(ልዩ ዝግጅት) ዛሬ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን ታስቦ ይውላል። የግፍ ፅዋ ሞልቶ በፈሰሰባት ኢትዮዽያ ዛሬም ነገም ሰው በመሆናችን ስለሚገቡን መሰረታዊ መብቶቻችን መከበር እንጮሀለን። በግፍ ታስረው ስቃይ እየተፈፀመባቸው ያሉ ወገኖቻችንን ድምፅ እናሰማለን። ዋዜማና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት በጋራ ለመብታችን እንነሳ፣ ለተበደሉትም እንጩህ አንላላን።
አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን በፈረንጆቹ አቆጣጠር ዲሴምበር 10 ቀን ይከበራል፡፡ ይህ ቀን አንደአውሮፓውያን አቆጣጠር አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ዲክላራሲዬን የጸደቀበት ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ከዲክላራሲዬኑ ተከትሎ የጸደቁት የኢኮኖሚ የማህበራዊ እና የባህል መብቶች እና የሲቪክ መብቶችን የሚያረጋግጡት ሁለቱ የቃል ኪዳን ሰነዶችን 50ኛ አመት በማሰብ ይከበራል ፡፡ ሁለቱ የቃል ኪዳን ሰነዶች የሰው ልጅን የፓለቲካ የባህል የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መብቶችን ሰው በመሆን ብቻ ያገኛቸው መሆናቸውን ያረጋገጡ በመሆናቸው ለአንድ አመት ታስበው እንደሚቆዬ የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡ “መብቶቻቸን ነጻነቶቻችን ሁልጊዜም” በሚል መሪ ቃል የዘንድሮ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን ቀን መሪ ቃል ነው፡፡
[እነሆ ልዩ ዝግጅታችንን በድምፅ ተጋሩት]
አገራችን ኢትዬጲያም አብዛኛዎቹን የሰብአዊ መብት ሰነዶች የፈረመች ሲሆን ከዚያም አልፎ በአገር ውስጥ አንደወጡ ህጎች አንደአንዱ ተቆጥረው ሊከበሩ እንደሚገባ በህገ መንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ በተግባር በተደጋጋሚ በመሸርሸሩ እንደአገር ከምንታወቅባቸው ጉዳዬች ዋናው ጭቆና የመብቶች መጣስ የህገ መንግስቱ አለመከበር ከሆነ ቆይቷል::
እኛ በበኩላችን የዘንድሮን የሰብአዊ መብቶቸን ቀን ሀሳብን በነጻነት መግለጽና መብቶቸን መጠቀም የሚያስከፍለውን ዋጋ እና የሚያመጣቸውን ተከታታይ እና ተጨማሪ የመብት ጥሰቶችን በማውሳትና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በተለያየ ደረጃ ከሚገኙት ብዙ የፓለቲካ እስረኞች መካከል የተወሰኑትን በምሳሌ ለማየት ወደድን ፡፡
ይህንን ፕሮግራም ከዋዜማ ጋር በመተባበር የሚያቀርበው ኢትዬጲያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጄክት የ2001 አመተ ምህረት የወጣውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራትን ህግ ተከትሎ በአገር ውስጥ ያሉ ሰብአዊ መብት ድምጾች በመታፈናቸው እነዚህን ድምጾች ለማጉላት በባህር ማዶ የተቋቋመ መንግሰታዊ ያልሆነ የሰብአዊ መብት ድርጅት ነው ፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ስልጣን በቆየባቸው 24 አመታት በሙሉ ተደጋግሞ የሚነሳው ፓለቲካ እስረኞች አያያዝ ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ በሰፊው ለአደባባይ እየበቃ ይገኛል ፡፡ አጠቃላይ የእስረኞች አያያዝ እና ምርመራ የከፋ እንደሆነ ቢታወቅም የፓለቲካ እስረኞች ላይ ግን አያያዙም ድብደባውም እግዱም ይጠብቃል፡፡
ምሳሌዎችን አንዘርዝር ብንል
ፓለቲካ ፓርቲ መሪው አንዱአለም አራጌን መጠየቅ እንደእድለኛነት ይቆጠራል፡፡ ምንም አንኳን የተጻፈው ህግ በህግ ጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች የመጎብኘት መብታቸው አንዲከበርላቸው ቢደነግግም በተግባር ግን ቃሊቲ ጥበቃዎች ዛሬ ማየት አይቻልም ተመለሱ፣ እሱን መጠየቅ ክልክል ነው ፣ የስጋ ዘመድ ናችሁ ወይ ? ቤተሰብ ናችሁ ወይ ? ስማችሁ ዝም ዝርዝር ላይ የለም የሚሉ ተቆጥረው የማያልቁ እና አንዳቸውም ያልተጻፉ ህግጋትን ይጠቀማሉ ፡፡እድለኛ ከሆኑ ብቻ በድንገት በር ላይ ባለው ጥበቃ በእለቱ ባለው ስሜት ላይ የተመረኮዘ ፍቃደኝነት ይገኛል ፡፡
ይህ በወዳጆች ያለመጎብኘት መብት ጥሰት ሴት የፓለቲካ እስረኞች ላይ ደሞ ይበልጥ የከፋ ነው ፡፡ ይህ ያልተጻፈ ህግ ሴት የፓለቲካ እስረኞችን ለማንኛውም እንቅስቃሴያቸው በፓሊስ ክትትል ስር አንዲሆኑ የሚያዝ ሲሆን ይህ ቤተሰብን ለመጎብኘት ከእስር ክፍል ወጥቶ እስከ ቤተሰብ መነጋገሪያ ድረስ በፓሊስ ከበባ መሄድን ፣ የማረሚያ ቤት ውስጥ ጸጉር ለመሰራት ወይም ድግሞ ሱቅ መሄድን በፓሊስ አጀባ ማከናወን ድረስ ይሄዳል፡፡
በቃሊቲ ያሉ ዞኖች ውስጥ እስረኞች መንቀሳቀስ ቢችሉም ይህ ለፓለቲካ እስረኞች የተፈቀደ አይደለም፡፡ ማረሚያ ቤቱ በሽብር ስለተከሰሱ በተለየ ሁኔታ በአይነ ቁራኛ መታየት አለባቸው ቢልም ሽብር ሳይሆንም አመጽ ማነሳሳት ተብለው የተያዙ ወይም ተቃዋሚ የፓርቲ አባላትም በዚሁ ምድብ ተካተው ከአይነ ቁራኛ ጥበቃ እና ከእስር ቤት ውስጥ ያለ ሌላ እስር አያመልጡም ፡፡
ማንኛውንም ተግባር ለመፈጸም ጸጉር ለመሰራትም ሆነ ሱቅ ለመሄድ ቀድሞ ማመልከት እና አጃቢ ፓሊስ ማግኘት የሚጠበቅባቸው የፓለቲካ እስረኞ ከዚያም በተጨማሪ ከእነሱ ጋር ማውራት አመክሮን መከልከልን ስለሚያስከትል እና ለሽብርተኛ መላላክ በሚል በተለየ ሁኔታ ጥርስ ስለሚነከስባቸው በጣም የተገለሉ እስረኞች ናቸው ፡፡ ይህ ተወርቶ የማያልቀው የእስር ቤት ውስጥ እስር ቤት ደረጃ ከመደረሱ በፌት የፓለቲካ እስረኞች ረጅም መከራን ያሳልፋሉ ፡፡
ምርመራ በማእከላዊ ምርመራ
በነዘላለም ወርቃገኘው የክስ መዝገብ በሽብር ተጠርጥረዋል በሚል ታስረው የሚገኙትን ታሳሪዎች በቅርቡ የሰጡትን ቃል ብንወስድ በኢንተርኔት ጸሃፌው ዘላለም ወርቃገኘሁ 40 ቀናት ጨለማ ከፍል ውስጥ ለብቻው ታስሮ አንደተመረመረ ለአንድ ወር ያህልም ማንንንም የቤተሰብ አባል እንዳላየ ተናግሯል፡፡ ይህ ሂደት አብዛኛው የፓለቲካ ታሳሪ በመአከላዊ ምርመራ ወቅት የሚያጋጥመው ሲሆን በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት የዞን9 ጦማር ጸሃፍያን እና ጋዜጠኞች በማእከላዊ ምርመራ የድረሰባቸውን ድብደባ ፣ እርቃንን ሆኖ መመርመር ፣ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳትና ስድቦች በዝርዝር ይፋ ሆነው ማየታችን ይታወሳል ፡፡
ይህ የማእከላዊ ምርመራ ውስጥ ያለ የማሰቃየት ተግባርን በነዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ 9ኛ ተከሳሽ የሆነው ባህሩ ደጉለፍርድ ቤት የተከሳሽነት ቃሉን ሲሰጥ
“ ማእከላዊ እያለሁ ራቁቴን ተደብድቤያለሁ፡፡ በብሄሬ ላይ የተሰነዘሩ ስድቦችን ተሰድቤያለሁ ፡፡ ደም ስርህን በጥሰን አንገልሃለን፣ ፓሊሱ አቃቤ ህጉ ፍርድ ቤቱ ደህንነቱ ሁሉም የእኛ ነው ፣ 20 አመት እናስርሃለን ተብያለሁ፡፡እርቃኔን ተደብድቤያለው፡፡ በድብደባው የተነሳ ኩላሊቴን ታምሜ ሽንቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር ፡፡ የገዛ ሽንቴንም አንድጠጣ ተገድጃለሁ ፡፡ ከማእከላዊ ድብደባ ተርፌ እዚህ መቆሜ ለእኔ ተአምር ነው” ብሏል
ማእከላዊ ምርመራ ቀጥታ የገቡ ሰዎች የሚደርስባቸው ማሰቃየት ብሄርን እና ማንነትን የሚነካ ስድብ ፣ ከክሳቸው ጋር ያልተያያዙ ጥያቄዎች እና ማሰቃቶች ለወራት የሚቆዬ ሲሆን ሳይከሰሱ ከከፍተኛ ማሰቃየት በኋላ የሚለቀቁ ሲኖሩ ቀድመው መአከላዊ ምርመራ ከመግባታቸው በፌትም በከፍተኛ ስቃይ ምርመራ ውስጥ የሚቆዬ ጥቂት አይደሉም፡፡
ቅድመ ማእከላዊ ምርመራ
ይህ አይነቱ ታስሮ የሚደርስ ማሰቃየት አይነቶቹ ብዙ ሲሆኑ ከሃሮማያ ዬኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ የታሰረው አበበ ኡርጌሳ ከማእከላዊ ከመግባት በፌትም የስቃይ ምርመራ አንዳለ ይናገራል፡፡
“በሩን ከፍቼ ወጣ እንዳልኩ አንዱ ደህንነት በቡጢ መታኝ፡፡ ወዲያው በራሴ ቀበቶ እጆቼን የፊጥኝ አሰሯቸው፡፡ እግሬንም አሰሩኝ፡፡ አካባቢውን በደንብ ቃኘት ሳደርግ ስድስት መኮኖችና 18 ፖሊሶች እንዲሁም 8 ደህንነቶችን (ሲቪል የለበሱ) ቆጠርኩ፡፡ ይሄ ሁሉ እኔን ለመያዝ ነው ብዬ ተከረምኩ፡፡ እመቤት የምትባል እህቴ ‹‹ወንድሜን አትሰሩት›› በማለቷ ደብድበዋታል፡፡ ደጅ ላይ አስረው ትንሽ ከቆዩ በኋላ (ይደዋወላሉ፣ ይጠቃቀሳሉ) ተሸክመው መሀል ላይ ካለው መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ለምን አሰሩኝ፤ ራሴ መኪና ውስጥ እገባላቸው ነበርኮ እያልኩ አስባለሁ፡፡
መኪና ውስጥ አስገብተውኝ ትንሽ እንደተጓዝን ደግሞ መኪኖችን ወዲህና ወዲያ ካሽከረከሯቸው በኋላ ዓይኔን ሸፍነው ሌላ መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ሁኔታው ሁሉ ድብልቅልቅ ሲልብኝ ይታወቀኛል፡፡ የሆነ ቦታ ስንደርስ ‹‹እኛ እንኳን አንተን…›› እያሉ መኪናው ላይ ይደበድቡኝ ጀመር፡፡ ዓይኔ ስለተሸፈነ ወዴት እየወሰዱኝ እንዳለ አላውቅም፡፡ ከዚያ የሆነ ቦታ ወስደው ሲያወርዱኝ ይታወቀኛል፡፡ እዚያ ቦታ ለአምስት ቀናት ያህል ዓይኔን እየሸፈኑ ደብድበውኛል፡፡ ደሞ ከዱላው በላይ ቆሻሻ ስድባቸው አጥንት ይሰብራል፤ ‹‹እናትህ እንዲህ ትሁን…ምናምን…›› እያሉ ይሳደባሉ፡፡ እርስ በእርስ የሚያወሩት በትግርኛ ነበር፡፡
የተያዝኩ ለታ ማታውን ሲደበድቡኝ ነበር ያደሩት፡፡ በድብደባው ምክንያት ኩላሊቴን ታመምኩ፡፡ ሽንቴን መቆጣጠር አልችልም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የነበርኩበት ክፍል ጠረኑ ደስ አይልም ነበር፡፡ በጣም ስታመምባቸው ጊዜ ዓይኔን እየሸፈኑ ሀኪም ቤት ሁለቴ ወስደውኛል፡፡ ግን ስመለስ ድብደባው አይቋረጥም፡፡ ሀኪም ቤቱ የት እንደነበር አላውቅም፡፡ አንዴ ሀኪሟን ‹‹የት ነው ያለሁት›› ብየ ስጠይቃት ‹‹ያመጡህን ሰዎች ጠይቃቸው›› አለችኝ፡፡
በዚህ ሁኔታ የማላውቀው ስፍራ ለአምስት ቀናት ስቃየን ካየሁ በኋላ ግንቦት 22/2006 ዓ.ም ወደ ሌላ ስፍራ ተወሰድኩ፡፡ ለካ አሁን የተወድኩበት ቦታ ማዕከላዊ የሚባለው ኖሯል፡፡ ይሄንም ሰዎች ናቸው የነገሩኝ፡፡
ዘመዶቼ ሞቷል ብለው ነበር የሚያስቡት፡፡ ከተያዝኩ ጀምሮ እስከ ሰኔ 2/2006 ዓ.ም የት እንዳለሁ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ አንድ የሚያውቀኝ ሰው ማዕከላዊ አይቶኝ ነው ለዘመዶቼ ደውሎ ያለሁበትን ቦታ የነገረልኝ፡፡”
በዚህ አያያዝ ውስጥ ተገደው የሰጡት ቃል የሚቆጠርባቸው ታሳሪዎች የፍርድ ቤት ሂደታቸው ላይ ደግሞ ያለፉበትን ስቃይ ተናግሮ ሰጡት የተባለውን ቃል እውነተኛነት አለማሳወቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ እንዲሁም ገለልተኝነቱ በቋፍ ያለው ፍርድ ቤት ደግሞ የታሳሪዎችን መደብደብ ምስክሮች ቢናገሩም ሲገቡ ደህና ሆነው ገብተው ሲወጡ ያነክሱ ነበር ከማለት ውጪ ሲደበደቡ አይነተናል ብለው ስላልመሰከሩ ቃላቸው ተገደው የሰጡት አንደሆነ አላረጋገጥንም በማለት በተደጋጋሚ ምስክርነቶችን ውድቅ ሲያድርግ ይስተዋላል፡፡
በማእከላዊ መርመራ ሳያልፉ በቀጥታ ማረሚያ ቤት የገቡ አንደጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አይነት የፓለቲካ እስረኞች ደግሞ የባሰው እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ተሰምቷል ፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ጀርባ ህመም እና በጆሮ ህመም እየተሰቃ ህክምና የተከለከለ ሲሆን ቤተሰቦቹን ጋር ለመገናኘትም 24 ቀናት ድረስ የሚፈጅበት ወቅት አንዳለ ተነግሯል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በወዳጆች እነደማይጠየቅም የአደባባይ ሚስጥር ነው ፡፡
ከላይ የጠቃቀስናቸው ክስተቶች በከፌል በአደባባይ የወጡና የታወቁ ሲሆኑ ሳይታወቁ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ተቃውሞ ተከትሎ የታሰሩ የሃይሞኖት ነጻነት መብት ጠያቂዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከኦሮሚያ ክልል የሚታሰሩ የመብት ጠያቂዎች ከጋምቤላ ከኦጋዴን ከጎንደር ከሽብርተኛ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ክስ የሚታሰሩ ዜጎች የዚህ ሰቆቃ ሰለባዎች ናቸው ፡፡