US Ambassador Ervin Massinga-FILE

ዋዜማ- በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በመንግስትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ድርድር እንዲደረግ ለማመቻቸት የተቋቋመው ምክር ቤት ዛሬ በአሜሪካ ኤምባሲ ከዲፕሎማቶች ጋር እንደሚወያይ ዋዜማ ተረድታለች። 

ከተቋቋመ ከሁለት ወራት በላይ ያስቆጠረው የአማራ ክልል የሰላም ምክር ቤት ከአሜሪካ በተጨማሪ አፍሪካ ኅብረት እና ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የልማት ባለስልጣን (ኢጋድ) ጨምሮ ከተለያዩ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ጋር  ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ተረድተናል።

ምክር ቤቱ ከአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጋር ዛሬ ነሀሴ 29/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚነጋገር ምንጮች ገልጠዋል። የሰላም ምክር ቤቱ ከአምባሳደሩ ጋር በሚያደርገው ውይይት ስለ ገጠመው ፈተና እና ሁለቱን ኃይሎች ወደ ድርድር ለማምጣት አሜሪካ ስለሚኖራት ሚና እንደሚወያይ ዋዜማ ተረድታለች።

በተመሳሳይ ዛሬ ነሀሴ 29/2016 ዓ.ም ምክር ቤቱ  ከኢጋድ የሰላም እና ደህንነት ክፍል ጋር ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ይዟል።

እንዲሁም ለአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉደዮች፣ ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽን ቀጠሮ እየጠበቀ ነው። በቀጣይም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአገራት አምባሳደሮች እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ተቋማት ጋር የመነጋገር እቅድ እንዳለው ምንጮች ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የሚመክረው ገጠሙኝ ባላቸው ውስብስብ ችግሮች ላይ እንዲደግፉት ነው።

ካውንስሉ ከአምባሳደሮች እና ከሌሎች የዲፕሎማቲክ ማኅበሰብ አካላት ጋር በሚያደርጋቸው ውይይቶች የክልሉን ቀውስ ሁኔታ ያስረዳል ተብሏል። እስካሁን መንግሥት እና የፋኖ ታጣቂዎችን ለማግባባት ባደረገው ጥረት ካውንስሉ የገጠሙት ችግሮች ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እንደሚያስረዳ ምንጮች ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ መንግሥት እና የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ግፊት እንዲፈጠር ይፈልጋል ተብሏል። የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን የድርድር ማመቻቸት ጥረቱ አካል አድርጎ ለማስቀጠል ያቀደው ምክር ቤቱ፣ ከዲፕሎማሲያዊ ጫና በተጨማሪ የቴክኒክና የሎጀስቲክስ ድጋፍ እንደሚፈልግ ዋዜማ ተረድታች።

እስከ ተኩስ አቁም የሚደርስ የቅድመ ድርድር ሁኔታ ለማመቻቸት የተቋቋመው ምክር ቤቱ ፈተናዎች እንደገጠሙት ዋዜማ የተመለከተችው የግምገማ ሰነድ ያስረዳል። የሰላም ምክር ቤቱ ገጥመውኛል ካላቸው ውስብስብ ፈተናዎች መካከል በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ያለው ስር የሰደደ አለመተማመን አንዱ ነው።

ሌላኛው ምክር ቤቱ ገጥመውኛል አካላቸው ችግሮች መካከል የፋኖ ታጣቂዎች አንድ ወጥ አደረጃጀት አለመኖር ነው። የፋኖ ታጣቂዎች አደረጃጀት የወሎ፣ የሸዋ፣ የጎንደር እና የጎጃም በሚል በተናጠል አደረጃጀትና መሪ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ምክር ቤቱ በግምገማ ሰነዱ ላይ ጠቅሷል።

እንዲሁም በክልሉ እና በአጎራባች ክልሎች የቀጠለው አለመረጋጋት እና ሁከት ለሰላም ምክር ቤቱ እክል እንደሆነበት ይገልፃል። ክልሉ እንደ በትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች በኩል የብሔር ግጭት አውድ መቀጠሉ ለሰላም ምክር ቤቱ ጥረት እንቅፋት መፍጠሩን ያስረዳል።

ካውንስሉ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር ወደ ውይይት ከማምራቱ በፊት በመንግሥት በኩል ከክልል እስከ ፌደራል ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መክሯል። በክልል  ደረጃ ከአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደ ጋር እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ከሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ጋር ከሰሞኑ መወያየቱን የዋዜማ ምንጮች አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ለ ምክር ቤቱ አረጋግጧል ተብሏል። ይሁን እንጂ በምክር ቤቱ በኩል የፌደራል መንግሥት ከፋኖ ጋር እንደሚደራደር በግልጽ አቋም ይዞ ይፋ እንዲያደርግ ፍላጎት መኖሩን ዋዜማ ተረድታለች።

ይሄንኑ ይሁንታ ከፌደራል መንግሥት ለማረጋገጥ ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ለማነጋገር እቅድ መያዙን ዋዜማ ሰምታለች።

በፌደራል መንግሥት በኩል ከአንዳንድ የፋኖ ክንፎች ጋር ንግግር እንደተጀመረ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኔ ወር መጨረሻ መናገራቸው የሚታወስ ነው። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር መጀመሩን ቢገልጡም በሰላም ምክር ቤቱ በኩል ድርድር ስለመጀመሩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተረድተናል።

የክልሉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ የተቋቋመው 15 አባላት ያሉት የሰላም ምክር ቤቱ ሰሚ አግኝቶ ለድርድር መጀመር የሚያበቃ ውጤት ማምጣት አልቻለም። [ዋዜማ]