ዋዜማ- የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉንም አገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ፖለተካ ፓርቲዎችን ለማወያየት ወደ አዲስ አበባ አስጠርተዋል።
ለአገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እና ጸሐፊ ወይም የጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና ሦስት የሥራ አስፈፃሚ አባላት በድምሩ ስድስት ተወካዮች እንዲሳተፉ እድል ተሰጥቷቸዋል።
ከክልላዊ ፓርቲዎች ደግሞ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እና ጸሐፊ ወይም የጽሕፈት ቤት ኃላፊ በድምሩ ሦስት ሰዎች ተጋብዘዋል፡፡
ዐቢይ ለውይይት የጠሯቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች የሦስት ቀን ፕሮግራም እንደተያዘላቸው ዋዜማ ለፓርቲዎች ከደረሰው ፕሮግራም ተመልክታለች።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመወያየት የሚገኙ የፓርቲ መሪዎች በቅድሚያ፣ ነገ እሁድ መጋቢት 22/2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዋና ዋና የልማት ሥራዎችን ይጎበኛሉ።
ከጉብኝቱ በኋላ የፊታችን ሰኞ መጋቢት 23/2016 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ውይይት ያደርጋሉ። በሦስተኛው ቀን ፕሮግራም ማክሰኞ መጋቢት 24/2016 ዓ.ም ስልጠና ይወስዳሉ።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረገው ውይይት ላይ እንዲሳተፉ የቀረበላቸውን ግብዣ ውድቅ ያደረጉ ፓርቲዎች መኖራቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በማካሄደውን ውይይት አንሳተፍም ካሉት መካከል፣ አብዛኛዎቹ “የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ” የተሰኘው የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስብስብ አባላት ናቸው።
በአሁኑ ወቅት 13 አባላት ያሉት ስብስቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረገው ውይይት ተሳትፎ ላይ የጋራ አቋም መያዙን የኮከሱ አባላት ለዋዜማ አረጋግጠዋል።
የኮከሱ አባል ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ ላለመሳተፍ መወሰናቸውን፣ የኦከሱ አባል የሆነው የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ለዋዜማ ተናግረዋል። የስብስቡ አባል ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ተሰብስበው የመከሩ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት ዘጠኝ ፓርቲዎች የውይይት ተሳትፎውን ውድቅ አድርገዋል ተብሏል።
ምንም እንኳን የኮከሱ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ለማድረግ የቀረበውን ግብዣ ውድቅ ቢያደርጉም፣ ልዩ የፓርቲ ጉዳይ ያላቸው አባላት መሳተፍ እንዲችሉ ስምምነት ላይ መደረሱን ግርማ ጠቁመዋል።
ፓርቲዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ ያልሆኑት፣ “መንግሥት ለይስሙላ አወያየሁ ከማለት የዘለለ” የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀሳብ የመቀበል ፍላጎት የለውም በማለት መሆኑን ገልጸዋል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ሦስት የፓርቲ መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚደረገው ውይይት፣ “የተለየ ነገር አይፈጥርም” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡት ከዚህ ቀደም በተለይ በሰላም ጉዳይ ተደጋጋሚ የመፍትሔ ሀሳብ አቅርበው፣ በመንግሥት በኩል እንደ አማራጭ ከመቀበል ይልቅ በተደጋጋሚ ገፍቶናል የሚል ነው።
በፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ ሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ፣ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲ ግንባር (ዎሕደግ)፣ አገው ለፍትህና ዴሞክራሲ ፓርቲና ሌሎችም የኮከሱ አባላት ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት የክልሎች ተወካዮችን፣ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችን፣ ባለ ሀብቶችንና ሴቶችን በየተራ አወያይተዋል። [ዋዜማ]