ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ግማሽ ህይወታቸውን በፖለቲካ ትግል ያሳለፉ ናቸው። የበየነ የሰላማዊ ትግል መርህ ከበርካቶች ክብርን እንዳስገኘላቸው ሁሉ አብዝቶ “መለሳለሳቸውን” ያልወደዱላቸው ተቺዎች ነበሯቸው። በ1997 ዓ.ም. በነበረው የፖለቲካ ውጥረት ከፊት ረድፍ ተሰልፈው የነበሩት በየነ ያገነገነው የህዝብ ተቃውሞና ያልተጠበቀው የተቃዋሚዎች “ድል” በተቀለበሰበት ወቅት ቀውሱን “በማብረድ” ስማቸው ይታወሳል።

በምሁርነታቸው እና በኢትዮጵያ የሰላማዊ ተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፎአቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መስከረም 7 ቀን 2017 ሕልፈታቸው ተሰምቷል፡፡ ዋዜማ ፕሮፌሰሩን እንዲህ ታስታውሳቸዋለች፡፡

ፖለቲከኛ፣ የዩኒቨርሲቲ መምሕር፣ በአለምአቀፍ ጆርናሎች ላይ ከ120 በላይ ሳይንሳዊ የምርምር ጽሁፎችን ያሳተሙት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተለወዱት በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሐገር ሐዲያ ዞን መጋቢት 1942 ዓ.ም. ነው፡፡ ለጅነታውን በአርሲ ሲራሮ እና ምስራቅ ሐዲያ ያሳለፉ ሲሆን እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በትውልድ አካባቢያቸው፤ 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ደግሞ በሻሸመኔ ኩየራ አድቬንቲት ትምሕርት ቤት ተምረዋል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን አዳማ አጼ ገላውዴዎስ አዳሪ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በሕዋላ ወደ ቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተቀላቀሉ፡፡ ወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የጎላበት በመሆኑ የአገሪቱን እና አለም አቀፍ ሁኔታዎችን እንዲረዱ አስችሏቸዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ በመመረቅ በነበራቸው የላቀ ውጤት በረዳት መሕርነት በዚያው ዩኒቨርሲቲ ተቀጥረዋል፡፡ ቀጥሎም ወደ አሜሪካ አቅንተው የከፍተኛ ትምህርታቸውን ቀጥለው በ 1969 በዊስኮንሲን – ማዲሰን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ የሶስተኛ ዲግሪ ትምሕርታቸውንም በዚያው በአሜሪካ ቀጥለው በትሮፒካል በሽታዎች እና የህዝብ ጤና በ1978 ጨርሰዋል ።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከመጡ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የድህረ ምረቃ እና የዶክትሬት ተማሪዎችን በማስተማር እና በማማከር የሚታወቁ ተመራማሪ ናቸው። የትምህርት ምክትል ሚኒትርነት ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ በአካዳሚክ ማህበራት፣ በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ የሙያ ማህበራት አገልግለዋል። ፕሮፌሰር በየነ ከ1978 እስከ 1983 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር በመሆን የአካዳሚክ እና የምርምር ስራ የጀመሩ ሲሆን በተጨማሪም ከ1981 እስከ 1983 የኢትዮጵያ ባዮሎጂካል ሶሳይቲ መስራች እና ፕሬዝዳንት ነበሩ።

ከ1989 እስከ 2008 የዓለም ጤና እና ልማት ድርጅት አማካሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር እና ከ1979 እስከ 1983 የኢትዮ – ሶቪየት ባዮሎጂካል ጉዞ ሳይንሳዊ ፀሐፊ ፣ በ2006 የፓን አፍሪካ ባዮኤቲክስ ኢኒሼቲቭ (PABIN) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ 2005 በቺካጎ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተጋባዥ ፕሮፌሰር በመሆን ሰርተዋል። በተጨማሪም በብሔራዊ የጤና ተቋማት (NIH) ከፍተኛ የፉልብራይት ባልደረባ በመሆን ስለ ወባ ሞለኪውላር ባዮሎጂ ምርምር ማድረጋቸውን ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ በወባና በሌሎች ጥገኛ ተውሳኮች ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተካሄዱትን የምርምር ፕሮጀክቶች መርተዋል። በተጨማሪም የበርካታ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሙያ ማህበራት አማካሪ ቦርድ እና የኮንፈረንስ አዘጋጅ ኮሚቴዎችን በመምራት አገልግለዋል።

ከአካዳሚክ ክበብ ውጪ ፕሮፌሰር በየነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ በኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሰሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቋቋምና በመምራት ፈር ቀዳጅ ናቸው። በዚህም መሰረት ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ስልጣን በተቆጣጠረበት የሽግግር ዘመን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ኅብረት የተባለ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት በሽግግር መንግስቱ ውስጥ 17 መቀመጫ በመያዝ ታግለዋል። በሽግግር መንግስቱ ውስጥም ከ1983 እስከ 1985 የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እና ከ1983 እስከ 1985 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡

በተጨማሪም ከ1992 እስከ 2002 ድረስ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን አገልግለዋል።በ1997 ምርጫ ወቅት መንግስትን በብርቱ ከተገዳደሩ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ማለትም ህብረት ውስጥ በነበራቸው ከፍተኛ አመራርና ተሳትፎ ይታወሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)ን በፕሬዚዳንት የመሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ ሐሳባቸውን በምክንያትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመግለጽ የሚታወቁ ናቸው፡፡ በ1983 በተመሰረተው ሽግግር መንግስት ወቅት እና በ10 ዓመት የፓርላማ አባልነታቸው ወቅት በዩኒቨርሲቲ መምህርነቴ የሚከለፈኝ ደመወዝ በቂ ነው በማለት ቤት እና ከፓርላማ ደመወዝ እንዳልተቀበሉ በአንድ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ከጥር 6 2014 ጀምሮ የኢፌዲሪ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት (PSI) ዳይሬክተር ሆነው ተሹመው እያገለገሉ የነበሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 7 ቀን 2016 በ75 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡ [ዋዜማ]