ዋዜማ ራዲዮ- ግብፅ በኢትዮዽያ ላይ ስጋት በመፍጠር ጫና ለማሳደር አዲስ ስትራቴጂ አውጥታ መንቀሳቀስ ከጀመረች ቢያንስ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል። የግብፅ ስትራቴጂ በዋንኝነት በኢትዮዽያ ውስጣዊ ድክመት ላይ የተመሰረተና በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ህልውና በመገዳደር ላይ ያነጣጠረ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ኢትዮዽያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እንድትለሳለስ ያለመ ነው። ይህን ነባር የግብፅ ስትራቴጂና አደጋውን የተረዳው የሚመስለው የኢትዮዽያ መንግስት ተጨማሪ የደህንነት ሰዎቹን ወደካይሮና ወደ ጎረቤት ሀገሮች ለማንቀሳቀስ ሞክሯል።
ግብፅ በጓሮ በር ከምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ይፋዊ ወታደራዊና የደህንነት ምክክሮችን ከኢትዮዽያ ጎረቤቶች ጋር ማድረጓንም አጧጧፋ ቀጥላለች። ኬንያ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ሶማሊላንድ አንድ በአንድ ባለፉት ወራት ከካይሮ ጋር በጠረዼዛ ዙሪያ ታድመው ተመካክረዋል።
በኤርትራ ፕሬዝዳንት አማካሪ የማነ ገብረአብ የተመራ የልዑካን ቡድንም በአሁኑ ሰዓት (May 18)ካይሮ ይገኛል። ከሁለት ወራት በፊት የማነ ገብረአብ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩን ኦስማን ሳለህን አስከትለው ወደ ግብፅ ተጉዘው የነበረ ሲሆን በሁለቱ ሀገሮች መካከል ስለሚኖረው ትብብርና ስለ አካባቢያዊ ጉዳዮች ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አል ሲሲ ጋር ተወያይተዋል።
የግብፅ መከላከያ ሚኒስትር ጄነራል ሰዲ ሶቢህ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ (May12-13)ከሱዳን ወታደራዊ ደህንነት ኃላፊ ጄነራል አሊ ሙሀመድ ሳሌም ጋር በካይሮ ተገናኝተዋል። የሁለቱ ወታደራዊ ባለስልጣናት ውይይት በዝርዝር ባይገለፅም በደፈናው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር በማጠናከር ዙሪያ ባሉ “የጋራ አሳሳቢ ጉዳዮች” ላይ መምከራቸው ተነግሯል።
በውይይቱ ላይ በርካታ የግብፅ ወታደራዊ መኮንኖች የተሳተፉ ሲሆን የወታደራዊ ደህንነት ኃላፊያቸውን ተከትለው ወደ ካይሮ ያቀኑ የሱዳን ልዑካኖችም ተሳትፈዋል። የሱዳኑ ከፍተኛ ወታደራዊ ሰው ከግብፅ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሌፍተናት ጀነራል መሀሙድ ሄጋዚ ጋር በመከላከያ ሚኒስቴር ዋና ፅህፈት ቤት መገናኘታቸውም ተዘግቧል።
በሱዳንና ግብፅ መካከል የሰነበተ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ያለ ሲሆን ሱዳን ጉዳዩ በድርድር እንዲፈታ ትፈልጋለች። ግብፅ ጉዳዩን በዓባይ ውሀ ላይ ላላት ፍላጎት እንደመደራደሪያ ለማቅረብ ስትሞክት ቆይታለች። በተለይ ሱዳን ከኢትዮዽያ ጎን መሰለፏ ካይሮን አስኮርፎ ቆይቷል። በቅርቡ ሱዳንም ሆነች ግብፅ ከሳዑዲ ዐረቢያ ጋር በጀመሩት አዲስ ወዳጅነት አስታከው ልዩነታቸውን ለማጥበብ ሙከራ እያደረጉ ነው። ውይይቱ በዚሁ ጉዳይ ላይ ስለመሆኑ አንዳንድ ፍንጮች አሉ። የሊቢያ ቀውስም ሱዳንና ግብፅን የሚያነታርክ ሌላው ጉዳይ ነው።
የኢትዮዽያ መንግስት ለሱዳን መደለያ በማቅረብ የሀይል ሚዛኑን ለመጠበቅ እየጣረ ይገኛል። በተለዋዋጭ አቋሙ የሚታወቀው የሱዳን መንግስት ለኣኢትዮዽያ ዘላቂ ጥቅም ዋስትና መስጠት ስለመቻሉ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
የግብፅ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሌፍተናት ጀነራል መሀሙድ ሄጋዚ ከሁለት ሳምንት በፊት የኬንያ አቻቸውን ሳምሶን ማዋቴቴን በተመሳሳይ በካይሮ ተቀብለው አስተናግደው ነበር። ግብፅ በቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደሯ ሞሀመድ ኢድሪስ የሚመራ የልዑካን ቡድን ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ወደ ሶማሊያ ሞቃዲሾ እና የሶማሌላንዶቹ ሀርጌሳና በርበራ መላኳ ይታወሳል። በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የወታደራዊ እና ደህንነት ሰዎች ነበሩበት።
ግብፅ ሙከራዋ ሳይሳካ መቅረቱም በሶማሊያ የጦር ሰፈር ለመመስረት የነበራት ዕቅድ በሶማሊያና በሶማሊላንድ መሪዎች ውድቅ መደረጉ ተሰምቷል። የግብፅ ልዑካን ወደ ካይሮ ሲመለስ ግን ከሶማሊያ ይሁንታ ማግኘቱንና ሞቃዲሾ ከምርጫ በኋላ አቋሟን እንደምታስታውቅ ሪፖርት አድርጓል።
በሱዳን በግብፅና በኢትዮዽያ መካከል ታሪካዊ ሰነድ ተፈርሟል ሲል ለሰነበተው የኢትዮዽያ አስተዳደር ስጋቱንም ይሁን ሁኔታውን አውጥቶ ለመናገር እንዳልደፈረም እየተነገረ ነው።