ዋዜማ- ገዢው የብልጽግና ፓርቲ፣ “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል ስያሜ፣ ለፓርቲው አመራሮች ሦስተኛውን ዙር ሥልጠና በመላ አገሪቱ እየሰጠ ይገኛል።

በአዲስ አበባ እየተሰጠ ስላለው የፓርቲው አመራሮች ሥልጠና ዋዜማ እንደሰማችው ከሆነም፣ ከሳምንት በፊት ለ10 ቀናት ስልጠናውን የወሰዱ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በርከት ያሉ ጥያቄዎችን በግላቸው አቅም ብቻ ሰርተው እንዲመልሱ ተደርጓል።

ከባለፈው ሰኞ ዕለት ጀምሮም፣ ለ11 ቀናት የሚቆየውን እና ሦስተኛውን ዙር ስልጠና እየተካፈሉ ያሉ የፓርቲው አመራሮችም፣ እነዚሁኑ ሃያ ሰባት የሚሆኑ ጥያቄዎች፣ እርስ በእርስ ሳይመካከሩ መመለስ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል። ገዥው ብልጽግና ፓርቲ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮቹ እየሰጠ ባለው ሦስተኛው ዙር ሥልጠና ሠልጣኞቹ 27 ጥያቄዎችን በግላቸው አቅም ብቻ እንዲመልሱ እያደረገ መኾኑን ዋዜማ ሰምታለች።

ዋዜማ ከተመከተችው የጥያቄ ወረቀት ላይ ከሠፈሩ ጥያቄዎቹ መካከል፣ “የዳቦ ጥያቄ እያለ የኮሪደር ልማት ለምን መስራት አስፈለገ?” ለሚል ጥያቄ ምን ምላሽ ትሰጣላችሁ? የሚል ይገኝበታል።

ጥያቄዎቹ፣ የኮሪደር ልማት እንዲሁም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻያ ለምን እንዳስፈለገ፣ የአብዮታዊ ዲሞክራሲና የመደመር ቁልፍ ልዩነቶችን ምን እንደኾኑ፣ የሰላም እጦት ቁልፍ ምክንያቶችን፣ ሰላምን ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶችንና ተግዳሮቶችን እንዲሁም ውጭ ጉዳይና ብሄራዊ ትርክትን ማብራራትን ይጨምራሉ።

“የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረግ ለምን አስፈለገ? የሪፎርሙ አንጓዎች ምንድናቸው? ምን አይነት ውጤትስ ያመጣል?” ሲልም፣ ሠልጣኞቹን መልሱ ይላል።


“የአብዮታዊ ዲሞክራሲ እና የመደመር ቁልፍ ልዩነቶችን ምንድናቸው?” ሲል ከሥድስት ዓመታት ከመንፈቅ ገዢ ድርጅትነት በኋላ አመራሮቹን የሚጠይቀው ብልጽግና፣ “በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በውጪ ግንኙነት የምንከተላቸው መንገዶች ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር ያለውን ልዩነት በዝርዝር አስረዱ?” ማለቱን ከጥያቄ ሰነዱ መመልከት ችለናል።

ምንም እንኳን፣ “ህልውና መር” የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ የማያብራራው የድርጅቱ ማሠልጠኛ መጥይቅ፣ “ህልውና መር እይታ ከችግር የማያሻግር የተባለበት ምክንያት ምንድነው?” ሲል አመራሮቹን ይጠይቃል።

ዋዜማ በአዲስ አበባ አድዋ ሙዚየም እየተሰጠ ስላለው የሦስተኛ ዙር ስልጠና እንደሰማችው ሠልጣኞች ሥልጠናቸውን የሚከታተሉት በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አስቀድሞ በቪዲዮ ተቀርጾ የተዘጋጀውን ማብራሪያ በመስማት ነው። ከዚህ በታች የምታነቡት ሰልጣኞቹ የቀረቡላቸው ጥያቄዎች ናቸው (ምንም አርትዖት አላደረግንባቸውም) – በድምፅ ከፈለጉ ደግሞ በማስፈንጠሪያው ይከተሉን- https://www.youtube.com/watch?v=Xp3CjpaN8l4


የአመራር ምዘና ጥያቄዎች

  1. አንድ ሰው ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ችግሮች እያሉ ወይም የዳቦ ጥያቄ ሳይመለስ ለምን የኮሪደር ልማት ትሰራላቹ ቢል ምላሻችን ምንድነው?የኮሪደር ልማት መፍጠር ለምንፈልገው ኢኮኖሚ እና ማሳካት ለምንፈልገው ማህበራዊ ግብ ያለው ዋጋ ምንድነው?
  2. የብልፅግና ማዕከልነት ምንድነው? ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ እና ከውጭ ጉዳይ አንጻር የሀሳብ መነሻዎችን እና ተግባራዊ ምሳሌዎችን በመጥቀስ አስረዱ? ከትርክት አንጻር በመዳሰስ አስረዱ?
  3. አገልጋይነት ስነ-ምግባራዊ አመራር የሚያደርገው ምንድነው?አገልጋይነት ከሌሎች አመራር ዘዴዎች የተለየ የሚያደርገው ምንድነው?አገልጋይ መሪነት ለብልፅግና ተመራጭ የሚሆነው ለምንድነው?
  4. የመደመር መሰረታዊ እሳቤ ከብሔራዊነት ትርክት እና ከህልማችን ጋር ያለው ትስስር ምንድነው?የብሔራዊነት ትርክት እና የሀገራዊ ህልም ትስስር ምንድነው?
  5. ህልውና መር አካሄድን ከሀገራችን ታሪክ ጋር በማያያዝ አስረዱ? ያመጣው ውጤት እና የፈጠረው ውድቀት ምንድነው?
  6. ብልፅግና የእይታ እና የምናብ ለውጥ ነው፡፡ ይህንን የእይታ ለውጥ ከታሪክ ምልከታ እና እጣፈንታችን ከመወሰን አንጻር አስረዱ?
  7. የተለያዩ የተሰሩ ስራዎችና ኢንሼቲቮች መነሻ ህልም እና የሚፈጥሩት አለም እና አቅም ምንድናቸው?
  8. ሳይንስ ሙዚየም፣ አብርሆት፣ ገበታ ፕሮጀክቶች ከፍ ያለ ምናብ እና አርቆ እይታ ውጤቶች ናቸው ሲባል ምን ማለት ነው? ህልማችንን ልዕልና መር የሚያደርገው ምንድነው? የህልማችን መዳረሻ እና ተግባራዊ ምሳሌዎችን በማገናኘት አስረዱ?
  9. የፖለቲካ ገበያ የጋራ ህልማችን እንቅፍት ነው ሲባል ምን ለማለት ነው?
  10. በነባራዊና አለም አቀፋዊ ትንታኔያችን ውስጥ ብዝሀ ቀውስ፣ የመረብ ዘመን እና ድህረ-እውነት የሚሉ ጉዳዮችን ደጋግመን እንገልጻለን፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በማያያዝ እና በማሰናሰል ነባራዊ አለም አቀፍ ሁኔታ ምልከታችንን አስረዱ? እነዚህ እውነታዎች ከሀገራችን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ አንጻር እየፈጠሩ ያሉትን እና የሚኖረውን አወንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖ አስረዱ?
  11. የስነ-ምግባር አስተውሎት/ኢንተለጀንስ ለአመራሩ ቁልፍ የሚያደርገው ምንድነው? ብልፅግናን ለማረጋገጥ እና ለመደመር ስነ-ምግባር አስፈላጊ ነው ቢባል ምን ለማለት ነው?
  12. የለውጥ ዋና ዋና ስኬት ከሆኑት ውስጥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና በውጭ ግንኙነት ውጤቶች አንዳንድ በመዘርዘር ከእነዚህ ውጤቶች ጀርባ ያለውን የሀሳብ መነሻ እና የአካሄድና የመንገድ ልዩነት አስረዱ?
  13. የህግ ማስከበር ተቋማት ሪፎርም በተቋማት ውስጥ እና በሀገር ግንባታ ውስጥ የፈጠረው ለውጥ እና ያመጣውና የሚያመጣው ተጽዕኖ ምንድነው?
  14. ተቋማት ግንባታ የለውጡ መሰረታዊና ቁልፍ ጉዳይ የሆነው ለምንድነው? አመራሩ በተቋማት ግንባታ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ምንድነው?
  15. የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎቻችን ከህልማችን መዳረሻ እና ስኬት ጋር በማያያዝ አስረዱ?
  16. ህልውና መር እይታ ከችግር የማያሻግር የተባለበት ምክንያት ምንድነው?
  17. የሀገራዊ ህልማችን ቁልፍ መዳረሻዎች ምንድናቸው? በዝርዝር አስረዱ?ህልምን ለማሳካት እንቅፋቶች ምንድናቸው? ህልምን ለማሳካት ከአመራሩ ምን ይጠበቃል?
  18. የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ለምን አስፈለገ? የፖለቲካ ሪፎርም ገፊ ምክንያቶች፡-የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት፡-የሪፎርሙ መሰረቶች ምንድናቸው? ውጤታማነቱስ እንዴት ይመዘናል? የፖለቲካ ሪፎርም ውጤታማነት መመዘኛዎች፡-የመሃል ፖለቲካን ባህሪያትና ፋይዳ ተረድቶ የመምራት አስፈላጊነትን አስረዱ? የጠንካራ ፓርቲ ግባችንን ማሳካት ለህልማችን እውን መሆን ያለውን ፋይዳ አስረዱ?የጠንካራ ፓርቲ ግባችንን ማሳካት ለህልማችን እውን መሆን ያለውን ፋይዳ፡-ፓርቲያችንን ለማጠናከር ከአመራሩ ምን ይጠበቃል?
  19. የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረግ ለምን አስፈለገ? የሪፎርሙ አንጓዎች ምንድናቸው? ምን አይነት ውጤትስ ያመጣል?
  20. አብዮታዊ ዲሞክራሲ እና መደመር ቁልፍ ልዩነቶችን አስረዱ? በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በውጪ ግንኙነት የምንከተላቸው መንገዶች ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር ያለውን ልዩነት በዝርዝር አስረዱ?
  21. የሰላም እጦት ቁልፍ ምክንያቶች ምንድናቸው?የብልጽግና የሰላም ግንባታ ግብ ምንድነው? ሰላምን ለማምጣት የምንከተለው አካሄድ ከነባሩና ከተለመደው አካሄድ ጋር ያለው ልዩነት ምንድነው? ሰላምን ለማረጋገጥ ያደረግናቸው ጥረቶች እና የመጡት ውጤቶች ምንድናቸው? የገጠሙን ተግዳሮቶችስ?
  22. ከለውጡ በኃላ ብዙ ኢንሼቲቮች ተጀምረው ውጤት አምጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ኢንሼቲቮች ጀርባ ያለው ሀሳብ፣ የተሰሩበት መንገድ፣ የሚያመጡት ውጤት ምን ለመድረስ  እና ለመፍጠር በማመን ነው? ከሀሳቦቻችን ጋር በማስተሳሰር አስረዱ? እየፈጠሩት ያለው የአመለካከት እና የባህል ለውጥ አስረዱ?
  23. የምግብ ሉዓላዊነት የብልጽግና ቁልፍ አጀንዳ ሆነ? የምግብ ሉዓላዊነት ግቦቻችን   ምንድናቸው? የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ዋና ዋና ስራዎች ምንድናቸው? ያመጡት ውጤትስ?
  24. የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ያለውን ቁልፍ ሀገራዊ ፋይዳ አብራሩ? ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከተቋማት መፈጸም ብቃት እና ከዲፕሎማሲ አንጻር?
  25. የለውጡ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ የአመለካከት እና የተግባር ልዩነት ምንድነው? ዘላቂ ወዳጅነት የመሰረትንባቸው ሀገራት እነማን ናቸው?
  26. ለስኬት እያበቁን ያሉ ቁልፍ የአመራርነት ሚናዎች ምንድናቸው? በሀገራችን ቁልፍ የአመራር ክፍተቶች እና ውድቀቶች ምንድናቸው? በተለይም ለችግር እየዳረጉን ያሉ ቁልፍ የአመራር ክፍተቶች ምንድናቸው? በአመራር ክፍተት ምክንያት የተፈጠሩ ወይም የተባባሱ ቁልፍ ሀገራዊ ችግሮች ምንድናቸው? እንደ ብልጽግና  አመራር ካለፈው መማር እና ማዳበር ያለብን ቁልፍ የአመራርነት ክህሎቶች ምንድናቸው?  አንድ አመራር የብልጽግና አመራር የሚሆነው ምን ሲሆን ነው? ፓርቲያችን የአመራርን ክፍተት ለማረም እየተከተለው ያለው ስትራቴጂ ምንድነው? ምን ይጎድለዋል? ምን ይታረም?
  27. ከዚህ አመራር የቀሰሙትን እውቀት እና ያገኙትን ውጤት ከሚመሩት ተቋም፣ ከሚመሩት ክልል፣ ዞን ጋር በማስተሳሰር በዝርዝር አስረዱ? ከስልጠናው ተነስተው ቀጣይ ግለሰባዊ እቅድ እና ተቋማዊ እና አስተዳደራዊ እቅድ በዝርዝር ያስቀምጡ?

[ዋዜማ]