ዋዜማ ራዲዮ- በሐዲስ ዓለማየሁ ወራሾች ፍቃድና በሜጋ አሳታሚና አከፋፋይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አሳታሚነት ነው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የኅትመት ብርሃን ያገኘው፡፡
ሜጋ ከ2004 ጀምሮ በተከታታይ ባሉ ዓመታት መጽሐፉን በ10ሺ ቅጂ በየዓመቱ ሲያትመው የቆየ ሲሆን መጽሐፉን በድጋሚ ዕትም ለአንባቢ ሲያቀርብ የዘንድሮው ለ6ኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ቀደም በነበሩት ዓመታት መጽሐፉ በኩራዝ አሳታሚ በኩል ሲታተም ቆይቷል፡፡
‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው የዛሬ 50 ዓመት በ1958 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ የመጽሐፉ የሽፋን ዋጋ 2 ብር ከ45 ሳንቲም ብቻ ነበር፡፡ መጽሐፉ በሥርዓተ ትምህርት ዉስጥ ለአማርኛ ትምህርት ማጣቀሻ አገልግሎት ላይ ይውል ስለነበር ለረዥም ዓመታት በትምህት ሚኒስቴር አማካኝነት በዚሁ ዋጋ እየታተመ ለቤተመጻሕፍትና ለተማሪ ቤቶች ሲከፋፈል ቆይቷል፡፡ የኩራዝ ዕትሞች ደግሞ ከ5 እስከ 7 ብር ሲሸጡ ቆይተዋል፡፡ አሁን መጽሐፉ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ የሽፋን ዋጋው 91 ብር ደርሷል፡፡
በዚህ ሳምንት ገበያ ላይ የዋለው 19ኛው ዕትም የፊደል ማረሚያ፣ መቅድምና ማውጫን ጨምሮ 553 ገጾችን የያዘ ሲሆን አታሚው ‹‹የመስቀል ምንጭ ማተሚያ›› የሚባል ነው፡፡
በአዲሱ ዕትም የጀርባ ሽፋን ገጽ መግለጫ ላይ የተጻፈው የደራሲው አጭር የሕይወት ታሪክ እንደሚያትተው ደራሲ ክቡር ሀዲስ አለማየሁ ሰለሞን በ1902 ዓ.ም ጎጃም ደብረማርቆስ አውራጃ እንዶዳም ኪዳነምሕረት ነው የተወለዱት፡፡ አያታቸው የዜማ መምህር ስለነበሩ እዚው በተወለዱበት አገር በስድስት ዓመታቸው ፊደል መቁጠር ጀምረው አስራ አምስት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ የዜማ ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው ከዚያም ደብረ ኤሊያስ ደብረወርቅና ዲማ በሚባሉ አድባራት እየተዘዋወሩ የቅኔ ትምህርት ተምረው አጠናቀዋል፡፡
በ1918 ዓ.ም አዲስ አበባ መጥተው መጀመርያ በስዊድን ሚሲዮን ቀጥሎም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ በተማሩበት በዚያው በስዊድን ሚሲዮን ቀጥሎም ጎጃም ዳንግላ ደብረማርቆስ በአስተማሪነት ማገልገላቸው ተወስቷል፡፡
በ1928 ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ማስተማሩን ትተው በዚያን ዘመን የጎጃም እንደራሴ ከነበሩት ልዑል ራስ እምሩ ኃይለስላሴ ስር ሆነው ትግራይ ሽሬ ግንባር ዘምተዋል፡፡
ከዚያም በ1929 ዓ.ም በታህሳስ መጨረሻ ላይ ጌራ ላይ ከተደረገው ትልቅ ጦርነት በኋላ ጅማንና ከፋን በሚያዋስነው ጎጀብ ወንዝ ላይ ተከበው ተይዘው ወዲያዉኑ ወደ ጣሊያን አገር ተግዘው በ1936 ዓ.ም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጣሊያንን ድል አድርገው በያዙት በእንግሊዝና በካናዳ ወታደሮች እስኪፈቱ ድረስ ፖንዛና ሊፓሪ በሚባሉ ደሴቶች በኋላም በላይቤሪያ ዉስጥ ሎንግቦኮ በሚባል ተራራማ ገጠር ከሰባት ዓመት በላይ ታስረዋል፡፡
በ1936 ዓ.ም ጣሊያን ተመልሰው በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት፣ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ፣ ተቀማጭነታቸው እንግሊዝ አገር ሆኖ የእንግሊዝና የሆላንድ አምባሳደር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ አምባሳደር፣ ከዚያም መልስ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የሕግ መወሰኛ እና የብሔራዊ ሸንጎ አባል፣ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡
ሀዲስ አለማየሁ በድርሰት ዓለም የመጀመርያ የፈጠራ ድርሰታቸው ‹‹ያበሻና የወደኃላ ጋብቻ›› የተሰኘ ተውኔት ሲሆን በወቅቱ የተመልካችን ልብ የሳበ ነበር፡፡
ደራሲ ሀዲስ ከግዞት ከተመለሱ በኋላ የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም ተረት ተረት፣ ፍቅር እስከ መቃብር፣ ወንጀለኛው ዳኛ፣ የልምዣት፣ ትዝታ የተባሉ ድርሰቶቻቸውን ለአንባቢ አቅርበዋል፡፡
‹‹ማዕቀብ›› በተሰኘ የደራሲ እንዳለጌታ ከበደ መጽሐፍ እንደተወሳው ደራሲ ሐዲስ ደርግ ወደ ስልጣን በመጣ ማግሥት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር እንዲሆኑ ከታጩ ግለሰቦች አንዱ ነበሩ፡፡ እርሳቸው ግን ጥያቄዉን ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡
ደራሲ ሀዲስ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተበረከተላቸው ሲሆን በ94 ዓመታቸው ኅዳር 26፣1996 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ኡራኤል ፕላዛ ሆቴል ገባ ብሎ የሚገኘው የሀዲስ ዓለማየሁ መኖርያ ቤት አሁን አቶ ሰኢድ ካሴ በሚባሉ ባለሐብት ባለቤትነት ይገኛል፡፡
በኢትየጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ከተጻፈበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ለ19ኛ ጊዜ መታተሙ ቢወሳም በጠቅላላ በምን ያህል ቅጂ እንደተባዛ በውል የሚጠቅስ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ኾኖም ለመጽሐፍ ኅትመት ቅርብ የሆኑ ሰዎች እስከዛሬ የታተመው ቅጂ ብዛት ወደ ግማሽ ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገምታሉ፡፡