• የአማራና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ጉዳይ አብይ አጀንዳ ነው

ዋዜማ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በተለያዬ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሊወያዩ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር የውይይት ቀጠሮ የያዙት በየክልሎቹ የተካሄደው የመንግሥትና የፓርቲዎች ውይይትን ተከትሎ ነው ተብሏል። ከአንድ ወር ገደማ በፊት የሁሉም ክልሎች ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ከተቃዋሚ የፖለተካ ፓርቲዎች ጋር በየፊናቸው ውይይትት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ለዚሁ ውይይት ፖለተካ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ተወካይ እንድመድቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ቀርቦላቸዋል። መሳተፍ የሚችሉት የየፓርቲዎቹ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ወይም ጸሐፊ መሆን እንዳለባቸው ዋዜማ የተመለከተችው የግብዣ ደብዳቤ ያመላክታል።

የውይይት ገብዣውን የተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ውይይቱ ወደሚካሄድበት ሱሉልታ ሐምሌ 13/2016 ዓ.ም ማቅናታቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።

ውይይቱ የሚካሄደው ዛሬ ሐምሌ 14 እና ነገ ሐምሌ 15/2016 ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲሆን፣ ቦታው ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ነው ተብሏል።

የመጀመሪያው ቀን ውይይት የሚመራው በገዥው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል። 

አደም በሚመሩት በመጀመሪያ ቀን ውይይት ላይ የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች በዕለቱ ማታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባል ተብሏል። የመጀመሪያ ቀን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የአደም ፋራህ ውይይት ጭብጥ የሚደርሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማግስቱ ሰኞ ውይይቱን ይመራሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በፓርቲዎች በኩል የውይይት ሰነድ ማዘጋጀቱን የምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ምንጭ ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

የምክር ቤቱ ስነድ በመጀመሪያው ቀን መድረክ ላይ ቀርቦ ወይይት ከተደረበት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት በሁለተኛው ቀን ደግሞ ዋና ዋና አጀንዳዎች ተለይተው ይቀርባሉ።

ምክር ቤቱ ለመድረኩ ያዘጋጀው ሰነድ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከክልል ፕሬዝዳንቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የተነሱ አጀንዳዎችን አሰባስቦ ነው። የጋራ ምክር ቤቱ ያዘጋጀው የመወያያ ሰነድ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ ሰላምና ጸጥታ እስከ ጎረቤት አገራት አሁናዊ ግንኙነት ያካተተ መሆኑን የምክር ቤቱ ምንጮች ጠቁመዋል።

ሰነዱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያነሷቸው ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ብሎ ከለያቸው መካከል የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ ችግር ይገኝበታል። የምክር ቤቱ ሰነድ የቀጠለውን የሁለቱን ክልሎች የጸጥታ ችግሮች መንግሥት “በሀቀኛ ድርድር ለምን መፍታት አልተቻለም” የሚል ጥያቄ አዘል አጀንዳ ይዟል።

የፖለተካ ምህዳር ጉዳይ በምክር ቤቱ ሰነድ ለውይይት ከተዘጋጁ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳ መካከል ተካቷል። ከዚህ አንጻር እንደ ዋና ጉዳይ የተጠቀሰው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስርና ወከባ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እስከ መፈጸም የደረሰ ነው የሚል ግምገማ በሰነዱ ተመላክቷል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር አሁን ላይ ስላላት የዲፕሎማሲ ግንኙነና የባህር በር ጉዳይ በሰነዱ የውይይት አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል። 

ሌላኛው በተፎከካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ጥያቄ ተስቶበት የውይይት አጀንዳ ሆኖ የቀረበው ጉዳይ፣ ተፎካካሪዎችን ሥልጣን አጋርቶ አብሮ መስራት የሚባለው የገዥው ፓርቲ አካሄድ ነው። ጉዳዩ የውይይት አጀንዳ ሆኖ የቀረበው በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የመርህ ጥያቄ ተነስቶበት መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከወራት በፊት በተመሳሳይ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን አራት ኪሎ ተጋብዘው ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። [ዋዜማ]