B. General Kinfe Dagnew former head of METEC


ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬ (የካቲት 26/2011) ውሎው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪን ኮርፖሬሽን(ኢብኮ) የቀድሞ ዋና ሀላፊ ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው ከተከሱሳባቸው 4 ክሶች ውስጥ በአንዱ ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡


ጥር 7 ቀን 2011 ዓም የተከፈተው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ሁለት ክሶችን በውስጡ የያዘ ሲሆን ይህም ኢብኮ የገዛቸውን የሪቬራ ሆቴል፣ ፒቪሲ ፕላስቲክ ማምረቻ እና ኢምፔርያል ሆቴልን የሚመለከት ነበር፡፡


በአቃቤ ህግ ክስ ላይ አንደኛ ተከሳሽ ከሆኑት ከሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው ውጪ፣ኮረኔል በርሀ ወልደሚካኤል፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል፣ ብርጋዴር ጀነራል ብርሀ በየነ፣ ሌተናል ኮረኔል ስለሺ ቤዛ፣ ወይዘሮ ሲሳይ ገብረመስቀል፣ ሌተናል ኮሎኔል አስምረት ኪዳነ፣ ሌተናል ኮሎኔል ግርማ መንዘርጊያ እና ሻምበል አግዘው አልታዬ የተባሉ የኢብኮ የቀድሞ ከፍተኛ የስራ ክፍል ሀላፊዎች እና የግዥ ክፍል ሀላፊዎች ተካተውበታል፡፡
በተጨማሪም ሽያጩን አድርገዋል የተባሉት የአለምገና ቆርቆሮ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁም እና የአክሰስ ሪልስቴት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ በክሱ ተጠቃለዋል፡፡


የአቃቤ ህግ ክስ የአቶ አለም የነበረው ሪቬራ ሆቴል እና ፒቪሲ ፕላስቲክ ማምረቻ ሽያጭ ከኢብኮ ሀላፊዎች ጋር በነበረ የጥቅም መመሳጠር ያለ ጨረታ ተከናውኖ 415 ሚሊየን ብር ኪሳራ በመንግስት ላይ ሊደርስ ችሏል ይላል፡፡ የአቶ ኤርሚያስን ኢምፔርያል ሆቴል በሚመለከት ደግሞ ሆቴሉ በወቅቱ ያወጣል ተብሎ ከሚተመነው ውጪ በ72 ሚሊየን ብር ያለጨረታ በመግዛት በመንግስት ላይ 21 ሚሊየን ብር ኪሳራ አድረሰዋል በማለት የሚያስረዳ ክስ ነበር፡፡


በዚህም መሰረት በጥቅም በመመሳጠር ሀላፊነታቸውን ያለአግባብ ተጠቅመው ከባድ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በማለት አቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሶ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም የወንጀለኛ መቅጫ የስነስርዓት ህጉ አንቀፅ 130 በሚያዘው መሰረት በቁጥጥር ስር ካልዋሉት እና የክስ መቃወሚያ የለኝም ካሉት ሌተናል ኮሎኔል አስምረት ኪዳነ ውጪ የቀሪዎቹን የፅሁፍ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ ተቀብሎ ነበር፡፡


ሜ/ጀ ክንፈ በበኩላቸው በተፈፀመው ድርጊት ጉዳት ደርሷል እየተባለ በጥቅም በመመሳጠር የሚለው ሀረግ ግልፅ አይደለም፣ ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም የሚለው እና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት የሚለው ይጣረሳል የሚሉትን እና ሌሎች ነጥቦችን በማንሳት በጠበቆቻቸው በኩል የቀረበባቸውን ክስ ተቃውመው እንዲሻሻል ጠይቀው ነበር፡፡


ሌሎቹም ተከሳሾች በየግላቸው በዝርዝር የክስ መቃወሚያዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን በመቃወሚው ላይ ክስ መስራቹ አቃቤ ህግም በተናጠል መልስ ሰጥቶበታል፡፡
ይህንን ለመመርመር ጊዜ ወስዶ የነበረው ፍርድ ቤቱ ታዲያ ብይኑን ለመስጠት ዛሬ ጠዋት ተሰይሞ ነበር፡፡


ችሎቱ ዛሬ ሲሰየምም ተከሳሾች ያነሷቸው የክስ መቃወሚያ ነጥቦች የስነስርዓት ህጉን አንቀፅ 130ን መሰረት ያደረገ መሆን ሲገባው በፍሬ ነገር ክርክር መነሳት ያለባቸው ነጥቦች ናቸው የተነሱት ብሏል፡፡


በተጨማሪም በመቃወሚያው የተገለፁትን ዝርዝሮች የአቃቤ ህግ ማስረጃ ሳይታይ ፍርድ ቤቱ አቋም መያዝ አይችልም በማለት ዳኞች ተናግረዋል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግም ችሎቱ በየእዳንዱ ተከሳሽ መቃወሚያ ላይ የመረመረውን በተናጠል በማንበብ የሁሉንም መቃወሚያ ተገቢነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡


የስነስርዓት ህጉን መሰረት አድርጎ የሚከናወነው የችሎት ሂደት ቀጣዩ ተግባር የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል መቀበል በመሆኑ ፍርድ ቤቱም ቃላቸውን ተቀብሏል፡፡

በዚህም መሰረት ሜ/ጀ ክንፈን ጨምሮ በህግ ጥላ ስራ ያሉት የዚህ መዝገብ ተከሳሾች በጠቅላላ የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቃቤ ህግም የተከሳሾቹን ምላሽ ተከትሎ ማስረጃዎቹ እንዲመረመሩለት እና ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙለት ችሎቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህጉን ምስክሮች ከመጋቢት 30 ጀምሮ ለመስማት ቀጠሮ በመያዝ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ለፌደራል ፖሊስ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ በምርመራ ወቅት 20 የሚደርሱ የወንጀል አይነቶች ቀርበውባቸው የነበሩት ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው ላይ ከላይ ከተጠቀሰው የሆቴል ክስ በተጨማሪ ከመርከብ ግዥ ፣ ከትራክተር ግዥ እና የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ ጋር በተገናኘ 3 ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡


በቀጣይ በመርከብ ግዥ ላይ በተመሰረተው ክስ እና መቃወሚያ ላይ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ የያዘ ሲሆን በትራክተር ግዥ እና በትምርት ማስረጃ ላይ ለቀረቡት ክሶች በከፊል ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]