ዋዜማ- ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እና የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ፣ በባሕር በር ውዝግብ ሳቢያ በአገሮቻቸው መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ቁርሾ ለመፍታት ትናንት ምሽት በፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን አሸማጋይነት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ኹለቱ አገራት አንዳቸው የሌላኛቸውን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማክበር፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የንግድ ማዕቀፎችን ለመፍጠር እና በአንዲት ሱማሊያ ማዕቀፍ ሥር ለኢትዮጵያ ዘላቂ የኾነ የባሕር በር ለማስገኘት ተስማምተዋል።

ዐቢይና ሞሐመድ፣ በኹለቱ አገሮች መካከል በባሕር በር ውዝግብ ዙሪያ ውጥረት ከተፈጠረ ወዲህ በፕሬዝዳንት ኤርዶጋን አቀራራቢነት ለመጀመሪያ ጊዜ እጅ ለእጅ ተጨባብጠዋል። መሪዎቹ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።


አዲሱ የመሪዎቹ ስምምነት ዝርዝር ይዘት ይፋ ባይደረግም ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት ከሶማሊያ ጋር በሚደረስ የጋራ ትብብር ስምምነት ለመፈፀም መሪዎቹ እንደተስማሙ በፅሁፍ ያወጡት መግለጫ ያመለክታል።

የመሪዎቹ ስምምነት ከአንድ አመት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የባህር በር ኪራይ የማግኘት ዕቅድ ያሰናክለው እንደሆነ በይፋ አልተገለፀም።


የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን መሀመድ በመግለጫው ሀገራቸው የኢትዮጵያን የባህር በር የኪራይ ፍላጎት እንደሚረዱና ለዚህም ለመተባበር ፈቃደኛ ነን ብለዋል። መሀመድ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሰላም የከፈሉትን መስዋዕትነት ሀገራቸው ዕውቅና እንደምትሰጥ አውስተው ምስጋናም አቅርበዋል። [ዋዜማ]