ዘመናዊት ኢትዮጵያን በኹሉም መልኳ ከቀረፇት መሪዎች መካከል አፄ ኅይለ ሥላሴ ቀዳሚ መሆናቸው ላይ፣ የዘመናዊ ታሪኮቻችን ፀሐፍት ብዙም ሙግት ውስጥ አይገቡም። የጣሊያንን የአምሥት ዓመት ወረራን ቀንሰን፣ ከ1909 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1923 ድረስ በአልጋ ወራሽነት፤ ከ1923 ዓ.ም. እስከ 1967 መግቢያ ያሉትን ዓመታት ስንቆጥር፣ በጥቅሉ ለአምሣ ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያን በጠንካራው መዳፋቸው ሥር አቆይተዋታል።

የምኒልክ በአድዋ ጦርነት መዘዞች መያዝ እና የደቡቡ ግዛት ማስፋፋት ደም አፋስሽ ሂደት ፍፃሜውን ሲያገኝ፣ አስቀድመው ኢያሱን ከዚያም ዘውዲቱን ገፍተው መንበሩ ላይ የተገኙት ተፈሪ፣ አገሪቷን ከዘመናዊነት ጋር ለማስተቃቀፍ በመሞከር ስማቸው በክብር ይነሳል። ከዘመናዊ ትምሕርት እስከ ሕገ-መንግሥት ማቆም፣ ከጦር ኅይል ግንባታ እስከ ሊግ ኦፍ ኔሽን ምሥረታ የደረሱ አበርክቷቸው፣ ከእነ ግድፈቶቻቸው የታሪካቸው ደግ ገፆች ናቸው። 

ከህልፈታቸው 49 ዓመታት በኋላ፣ በዘመናቸው ከተፃፉላቸው አወዳሽ መዛግብትም ሆነ፣ በተለይም ከተማሪዎች ንቅናቄ በወጡ ፀሐፍት በብዙ ድርሳናት ከወረደባቸው ውግዘት ሻገር ያሉ ምርመራዎችን ጊዜው ግድ የሚል ይመስላል። ስለ ዘመናቸውም፣ ተደጋግመው ሊነሱ የሚገባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመኖራቸው፣ የዛሬያችን ኹሉን ዓቀፍ ድቀቶች በቂ መግፍዔዎች ይመስላሉ። 

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መካከል ካገኙት የአልጋ ወራሽነት ጅማሯቸው አንስቶ፣ በደም እስከተነቀሉበት 1960ዎቹ አጋማሽ ድረስ ባሉት ጊዜያት፣ እጅጉን ሲለዋወጡ ከነበሩት ሁነቶች ጋር ራሳቸውን አላምደው፣ እንደፈቀዱት አገሪቷን ቀረፇት? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ፣ የአፄውን ውርሶች በቅጡ የሚያሳየን ይመስላል። ከግብፅ እስከ ሶሪያ፣ ከከረን እስከ ሊግ ኦፍ ኔሽን ድረስ የጭቃ ላይ እሾኽ ሆኖ የቸገራቸው የኤርትራ ዳግም ውኽደት ጉዳይ፣ ከጅምሩ የከሸፈ ወይስ ሌላ ማንም ሳይሆን ራሳቸው የመጨረሻውን ምዕራፍ አበለሻሹት? ለሚለው መለስ ቀለስ እያለ ለሚሰማው ጥያቄም የሚሰጠው መልስ፣ ብዙ ድሮችን ይፈታል፤ አልያም ጠቅለል ስናደርገው፣ ከጣሊያን ወረራ በኋላ የመሩት ግዛተ-አፄ፣ ከውስጣዊው ባህሪው አኳያ፣ ደም ከማሽተት ባለፈ ለመሻሻል ፍፁም ያልተመቸ ነበርን? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ፣ ዛሬያችንን ጭምር በቅጡ እንድንረዳ ዋጋ ያለው ድርሻ አለው።

እኒኽን እና ሌሎች ተራዛሚ ጥያቄዎችን በቀጥታ ባይመልሱልንም፣ ብዙም ሲነሱ ያላስተዋልናቸውን አልያም የተለዩ ፍንጮችን የሚያቀብሉንን ኹለት መፃሕፍት በወፍ በረር እናያቸው ዘንድ መርጠንላችኋል።

በጥቂት ዓመታት ልዩነት የታተሙት እኒኽ ሁለት መፃሕፍት፣ የግብም፣ የይዘትም ተቀራራቢነታቸው አየል ይላል። እነርሱም፣ የአዛውንቱ የኢትዮጵያ አጥኚ ሃጋይ ኤርሊክ፣ “Haile Selassie: His Rise, His Fall” እና የዶክተር ልዑል ራስ አስፋ ወሰን ዓሥራተ ካሳ “King of Kings: The Triumph and Tragedy of Emperor Haile Selassie of Ethiopia” ናቸው። እነዚኽ ድርሳናት ቀዳሚ የጋርዮሽ ጠባያቸው፣ አንድን ፀሐፊ እና መፅሐፍ ከአፄው የታሪክ ፅሕፈት ማጣቀሻነት ቢቻል ለመፋቅ ያለሙ መሆናቸው ነው።

የዕድሜ ተቀራራቢነት ያላቸው ኹለቱም ፀሐፍት እንዲህ ጉልበታቸውን ሊያጠፉበት የመረጡት ሰው ራይስዛርድ ካፑሼንስኪ ይባላል። የእነ ኤርሊክንም ሆነ፣ የብዙ የተፈሪን ወዳጆች ያስቀየመበት፣ “THE EMPEROR፡ Downfall of an Autocrat” የተሰኘችው የጎበዝ መዳፍ የምታኽለው ኪስ ገብ መፅሐፍ፣ በአብዮቱ ማግስት ስትታም፣ በተለይም ደርግ እጅጉን ሲሻው ለነበረው ለወቅቱ ጃንሆይ ጠልነት መንፈስ ሁነኛ ስሜት መቀስቀሻ ክኒን ሆናለትም ነበር።

መፀሐፏ፣ ፖላንዳዊው ጋዜጠኛ ካፑሼንስኪ፣ ለብዙ ዓመታት ከአልጋ አንጣፊነት እስከ ትራስ ያዢነት፣ ከምግብ አብሳይነት እስከ ትንሿ ወዳጃቸው ከነበረችው ውሻይቱ ሉሉ ተንከባካቢነት ድረስ ካለማጉረምረም ያገለገሉትን፣ በወቅቱ ቋንቋ ድምፅ አልባ የአፄውን አሽከሮች ቃለ-መጠይቅ ያደረገባት መፀሐፍ ናት። ራስ አስፋ ወሰን፣ ባልተረጋገጡ መረጃዎች የተሞላ ሲሉት፣ ፕሮፌሰር ሃጋይ በበኩላቸው፣ “የኅይለሥላሴ ትዝታ በመጥፎ መንገድ እንዲቀመጥ ከሰሩት ሰዎች መካከል ትልቁን ቦታ ይይዛል” ሲሉ ያብጠለጥሉታል። 

የሆነው ሆነና፣ እነዚኽ መፃሕፍት ከሚሉን እና ብናስታውሳቸው ከሚጠቅሙን የአፄው የሕይወት እጥፋቶች መካከል ጥቂቶቹን እያነሳሳን እንውረድ። “ሃሳበ ግትር” ሲሉ የሚጠሯቸውን አፄ ኅይለ ሥላሴን በዘመነ-ሥልጣናቸው ጭምር ያጠኗቸው ኤርሊክ፣ “በራሳቸው ግርማ እና ግዙፍነት በመጋረዳቸው የተነሳ፣ ዝናቸው ሲቀዘቅዝ ያልታወቃቸው ሰው ነበሩ” የሚለው ፍርዳቸው፣ ተለምዷዊውን የኢትዮጵያን ገዢዎች ባህሪም ይገልጣል።

በዚህ ያላበቁት እስራኤላዊው የታሪክ አጥኚ፣ ተፈሪ በተለይም በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን፣ ወደ ቀጣዩ የፍፅምና ንግሥና ለሚያደርጉት መንደርደር እንቅፋት ይሆናሉ ያሏቸውን መሣፍንት እና ልዑላን ከማዕከላዊ ሥልጣኑ እየገፉ ሲሄዱ፣ ኋላ እራሳቸውንም ለስደት፣ አገሪቷንም ለወረራ መዳረጋቸውን ጠበቅ አድርገው ይነግሩናል። “የማዕከላዊ መንግሥቱ መጠናከር፣ ለእርሳቸው የኢትዮጵያን ነፃነት ማስከበሪያ ሆኖ ይታያቸው ነበር፡ በዚህ መንገድ መሄዳቸውም፣ በሁለተኛው ወረራ ኢትዮጵያ እንድትሸነፍ አስተዋፅዖ አድርገዋል” ሲሉም ከባዱን መደምደሚያቸውን ያስነብቡናል።

የአሜሪካንን፣ የእንግሊዝን እና የጣሊያንን ከዚህ ቀደም ሌሎች አጥኚዎቻችን ለማግኘት ቸግሯቸው የነበሩትን አፄውን አስመልከቶ የተሰነዱ መዛግብትን ማግኘት የቻሉት ፕሮፌሰር ኤርሊክ፣ የተፈሪን የሕይወት ግቦች በሦስት ይጠቀልሏቸዋል፤ እነርሱም፣ “በመፀሐፍት ብቻ ያነበብኩቱን የአውሮፓ ሥልጣኔ በአይኖቼ ማየት፣ ስመለስ ከአየኋቸው አንዳንዶቹን በአገሬ ማስጀመር እና የባህር በር ማግኘት” የሚሉ ናቸው የሚሉን ሃጋይ፣ “ቅዱስም፣ ፍፁማዊ ንጉሥም መሆንን ሻቱ፤ ተሳካላቸው ይሆን?” ሲሉም እኛኑ መልሰው ይጠይቁናል። በእርግጥም የአምሳ ሦስት ዓመታት የገዢነት ዘመናቸውን ከውግዘትም፣ ከቡራኬም ራቅ ብሎ ለተመለከተው፣ በከፊልም ቢሆን እኒህን ሦስት የሕይወት ግቦቻቸውን በሆነ ልክ ማሳካታቸውን አሌ አይልም።

“እንደ እርሳቸው ዓለምን የጎበኘ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መሪ አይገኝም” የሚለው የራሳቸው የኤርሊክ ድምዳሜ የመጀመሪያውን ጥያቄ ሲመልስልን፣ በመግቢያችን ያነሳናቸው፣ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ የምትኮራባቸውን ተቋማት እርሾ ማስቀመጣቸውን ስናስታውስ፣ ለሁለተኛው የፂዮናዊው አጥኚ ምላሹን እናገኛለን። የባህር በሩ ጉዳይ፣ እንኳንም እርሳቸውን እና ገዢውን መደባቸውን፣ የአፍሪካ ቀንድን ካርታ ጭምር በቀየሩ መዘዞች ቢሞላም፣ መመለሳቸውን ጠቅሰን እንለፍ። በእኚሁ የታሪክ ፀሐፊ ብዕር፣ “ከአባታቸው እና ከምኒልክ ውጪ የሚያከብሩት ሰው ጥቂት ነው”

የሚለው ገለፃ፣ የቀጣዩን ግማሽ ክፈለ-ዘመን የኢትዮጵያ እጣ ያሳብቃል። በእርግጥ ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤርሊክ ከእውነቱ ያፈነገጠ ሐረግ የተጠቀሙ አይመስለንም። ትንሽ ዘግይቶ፣ ከኤጄርሳ ቦሩ የተነሳው ብላቴና ሊሄድበት የመረጠውን መንገድ በሚገባ ይነግረናልና፤ ይኽም ከቅርብ ዘመዳቸውም፣ ከእኩያቸውም ልጅ ኢያሱ ጋር ዋኝተው የወጡትን ነባሩን የሸዋ ፖለቲካ ክርብርብቶሽ ያስታውሰናልና ጨዋታውን ጠቅሰነው እንለፍ።

     ሸዋም፣ ታሪክም የጨከነበት ብላቴና

የተፈሪ እና የልጅ ኢያሱ የምኒልክ ወራሽነት ግብግብ፣ ከዚያ ጀምሮ እስከአሁን የቀጠሉ ብዙ ክሮችን የጎተተ፣ ዳፋዎችንም ያስከተለ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ትራጄዲ ነው።  የፈረንሳዊው ስመ-ጥር አጥኚ የእነ ሼሜዲት እና ወዳጆቹ፣ “The Life and Times of Lij Iyasu of Ethiopia: New Insights” እስኪመጣ ድረስ፣ ስለ ልጅ ኢያሱ ሚዛን የሚደፋ ተረክ ያገኘነው አንድም እንደ ጎበዜ ታፈጠ “አባ ጤና ኢያሱ” እና እንደ መሃመድ ሃሰን “ማለት የምፈልገው” ዓይነቶቹ እና በየጥናታዊ መፅሔቶቹ ላይ በብዙ ዓመታት ልዩነት ከሚደርሱን መጣጥፎች ውጪ፣ ደህና የሚባል ጥናት ተነፍገን ሰንብተናል። በእርግጥ እነዚኽ ኹለት ድርሳናትም ታላቁን ሚስጥር ባያፈነዱትም፣ ጥቁምታዎችን ግን ያቀብሉናል።

ራስ አስፋ ወሰን፣ ከተፈሪ እና ከእቴጌ መነን ጋብቻ ጀርባ ልጅ ኢያሱ ስለመኖሩ፣ “ሁኔታዎቹን አመቻችቷል” ሲሉ ረገጥ አድርገው ይጠቅሳሉ። “ኢያሱን በመንቀል ምንም ጥያቄ በሌለው መንገድ ዋናው ተዋናይ ተፈሪ ናቸው” ሲሉም፣ በረዥም ገመድ የሚዛመዷቸውን አፄ ኅይለ ሥላሴን ከፊት ያደርጓቸዋል። በዚህ በኩል ሃጋይ ኤርሊክ፣ “ተፈሪ መፅሐፍ ሲያነቡ፣ ኢያሱ ወሎው እና አዳሩ መሸታ ቤት ነበር” ሲሉ የተለመደውን ነባር ክስ ሲያስተጋቡ፣ አስፋ ወሰን በበኩላቸው፣ ለኢያሱ ውድቀት ወሳኙ ሚና የአውሮፓ ኅይሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ከባድ ተፅዕኖ መሆኑን በስፋት ለመዘርዘር ጥረዋል።

ይሄ ከዚያ የጀመረው የአውሮፓውያኑ ሰፊ ጣልቃ ገብነት፣ ብዙ ዓሥርታትን ተሻግሮም፣ አንድም በእነ መለስ ዜናዊ እና በእነ ስዬ አብርሃ የዘጠናዎቹ መጀመሪያ የሥልጣን ትግግል ውስጥ፤ አንድም በወቅቱ ቲም ለማ ሲባል በነበረው ቡድን እና በሕወሓት ሰዎች መካከል ወሳኝ ሚና ሲጫወት አስተውለናል። በአስራ ስድስተኛው ክፍለ-ዘመን “ግራኝ” ባልነው ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ እና በሰሜን ተገዳዳሪዎቹ መካከል የነበረውን ውጊያ ሚዛኑን የቀየረው የፖርቱጋሎች ዘሎ መግባት፣ በአፍሪካ ቀንድ ጭምር የመጀመሪያው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከተባለ (አሁን ሰላም አስከባሪ እንዲሉ)፣ የኢያሱን ክንድ ያላላው የእነ እንግሊዝ ጣልቃ ደግሞ፣ የመጀመሪያው የአራት ኪሎ ጓሮ መደፈር አድርገን ልንቆጥረው የሚቻል ይመስላል።

 የሆነው ሆነና፣ ነገሩ ግን ምን ነበር? ሃጋይ ኤርሊክ እንደሚነግሩን፣ የሸዋ ፖለቲካን ናቅ ያደረገው ኢያሱ፣ አንኮበርን ዘሎ በአንድ በኩል የምሥራቅ ኢትዮጵያውያኑን ሙስሊሞች ከስሩ ለማሰለፍ እና ኦቶማኖችንም ከጎኑ ለማድረግ ላይ ታች ሲል፤ ተፈሪም ወደ ምዕራቡ ዞሩ። “በምኒልክ ሞት ማግስት ኢያሱ የአዲስ አበባውን የቱርክ ቆንስላ ይዘው ራሳቸውን ‘ወጣት ቱርኮች’ ከሚሉት ጋር አቆራኙ” የሚሉት ሃጋይ ኤርሊክ፣ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ኦቶማኖች አውሮፓ ላይ ጂሃድ ሲያውጁ፣ የአዲስ አበባው የኅይል ሚዛን ላይመለስ ተቀያየረ ይሉናል።

የአንድ የእንግሊዝን ሰነድ ጠቅሰውም፣ ልጅ ኢያሱ ሐረር በሚገኝ አንድ መስጂድ ውስጥ ፀለዩ የሚሉን ሃጋይ፤ የኢያሱ አብደላህ ሳዲቅን የሐረር ሙስሊሞች መሪ እና የተፈሪ ምክትል አድርጎ መሾም ነገሮችን እንዳወሳሰባቸው ይጠቅሳሉ። ከዚህ ባሻገርም፣ በአገሪቷ ምሥራቃዊ ክፍል ኦቶማን ቱርክን የሚያወድሱ፣ በተቃራኒው ደግሞ እንግሊዝን እና ክርስትናን የሚያንቋሽሹ በራሪ ወረቀቶች መበተናቸውን የሚነግሩን ኤርሊክ፤ ከአላህ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ የሚናገር ፁሑፍ ያለበት የኢትዮጵያ ባንዲራ ድሬደዋ ላይ ተውለበለበ ሲሉ በአደባባይ ሲነገር የነበረውን የሸዋ ሃሜት ምሁራዊ ድጋፍ ይሰጡታል።

ከሁለቱ ዘመዳማቾች ከባድ የወራሽነት ትግል መካከል፣ ተረካቸውን ወደ ተፈሪ ለማድረግ ያሏቸውን ምንጮች ሁሉ የተጠቀሙት እስራኤላዊው ፀሐፊ፣ እንግሊዞች ኢያሱ ላይ ያሴሩትን ግን ላለመጥቀስ ሲጥሩ ይታያል። ልዑል አስፋ ወሰን በበኩላቸው፣ እንግሊዞች ልጅ ኢያሱ የሙስሊም ቆብ አድርጎ የሚያሳይ የውሸት ፎቶ ሰርተው መበተናቸው፣ ከውጪያዊው ተለዋጭ እኩል የትግል ሜዳውን ወደ ተፈሪ እንዲያዘነብል ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ያትታሉ። ምናልባትም ይኽ የብሪታኒያውያኑ ክፉ ሴራ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ፎቶ ሾፕ ሳይሆንም አልቀረም።

ሁለቱም ፀሐፊዎች የሚስማሙበትን የኢያሱን መጨረሻ ከመጥቀሳችን በፊት፣ እስከ አሁን ከቀረቡልን መፀሐፍት በአስፋ ወሰን ዓሥራተ ካሳ መፀሐፍ ላይ ብቻ ያለ የመሰለንን አንዲት ሁነት በወሽመጥ እናስገባ። ከሠገሌው ጦርነት በኋላ ጊዜ ከርሱ ጋር ያልነበረውን ኢያሱ ከአዲስ አበባ ማራቅ ብቸኛ መፍትሄ አድርገው የቆጠሩት ኅይለ ሥላሴ፣ ወደረኛቸውን በአደራ አስሮ የሚያቆይላቸው ሲያፈላልጉ የፀሐፊውን አያት ያገኛሉ።

አያትየው ራስ ካሳ ኅይሉ ፍቼ ባለው የግል ቤታቸው አስቀምጠው ምን አይነት እንክብካቤ ሲያደርጉለት እንደቆዩ የልጅ ልጃቸው ሲገልፁም፣ ብዙ ክፍሎች ባሉት ቤት ውስጥ ያሰቀመጡት እንደ እስረኛ ሳይሆን እንደንጉሥ ነበር ይላሉ ። ወደ ኢያሱ ክፍልም ሲገቡ፣ ጫማቸውንና ካባቸውን አውልቀው መሆኑን የሚነግሩን ፀሐፊው፣ እንዳይመረዝ በመስጋትም ምግቡን የሚሰሩለት ባለቤታቸው እንደነበሩ የመጀመሪያ ደረጃ ምንጫቸውን ጠቅሰው ፅፈዋል።

ምግቡም የሚቀመጠው የራስ ካሳ ባለቤት እና ኢያሱ ብቻ ቁልፉ ያላቸው ሳጥን ውስጥ መሆኑንም ሲያክሉልን፣ ስለ ወቅቱ የቤተ-መንግሥቱ ቤዛንታዊ ፖለቲካ አንዲት ፍንጭ ይሰጠናል፤ ይኸውም፣ በራስ ካሳ አዕምሮ ይመላለስ የነበረው፣ ምናልባት በአንዳች ማለዳ፣ ዘውዲቱን ለስሙ ቢያስቀምጥም ወራሽ ይጠብቅ የነበረው የምንሊክ መንበር ወደ ኢያሱ ሊዞር ይችል ይሆን? የሚለውን እርግጠኛ አልባነት ነው፤ ስለምን ቢሉ፣ በነባሩ የአገረ-መንግሥቱ ሥልጣነ-ፖለቲካ፣ ወደረኞቹ በአረር ካለየላቸው በቀር ጊዜ ለማንም ዋስትና አይሰጥምና።

ወደ ፀሐፍቱ መስማሚያ መላምት ስንመለስ፣ የኢያሱን መጨረሻ አስመልክቶ፣ አስፋ ወሰን “ኢያሱ ከሞሶሎኒ ጋር ያብራል ብለው የሰጉት ተፈሪ፣ እንዲገደል አዘው ድንበሩን ተሻገሩት” ሲሉን፤ ሃጋይ በበኩላቸው “ለሐረር ቅርብ በሆነ ዋሻ ውስጥ የነበረውን ኢያሱ፣ ሞሶሎኒ እስልምናን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያስፋፋ ሲዝት እንዲገደል አዘዙ” ሲሉ የአስፋ ወሰንን መረጃ ይደግፉታል። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት አስከ አሁን ውግዘቱ እንዳልተነሳለት የሚነገርውን ልጅ ኢያሱ፣ ከውግዘቱ ለማላቀቅ የልጅ ልጁ ፕሮፌሰር ግርማ ዮሓንስ አቡነ ጳውሎስን ቢጠይቁም እምቢ ተብለዋል የሚለውን የአስፋ ወሰንን መረጃም በህዳግ ማስታወሻነት ብንጠቅሰው የሚከፋ አይመስልም።   

 ልጅ ኢያሱን በዚህ መልኩ ከመድረኩ የገፉት አፄ ኅይለ ሥላሴ፣ ሲመኙት ወደ ነበረው የምኒልክ መንበር ሲያማትሩ፣ አንድ ተግዳሮት ገጠማቸው፤ ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ። ለዘውዲቱም ሆነ ለተፈሪ ቅርበት ከነበራቸው ሹማምንት መካከል አንዱ የሆኑት ደጃዝማች ኅይለማሪያም ገሰሰ አጫወቱኝ ሲሉ መረጃውን እንካችኹ የሚሉን አስፋ ወሰን፣ ምናልባትም እስከ አሁን ያልተሰማች አንዲት የዘውዲቱን ድምፅ ያቀብሉናል። ንጉሥ የተሰኘውን ማዕረግ በመያዝ የመጨረሻው ሰው የሆኑት የጎንደሩ ወልደ ጎርጊስ ከዓመት በፊት መሞታቸው ያበረታታቸው አልጋ ወራሽ ተፈሪ፣ የንግሥና ስማቸውን እንዲቀበሉላቸው የቅርብ ሰዎቻቸውን ወደ ዘውዲቱ ላኩ። ይህን የሰሙት ዘውዲቱ፣ “ስለምን እንዲኽ ይጣደፋል? ከዚህ በኋላ ልጅ አልወልድ፤ ታምሚያለኹ፤ ፈጠነም ዘገየም ወራሼ እርሱ ነው” ሲሉ ለተላኩት እንደመለሱላቸው አስፋ ወሰን ይነግሩናል።

ነጉሠ ነገሥት ነኝ ባሉ ማግስትም፣ እንዴት ንጉሥ ሳይኖር ይኽ ይኖራል በሚል ላጉረመረሙት የሸዋው ፖለቲካ ባለከባድ ሚዛን ሰዎች፣ ልዑል ራስ የሚል ከዚህ ቀደም ያልነበረ ማዕረግ ፈጥረው ሸዋን ሊያረጋጉት ሞከረዋል ሲሉም፣ ራሳቸው ልዑል ራስ አስፋ ወሰን፣ የተፈሪን ከነባሩ የሥልጣነ-ፖለቲካ መዋቅር አፈንጋጭነት ይጠቅሱልናል። 

በዚኽም በዚያም ያሉትን፣ የወቅቱን ፖለቲካዊ ባህል የሰጣቸውን ተረታ ተረታዊ እምነትንም፣ የምኒልክ የጦር ሚኒስትር የነበሩትን የአንጋፋውን አዝማች አባ መላን የደነደነ ትከሻንም ተደግፈው፣ የሰለሞን ሥርወ-መንግሥት 225ኛው ንጉሠ ነገሥትነት ሆነው በ38 ዓመታቸው ዘውዱን ጫኑ። ሌላይኛውን የአድዋ ጀግና ባልቻ አባ ሳፎን በብረትም፣ በሴራ ብልጫም አልፈው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ታንክ ያየችበትን ዘመቻ ያደረጉበትን የደጃዝማች አባ ውቃው ብሩን ትግትግ ተሻግረው መሄዳቸውን ያዩት ኅብተ ጊዮርጊስ ዲነገዴ፣ “ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ አቃተን” ማለታቸው፣ የተፈሪን የንግሥና ጉዞ መደምደሚያ ይጠቀልልናል። 

አዋራጁ ስደት

      ለብዙ የኢትዮጵያ አጥኚዎች፣ የሁለተኛው የጣሊያን ወረራ መከሰት፣ በዋናነት ገዢው መደብ በአድዋው ድል ራሱን በዞረ ድምር ውስጥ ማግኘቱ መሆኑን አበክረው ይከራከራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከላይ አሳጥረን እንዳየነው ያለው፣ ማን ወደ መንበሩ ይውጣ የሚለው የመኳንንቱ እሰጥ-አገባ በሩን ለወረራ ወለል አድርጎ መክፈቱ እንደሆነም ይነሳል።

በአልጋ ወራሽነታቸው የጀመሩትን የአውሮፓ ጉዞ በርትተው የሄዱበት ንጉሠ ነገሥት አፄ ኅይለ ሥላሴ፣ ወደ ጣሊያንም ተጉዘው ሞሶሎኒን እንደጎበኙ የሚጠቅሱልን የአንደኛው መፀሐፍ ፀሐፊ አስፋ ወሰን፣ አሰብን እንዲሰጣቸው ሞሶሎኒን ቢጠይቁትም፣ ፋሺስቱ እጁን አወናጭፎ መሄዱን ይጠቀሳሉ።

ወረራውም አይቀሬ እየሆነ ሲመጣ፣ አፄው አንዲት ብዙም ያልተስተዋለች ጥረት ማድረጋቸውን የሚያስታውሱን ሃጋይ ኤርሊክ በበኩላቸው፣ ጃንሆይ ቢችሉ የዙሪያ ገባውን የቀንዱን ሕዝብ ከስራቸው ለማሰለፍ ሞከረው እንደነበር ይነግሩናል። እንደጠቀስነው እስከ ጥቂት ዓመታት ድረስ ለታሪክ አጥኚዎች አልደርስ ያሉትን የአውሮፓ አገራት የወቅቱ ዲፕሎማቶችን የደብዳቤ ልውውጦች ማግኘት የቻሉት ፕሮፌሰር ኤርሊክ፣ “እኔ የሁሉም ጥቁር ንጉሥ ነኝ፤ ሁሉም ጥቁሮች የእኔ ታዛዦች ናቸው፤ የኢትዮጵያ ጥቁሮች ብቻ አይደሉም ከእኔ ጎን መቆም ያለባቸው፤ በነጮች ጭቆና ስር በእንግሊዝ ሶማሌ ላንድ፣ በኬኒያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ በጣሊያን ሶማሊያ የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ጭምር እንጂ” ሲሉ፣ ወደ ምሥራቋ ኢትዮጵያ ጎራ ብለው መናገራቸውን ይጠቅሳሉ።

ይሄ ንግግራቸው፣ እስከ ዛሬም በተለይ በኦሮሞ ብሄረተኞች ዘንድ ምኒልክ፣ “እኔ ኒግሮ አይደለሁም፤ ካውክሲያን እንጂ” ማለታቸው የጥቁር ጨቋኝነታቸውን ይነግራል ለሚለው እንካ ሰላንቲያ ማጣቀሻ አፍራሽ መነሾ ሳይሰጠን አይቀርም።

“የተፈሪን ሱሪ ሰፊ አሳጥሮበት፣ ከማይጨው ሲመለስ ጉልበቱ ታየበት” በሚል በዋለልኝ መኮንን የተገለፀውን ከባዱን ሽንፈት ተከትሎ አፄው ስደት ወጡ። አስቀድሞ ስለ ስደታቸው ወሳኔ፣ አፄው ባይሰሙም ድምፅ እንዲሰጡ ኢዮበልዮ ቤተ መንግሥት ከተጠሩት የዘመኑ ሹማምንቶች መካከል አፈንጋጭ መንፈስ የነበራቸው ታከለ ወልደ ሃዋሪያት፣ የለም እንደ ቴዎድሮስ ትሆናለኽ እንጂ አትሰደድም ሲሉ የመዘዙባቸውን ፒስትል ከቁብ ያልቆጠሩት ኅይለ ሥላሴ፣ ጉዞ ሲጀምሩም አትሄድም በሚል ከቀድሞ ወዳጃቸው በጅሮንድ ተክለሃዋሪያት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጣቸውን ኹለቱም ፀሐፍት ያስታውሱናል።

ኋላ ጥቁሩ ኢየሱስ ብሎ ሊጠራቸው አንደበቱን ያልያዘው ማርክስ ጋርቬይ፣ ስደታቸውን ተከትሎ “ታላቁ ፈሪ” የሚለውን ስድቡን ጭምር አልፈው ራሳቸውን የለንደኗ ብርዳም ከተማ ባዝ ውስጥ ያገኙት ንጉሠ ነገሥቱ፣ ምንም እንኳን የሕይወት ታሪካቸውን እየተረኩ ኹለት ቅፅ መፀሐፍት ማፃፍ ቢችሉም፣ ባልተሰማ ደረጃ በከባድ ችግር ውስጥም እንዳለፉ በሁኔታው ላይ ቀረብ ያለ መረጃ የነበራቸው አስፋ ወሰን ጥቂት መረጃዎች ይሰጡናል።

በተለይም፣ “በአማርኛ ብቻ ነው በአዕምሮዬ ያለውን ከልቤ እና በሙሉ ኅይሌ መናገር የምችለው” ያሉበትን የጄኔቫውን ተጠቃሽ ንግግራቸውን ባደረጉ ማግስት፣ የስደቱ ሕይወት እጅጉን መራር እንደነበረ አንድ ማሳያቸውን ፀሐፊው ይጠቅሳሉ። ዶክተር አስፋ ወሰን እንደሚሉት፣ ለተጠለሉበት ቤት ማሞቂያ ከሰል መግዣ ማጣትን የጨመረው እጦታቸው፣ የባለቤታቸውን ጌጣጌጥ እና ከብር የተሰራውን የንግሥናቸውን የመመገቢያ ዕቃ እስከመሸጥ አድርሷቸው እንደነበር ይነግሩናል።

በሌላ ጫፍ ደግሞ ሃጋይ ኤርሊክ፣ እንግሊዝን ለቀው ሲወጡ በባንክ ደብተራቸው ላይ የተገኘው 1500 ፓውንድ ብቻ ነበር ሲሉ፣ በተለይም በደርግ በኩል ሲነገርም፣ ሲፃፍም የነበረውን፣ ጃንሆይ የሰፊውን ሕዝብ ሃብት ዘርፈው ባንክ አከማችተዋል ተረክ ያጣጥሉታል። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአሰላለፍ መቀያየርን ጨምሮ፣ በአገር ቤትም ይደረግ የነበረው የአርበኞቹ ፀረ-ፋሺስት ትግል ፍሬ አፍርቶ፣ ሚስተር ስሚዝ በሚል የብዕር ስም እንግሊዝን ለቅቀው የወጡት ተፈሪ፣ በ2000 ዓመታት ውስጥ ስደት የወጣ የመጀመሪያው ንጉሥ የሆኑበት ዘመን ተቋጨ። 

 ከትውልዱ ማን አስተዋለ?

እነሆ የ1953ቱ ታኅሣሥ ወር፣ እንደቀድሙትም፣ ኋላ እንደመጡትም ሊያልፍ አልመጣም ነበር። ለውርደትም፣ ለውግዘትም የዳረጋቸውን ስደት አገባድደው የመጡት አፄ ኅይለ ሥላሴ፣ ራስ አስፋ ወሰን እንደጠቀሱት፣ “ዘመዶችሽ አላሳልፍ አሉን” ሲሉ በኢያሱ ጉዳይ ቂም የቋጠሩት የወሎ ሰዎችን በመጥቀስ ለእቴጌዋ ፅፈው፣ መናገሻ ከተማቸው በደረሱ ማግስት፣ የሚሰቅሏቸው አርበኞች በዝተው ነበር።

ከእነዚህ አንዱ የሆነውን በላይ ዘለቀን ቆሞ ያሰቀለው ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እርሱም አፄው ላይ የክብር ዘቡን አፈ ሙዝ ለመደገን ተገደደ። ይህንን ሥዒረ-መንግሥት ከበድ ባለ ጭካኔ አዳፍነው ያለፉት ጃንሆይ፣ እንደመጡበት ሊሄዱ ቢደፍሩም፣ ተዉ ባይ ግን አላጡም ነበር።

  በንዋይ ልጆች መሰቀል ማግስት፣ የአገሪቷ መጪ ጊዜ ያሳሰባቸው ታላቁ ደራሲያችን ሃዲስ አለማየሁ፣ ሕገ-መንግስቱ ይሻሻል፣ የመናገር እና የመሰብሰብ መብቶች ይከበሩ መሰል ሥርዓታዊ ማሻሻያዎች ቢደረጉ ይሻላል ሲሉ ባለ 13 ገፅ ማስታወሻቸውን ለጃንሆይ አስገቡ፡፡ ነገሩን እንደ ድፍረት የቆጠሩት ንጉሠ ነገሥቱ፣ ደራሲውን አስጠርተው፣ “ለኢትዮጵያ ያደረግነውን ለማወቅ ልጅ ነህ፤ እኛን አታውቀንም” ሲሉ ታበዩ፡፡

እኒኽ ኹለት ፀሐፍትም፣ አፄውን ደፈር ብለው ለመናገር የከጀሉ እንደነበሩ፣ በተባሉት ላይ ያክሉልናል። ራስ አስፋ ወሰን በበኩላቸው፣ ከተጠቀሰው የሃዲስ ዓለማየሁ የብቻ ጥረት ማዶ፣ ከታኅሣሡ ግርግር አንድ ዓመት በኋላ፣ አምስት የሚሆኑ የወቅቱ ባለ ጥርብ ትከሻ የአፄው ሰዎች አንዳች ሙከራ ለማድረግ መጣራቸውን ይጠቅሳሉ። እነርሱም የፀሐፊው አባት ራስ ዓሥራተ ካሳ፣ ጄኔራል ዐቢይ አበበ(ኋላ ‘አውቀን እንታረም’ የምትል አነስተኛ መፀሐፍ ከአስመራ ወደ ላይኛው ቤተ መንግሥት መወርወራቸውን ልብ ይሏል)፣ ጄኔራል መርዕድ መንገሻ፣ ኮለኔል ታምራት ይገዙ እና ደጃዝማች ግርማቸው ተክለኅዋርያት ሲሆኑ፤ በጊዜው አጠራር ከአፄው ነጭ ለባሾች ሰወር ብለው ላንጋኖ መምከራቸውን ያስታውሳሉ።

ከዚያም፣ እንደ ፀሐፊው ገለፃ፣ “ለእርሶ ያለን ታማኝነት ጊዜው ሳይረፍድ ማሻሻያ ሃሳቦችን እንድንሰጥ ያስገድደናል” ያሉት እኒኽ የአገሪቷ ሁነኛ ሰዎች፣ “የአብዮት አደጋ እየናረ ነውና፣ ከሕገ-መንግሥት ማሻሻያ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ተጠያቂ እንዲሆን” እስከሚሉት ድረስ ያሉ ምክረ ሃሳቦችን ቢያቀርቡም፣ ጌታቸው ጆሮ እንደነፈጓቸው ይጠቅሳሉ። እኚኹ ፀሐፊ፣ አፄው እንኳን ባይታያቸው፣ እንዴት ሌሎቹ ደም ያረገዘውን ደመና መመልከት ተሳናቸው? በሚል በአለፍ ገደም ለሚነሳው መሰል ጥያቄ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ምንጫቸውን ተንተርሰው ሌላ ተጨማሪ ሁነትን ያቀብሉናል።

ጉምቱው ፀሓፊ ማሞ ውድነህ በግል አጫወቱኝ እንደሚሉት፣ ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ በንዋይ ወንድማማቾች ሥዒረ-መንግሥት ማግስት የወቅቱን የኤርትራ ገዢ ራስ አሥራተ ካሳን ለመጎብኝት በሄዱበት ወቅት፣ “ይኽች መሬት ስጋችንን መቼ ነው የምትቀበለው? ይገባናልስ?” የሚል ተስፋ መቁረጥም፣ የራስ ንቀትም የተቀላቀለበትን ጥያቄ ወርወር ሲያድርጉላቸው፤ “ለምን ይገባናል? በፍፁም መሬቲቷ የቀረውን ሙት ገላችንን መቀበል የለባትም” የሚለው የፈጠነ የራስ መልስ ነበር።

“የታኅሣሡ ግርግር ነገ እኛኑ ለማደን ተመልሶ ይመጣል” የሚለው የራስ አሥራተ ካሳ የጨዋታቸው ማሳረጊያ ግን፣ አስቀድሞ የተፃፈ ይመስላል። በእርግጥም፣ ከዚያች የአስመራ ጨዋታ በኋላ፣ ጄኔራሉ አፄውን ለመግደል ሞክረው ሲከሽፍባቸው፣ ራስም አይገባንም እንዳሉት ሆነና፣ የደርግ የጭካኔ ርሸና ሰለባ ሆኑ።

ለአፄው ከታኅሣሡ ግርግር ማግስት አንዳችም ማሻሻያ ላለማድረግ፣ ፕሮፌሰር ኤርሊክ የተፈሪን እርጅና ዋንኛው ምክንያት ለማድረግ፣ “በ79 ዓመታቸው ያያቸው አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ፣ በገመድ እንደሚቆጣጠሩት አሻንጉሊት መራመድ የጀመሩ፣ ድምፃቸው የማይሰማ እና ግራ የገባቸው ብቸኛ ሰው” ያለውን ጠቅሰው ሊሞግቱ ሲጥሩ፤ ራስ አስፋ ወሰን በሌላ ጎን፣ የአፄውን ለውጥ እምቢ ባይነት ከኹሉን ጠቅላይ አምባገነንት ጋር ሊስተሳስሩት ይጥራሉ። 

 “የመጨረሻውን ቃል ለጀግናው ተዉለት” ነውና፣ አስቀድሞ የተወሰነውን ፍርድ ለመስማት ችሎት የቆመው መንግስቱ ንዋይ፣ “አልተሸነፍኩም!” አለ፡፡ እውነት ነው፤ “ዋ ለእናንተና ለገዢያችሁ” ሲል፣ ሊመጣ ያለው የደም አበላ ቢታየውም ቅሉ፣ የይሁዳው አንበሳ ግን ለቀጣዮቹ አስራ ሦስት ዓመታት እያገሳ መንበሩ ላይ ሰንብቷል፡፡ ከዚያስ? በወንድማማቾቹ ስቅላት ማግስት፣ “ካለ ደም ስርየት የለም!” የሚል ርዕስ ያለው ወረቀት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ተበተነ፡፡ ከትውልዱ ያስተዋለ አልነበረምና፣ አብዮትም ተከተለ፡፡

   ቀ.ኅ.ሥ. ያሳርጉ

    

እኒኽን ኹለት መፀሐፍት ለማንበብ የሚሻ፣ በዚህ መልኩ በወፍ በርረ ያየናቸውን የአፄውን የንግሥና እጥፋቶች ጨምሮ፣ ጥቂትም ቢሆን ወደ ጃንሆይ ሳይሆን ወደ ሰውዬው ተፈሪ መመልከቻ ሽንቆሮች አያጣም። የዶክተር ኤርሊክ መፅሐፍ በዋናነት ሁለተኛ ምንጮች ላይ ሲንተራስ፤ የራስ አስፋ ወሰን በሌላ መልኩ፣ እጅጉን በጥቂቱም ቢሆን የግል ጭውውቶችን እና ትውስታዎችን መጥቀሱ የመነበቡን አስፈላጊነት ከፍ ያደርገዋል።

ከላይ ጠቀስ ጠቀስ ያደረግናቸውን ጨምሮ፣ “አይስ ክሬም ይጋብዙኝ ነበር” ያሏቸውን ንጉሥ፣ ኢትዮጵያዊው ማኪያቬያሊ ያሉበትን ጠበቅ ያለ ገለፃ፣ ኤርሊክም በሌላ መረጃ ይደግፉታል። በህንድ የትምሕርት ሥርዓት መሠረት አራተኛ ክፍልን አጠናቅቀዋል የሚሉን ሃጋይ ኤርሊክ፣ ኹለተኛ ቁንቋቸው እንደሆነ የሚጠቀስላቸውን ፈረንሳይኛ ጨምሮ እንግሊዘኛም መማራቸውን ሲያክሉልን፣ በእርግጥም ባቢሌ ቶሎ በ”To kill A Generation” መፀሐፉ፣ የማካቪዬሊን ‘ዘ ፕሪንስ’ በአማርኛ አስተርጉመው አንብበዋል መሰል ክሶችን ያጣፋል።

የሸበተ ፀጉራቸውን ሽው ለማድረግ ከአንድ የጀርመን ድርጅት ብቻ ስለሚገዙት ጥቁር ቀለም፣ የታኅሣሡ ግርግር ላይ የተሳተፈው ልጃቸው አስፋ ወሰን፣ “በፍቃዴ ነው” ማለቱን ማንበባችን፣ የሜዳ ቴኒስ ስለማዘወተራቸውም ሆነ የአሁን ዘመን ሕፃናት ተወዳጅ ምግብ የሆነውን ኮርን ፍሌክስ በዚያ ዘመን ጭምር መመገባቸውን የራስ አስፋ ወሰንን መፀሐፍ ባንገልጥ ምናልባትም አንሰማ ይሆን ይሆናል።

 በኤርሊክ ድርሳን፣ “የመጨረሻ ወሮቻቸውን መዝሙረ-ዳዊት ሲያነቡ ነበር” የተባሉትን ንጉሠ ነገሥት አፄ ኅይለ ሥላሴ፣ የመጨረሻው የሥርወ-መንግሥቱ ወራሽ፣ የሳባ እና የሰለሞን የመጨረሻው ትውልድ፣ አይነኬው የይሁዳ አንበሳን ከግማሽ ክፈለ-ዘመን በላይ ከሰነበቱበት መንበር ከነቀሉት አንዱን ያናገሩት ልዑል አስፋ ወሰን፣ ደርጉ የነገራቸውን ንዑስ መዝጊያ እናድርገው፤

 “የመጀመሪያውን በር ከፍተን ስንገባ ባዶ ክፍል አገኘን፤ የሚቀጥለውን በርም ስንከፍት አሁንም ክፍሉ ባዶ ነበር፤ እንዲኽ እያልን ዘውዱ ጋር እስክንደርስ ሄድን፤ በሌላ ሰው እስኪሞላ የሚጠብቅ ባዶ ቤት ነበር ያገኘነው።” 

የዛሬውን የወፍ በረር የመፀሐፍ ዳሰሳችንን፣ በሌላ በማንም ሳይሆን፣ ከሥልጣን የወረዱበትን ዐዋጅ፣ ዲሞትፈሩን ታጥቆ ፊታቸው ያነበበው የያኔው ጎልማሳ ደበላ ዲንሳ፣ አጭር ንግግሩን ሲጨርስ፣ የመለሱት የራሳቸው የተመዘገበ የመጨረሻ ንግግር ማሳረጊያ ይሁነን፤ ቀ.ኅ.ሥ. ያሳርጉ–

                   “….ለአገር የሚጠቅም ነገር ካለበት፣ የአገርን ጥቅም በሌላ ለመለወጥ አይቻልምና ያነበባችኹትን ሰምተናል፣ በዚኹ ማቆም ነው።