገባል ሲል ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በርግጥ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም የሱማሌ ክልልን ልዩ ኃይል በኦጋዴን ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ግርፋት ይፈፅማል በማለት ሲከሱት ኖረዋል፡፡ ያንድ ክልል ልዩ ኃይል በቀጥታ በመንግስታዊ ተቋም በይፋ ህጋዊ ተጠያቂነት ሲመጣበት ግን የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የመጀመሪያው ነው፡፡ በብዙ ወገኖች ዘንድ በፖለቲካ ወገንተኝነቱ የሚጠረጠረው ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ከተለመደው ሪፖርት አወጣጡ ባፈነገጠ ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ህጋዊ ውንጀላ መሰንዘሩን ግን ህጋዊ ተጠያቂነትን ከማስፈን ይልቅ ከፖለቲካ ጋር የሚያያይዙት ወገኖች ቀላል አይደሉም፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስትም የኮሚሽኑን ሪፖርት ተቀብሎ በልዩ ኃይሉ አባላት ላይ ህጋዊ ርምጃ ስለመውሰዱ እስካሁን አንድም ፍንጭ የለም፡፡
በጠቅላላው ሲታይ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በፀጥታ መዋቅሩ ላይ መሰረታዊ ለውጥ የማያደርገው አሁን ባለው አወቃቀር ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ ስላልሆነ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙት ውስን ችግሮችም ቢሆኑ መንግስት በስልጣኑ ወይም በህዝብ ላይ ባለው ቁጥጥር ላይ ስጋት የሚፈጥሩ አልሆኑም፡፡ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በፀጥታ ኃይሉ ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያ ለማድረግ የሚገደደው የፀጥታ ኃይሉ ዕዝ ሰንሰለት ላልቶ ለሲቪሉ መንግስት የአለመታዘዘዝ አዝማሚያዎች ካሳየ ወይም በተለያዩ ፀጥታ ኃይሎች መካከል ከባድ አለመግባባት እና ግጭቶች ከተከሰቱ ብቻ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡
በርግጥ ባለፈው ሰኔ ወር በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በፌደራል ፖሊስ ተጠሪነት ላይ መጠነኛ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ፌደራል ፖሊስ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ በማድረግ ፀጥታ ኃይልን የማማከል ስራ ተሰርቷል፡፡ የዕዝ ሰንሰለት ማሻሻያው ግን ፌደራል ፖሊስ የሀገሪቱን ፀጥታ በሰለጠነ መንገድ እንዲይዝ ወይም ህገ መንግስታዊነቱን እንዲጠብቅ በማድረግ ረገድ አንዳችም አወንታዊ ለውጥ ወይም መሻሻል አላመጣም፡፡ ለዚህም አብነት የሚሆነው ፌደራል ፖሊስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአማራ ክልላዊ መንግስት ዕውቅና እና ፍቃድ ውጭ በሰሜን ጎንደር የወሰደው ህገ ወጥ የኃይል ርምጃ ነው፡፡ ህገ መንግስቱን ፈር ድሜ ያበላው ይኸው የማንአለብኝነት የኃይል ርምጃ ከዕዝ ሰንሰለት ለውጡ በኋላ የመጣ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልል፡፡
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በተቀሰቀሰበት ተከታታይ እና መጠነ-ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ክፉኛ መረበሹ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እጁን አጣጥፎ ኖሮ የጦር መሳሪያ ባለቤትነት፣ አያያዝና አጠቃቀምን የሚደነግግ አዋጅ ለማርቀቅ እየተጣደፈ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከተቀሰቀሱ በኋላ መሆኑም ስጋቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህም በህዝብ እና መንግስት መካከል ደም አፋሳሽ ግጭቶች እየተባባሱ ሂደዋል፤ በርካታ ታዛቢዎችም መንግስት በሚወስደው የግድያ ርምጃ ሳቢያ ባንዳንድ ቦታዎች ህዝባዊ ተቃውሞው ወደ ትጥቅ ትግል ሊለወጥ እንደሚችል እየተነበዩ ነው፡፡ በቅርብ በህዝባዊ ተቃውሞው የታዩት አዝማሚያዎችም በመረቀቅ ላይ ባለው አዋጅ ይዘት ላይ በየጊዜው ተፅዕኖ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ አዋጁ በተለይም ገበሬዎችን፣ ስጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚባሉ የክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይሎችን ዒላማ እንደሚያደርግ መገመት ይቻላል፡፡
በጠቅላላው ግን እዚህም እዚያም የሚፈነዱት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ቀውስ እስካልተለወጡ ድረስ ልዩ ኃይሎች ካለባቸው ጥብቅ ፖለቲካዊ ቁጥጥር እና አቅም ውስንነት አንፃር ለመንግስት አደጋ ከመጋረጥ ይልቅ ህዝብን ማፈኛ መሳሪያ ሆነው እንደሚቀጥሉ ይታመናል፡፡ የሱዳኑ አል በሽር መንግስት ጃንጃዊድ በተባሉ አርብቶ አደር ጨካኝ ሚሊሺዎች ታግዞ በዳርፉር ግዛት ለዓመታት የፈፀመውን ሰብዓዊ ወንጀል የሚያስታውሱ ወገኖችም በኢትዮጵያ የክልል ልዩ ኃይሎች በፖለቲካዊ ቀውስ ጊዜ ሊኖራቸው የሚችለው አሉታዊ ሚና እጅጉን ያሳስባቸዋል፡፡