ዋዜማ- የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነ መረብ የዜና አውታር መስራች ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፤ የዓመቱ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማት ተመረጧል።
ተስፋለምን ለዓለም የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማት የመረጡት፣ ዓለማቀፍ የፕሬስ ኢንስቲትዩት እና ዓለማቀፍ ሚዲያ ሳፖርት የተሰኙ ሁለት ዓለማቀፍ ተቋማት ናቸው። ተስፋለም ያሸነፈው ዓለማቀፍ ሽልማት፣ ለመገናኛ ብዙኀን ነጻነት ወይም ላልተገደበ የዜና እና የመረጃ ፍሰት ሲሉ የግል ደኅንነታቸውን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ጥለው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለሚያደርጉ ጋዜጠኞች የሚሰጠውን ሽልማት ነው።
ሁለቱ ዓለማቀፍ ተቋማት ሐሙስ፣ መስከረም 29፣ 2018 ዓ፣ም በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ ተስፋለምን ለዚህ ዓለማቀፍ ሽልማት የመረጡት፣ “ለገለልተኛ ጋዜጠኝነት ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት” እውቅና በመስጠት እንደሆነ አስታውቀዋል።
ተስፋለም ከባለስልጣናት ለሚሰነዘርበት ቀጥተኛ የበቀል እርምጃ ዒላማ ሆኗል በማለት የጠቀሱት ሸላሚዎቹ ተቋማት፣ ጋዜጠኛው ከሥራው ጋር በተያያዘ የግል ሕይወቱን በተደጋጋሚ ለአደጋ አጋልጧል ብለዋል። ተስፋለም ለተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስር እንደተዳረገ እና “ከጊዜ ወደ ጊዜ ለነጻ መገናኛ ብዙኀን አስቸጋሪ በሆነ ምህዳር ውስጥ ለሕዝብ ለሚጠቅም የጋዜጠኝነት ቦታ ለመፍጠር ባለው ቁርጠኝነት በስደት ይኖርበት ከነበረበት አገር ከሰባት ዓመታት በፊት ወደ አገሩ ኢትዮጵያ መመለሱንም ተቋማቱ ጠቅሰዋል።
ተስፋለም፣ ለዚህ ታላቅ ዓለማቀፍ ሽልማት በመመረጡ ታላቅ ክብር እንደተሰማው መናገሩ እና የሽልማቱ ዓለማቀፍ መራጭ ኮሚቴም ለጥረቱ እውቅና በመስጠቱ ምስጋናውን ገልጧል።
ጋዜጠኛ ተስፋለም፣ ሽልማቱ ለእሱ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ እና በስደት ላይ ለሚገኙ ብርቱ ጋዜጠኞች ጭምር መሆኑንና በየዕለቱ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ለሚውሉ፣ ለሚታሰሩ፣ ማስፈራራት፣ ወከባ እና ዛቻ ለሚገጥማቸው፣ ለሚከሰሱ እና ጥቃት ለሚፈጸምባቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ድፍረት እንዲሁም ለሙያቸው ያላቸው ታማኝነት ምስክር እንደሚሆን ተናግሯል።
ተስፋለም የኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች የማይናወጥ ቁርጠኝነት እና ጥንካሬ በዚህ ሽልማት ቦታ ማግኘቱን በመግለጽም፣ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች የሚያከናውኑት ጠቃሚ ሥራ እና የሚፈታተኗቸው ተግዳሮቶች የበለጠ ትኩረት እንዲያገኙ ያደርጋል ብሏል። ለዚህ ዓለማቀፍ ሽልማት መመረጡ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረውን የጋዜጠኝነት ስራ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንዳነሳሳውም ገልጧል።
ተስፋለምን ለሽልማቱ በመረጠው ኮሚቴ ውስጥ፣ የፊንላንድ፣ የፓኪስታን፣ የሜክሲኮ እና የሌሎች አገራት ጋዜጠኞች በዳኝነት መሳተፋቸው ተገልጧል።
ተስፋለም እና ሌሎች ተሸላሚዎች የዘንድሮውን ሽልማት የሚቀበሉት፣ ስመ-ጥር ጋዜጠኞች፣ አርታዒያን እና የመገናኛ ብዙኃን ሥራ አስፈጻሚዎች ዓለማቀፍ ጥምረት የሆነው ዓለማቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት 75ኛ ዓመቱን በሚያከብርበትና ከጥቅምት 13 እስከ 15፤ 2018 ዓ፣ም በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪዬና በሚያካሂደው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው።
ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ የሽልማቱ አሸናፊ ሲሆን ተስፋለም ወልደየስ ሁለተኛው ነው። ከአሁን ቀደም ማለትም በ2009 ዓ፣ም ይህን ዓለማቀፍ ሽልማት የተቀበለው በወቅቱ እስር ላይ የነበረው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ብቻ ነው።
ተስፋለም ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ዓመት በላይ ለእስር የተዳረገው ከዞን-9 ጦማሪ ቡድን አባላት ጋር ተደርቦ በሚያዝያ 2006 ዓ፣ም ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዋና አዘጋጅ እያለ ደሞ በመስከረም 2014 ዓ፣ም እንዲሁም በነሐሴ 2017 ዓ፣ም ለቀናት ታስሯል።
ከተስፋለም ጋር ለእዚህ ዓመት የዓለም የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማት የሌሎች አገራት ስድስት ጋዜጠኞች እና አርታዒያን ተመርጠዋል። ለዘንድሮው ሽልማት ከተመረጡ ጋዜጠኞች መካከል፣ ሁለቱ በጋዜጠኝነት ስራቸው ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳጡ እና ሌሎቹ ሁለቱ ደሞ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጧል።
በሕይወት የሌሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች፣ በፍልስጤሟ ጋዛ እስራኤል በምትፈጽመው ጥቃት የተገደለችው ፍልስጤማዊቷ የፎቶ ጋዜጠኛ ማርያም አቡ ዳጋ እና በሩሲያ እስር ቤት ውስጥ ሕይወቷን ያጣችው ዩክሬናዊቷ ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ራሺና ናቸው።
እስር ላይ የሚገኙት ተሸላሚዎች ደሞ፣ ጆርጂያዊቷ ዚያ አማግሎቤሊ እና በሆንግ ኮንግ የጋዜጣ አሳታሚው ጂሚ ላይ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ የቀድሞው የዋሽንግተን ፖስት እና የቦስተን ግሎብ ጋዜጦች ስመ-ጥር አርታዒ ማርቲን ባሮን እና ፔሩቪያዊው ጉስታቮ ጎሪቲ እንደሆኑ ታውቋል። [ዋዜማ]