ሕልፈቱን ከሰዓታት በፊት የሰማነው ደበበ እሸቱ በኪነጥበብ ሙያው ካተረፈው አክብሮትና ዝና ባሻገር ለመብትና ነፃነቱ አበክሮ መታገልን የመረጠ አንድ ወቅትም ወደ ፖለቲካው ዘልቆ ገብቶ የበኩሉን የሞከረ ዜጋ ነበር። የደበበ ሕይወት ብዙ የሚገለጡ ምዕራፎች ያሉትና በፈተናና በስኬት የታጀበ እንደነበረ ከግለ ታሪኩ መገንዘብ ይቻላል። ዋዜማ ራዲዮ አንጋፋውን ደበበን እንዲህ ትዘክረዋለች መልካም ንባብ

አንጋፋ ተዋናይ ብቻ ሳይሆን የሀገራችን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እምብዛም በማይደፍሩት ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፤ በምርጫ 97 በቀስተ ደመና እና ቅንጅት አመራርነትና አስተባባሪነት ተሳትፏል፡- ደበበ እሸቱ፡፡

አንጋፋ የቴአትር አዘጋጅ፣ ስመጥር ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚ እና ደራሲ ጭምር ነው፡፡ የትወና ችሎታው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሕል ማዕከል ደምቆ መታየት የጀመረ ሲሆን፣ በሙያው አንቱታን ያተረፈው በተለያዩ ቴአትሮችና ድራማዎች ውጤታማነቱን አሳይቶና አስመስክሮ ነው፡፡

“ደበበ ከብዙዎቹ በፊት ችሎታውን አስመስክሮ ስመ ጥር የሆነው በሀገሩ መድረክ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ጭምር” እንደሆነ የምታስረዳው የረዥም ዘመን የመድረክ ባልደረባው አለምጸሐይ ወዳጆ “…አንጋፋው ከያኒና አርበኛ ደበበ እሸቱ በተለያዩ ዘርፎች ተሰጥአ ያደለችው ለመሆኑ፤ በድርሰቱ ውስጥ የተዋነዩት፣ በዝግጅቱ የተሳተፉት፣ በትወናው የረኩት፣ በመምሕርነቱ ያደጉት ሁሉ የሚመሰክሩት ነው” በማለት ከነዚህ መሐል እሷ ራሷ አንዷ መሆኗን ትጠቅሳለች፡፡

ደበበ እሸቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርቱን የተከታተለው አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ነው፡፡ ትወናን መሞመካከር የጀመረውም በዚሁ ትምሕርት ቤት ነበር፡፡ ስምንተኛ ክፍልን ሲያጠናቅቅ፣ በትምህርት ቤቱ በተዘጋጀ የመሰነባበቻ የቴአትር ፕሮግራም …ደበበ የሴት ገጸ ባህሪ ወክሎ ተወነ፡፡ በተፈሪ መኮንን እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ትምሕርቱን ከተከታተለ በኋላ አውሮፕላን ለመንዳት ባለው ፍቅር ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመግባት ፈተናውን አልፎ በደብረዘይት ዕጩ መኮንነት ስልጠና ጀምሮ ነበር፡፡

የአየር ኃይል ዲሲፒሊን እጅግ ከባድ ቢሆንበት ጊዜ ከግቢው ጠፍቶ ወጣ፡፡ ከመውጣቱ በፊት ግን በአየር ሃይል ውስጥ ቴአትር ለማዘጋጀትና ለማቅረብ እንደሚፈልግ ለዕጩ መኮንኖች የመዝናኛ ሃላፊ አስታውቆና ይኸው ተፈቅዶለት አንድ ቴአትር ከጓደኞቹ ጋር አዘጋጅቷል፡፡ 

ከአየር ኃይል በኋላ በፖስታ ቤት ተቀጥሮ የሠራ ሲሆን እሱንም ከአንድ ዓመት በኋላ አቋርጦ፣ በደብረ ብርሃን መምሕራን ማሰልጠኛ አስተማሪ ለመሆን የሚያበቃውን ትምሕርት መከታተል ቀጠለ፡፡ በማሰልጠኛው በመዝናኛ ክበብ ኃላፊነት ተመርጦ የፎቶግራፍ፣ የሥነ ጽሁፍ እና የቴአትር ክበብ በማዋቀር፣ አባላትን መልምሎ በርካታ ስራዎች አቅርቧል፡፡ በዚያ ወቅት ነው ደበበ ትኩረቱን ይበልጥ ወደ ቴአትር በማድረግ በርካታ የመዝናኛ ጭውውቶችና ለብቻው የሚያቀርባቸው ትርኢቶችን ራሱ በመጻፍና በመተወን ከመምህራን ማሰልጠኛ ት/ቤት ውጪ ለደብረብርሃን ነዋሪዎች ትርኢቱን ማሳየት የጀመረው፡፡ 

በ1953 ዓ.ም ደበበ ከመምሕራን ማሰልጠኛ ሊመረቅ አንድ ሳምንት ሲቀረው በአመጽ አስተባባሪነት ተፈርጆ ተመራቂ እንዳይሆን ታገደ፡፡ በታሕሳስ 1953 ዓ/ም የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት እንደግፋለን በማለት ደበበና ሌሎች ተማሪዎች በጠዋቱ የጸሎትና የሥነ ስርአት ፕሮግራም ላይ ላለመገኘት ወስነው አመጽ ማካሄዳቸው በማሰልጠኛው ኃላፊዎች ጥርስ ውስጥ አስገባቸው፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ደበበን ጨምሮ የአመጹ አስተባባሪ የተባሉ 10 ተማሪዎች የመጨረሻውን ዓመት ፈተና ወስደው ሊመረቁ ሳምንት ሲቀራቸው፣ ከግቢው በፖሊሶች ተይዘው ወደተለያየ ቦታ ተወሰዱ፡፡ ደበበም ኢሉባቦር ተመደበ፡፡ የኢሉባቦር ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ ጎሬ ደርሶ በቁም እስር ሆኖ ጠዋት፤ ቀን፤ ማታ እንዲፈርም… ሆኖም በአስተማሪነት አገልግሎት እንዲሰጥ ተብሎ በወር 70 ብር እየተከፈለው ለጥቂት ወራት ቆይቶ ወደ መቱ ተዛወረ፡፡ 

ደበበ ከኢሉባቦር ከተመለሰ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው የቴአትር ባለሙያዎች ማሰልጠኛ “ቤተ ኪነጥበባት ወ ቴአትር” ገብቶ ስልጠና ጀመረ፡፡ ለሁለት ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ግን ለሙከራ የተመደበው ገንዘብ በማለቁ ሳይመረቁ በመቋረጡ በግል አፈላልጎ በተገኘው የውጪ ትምህርት ዕድል ከጓደኛው ከወጋየሁ ንጋቱ ጋር ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሀንጋሪ ቡዳፔስት በማምራት የቴአትር ጥበብን ተምሮ ተመለሰ፡፡

ከቡዳፔስት መልስ ቀጥሮ የሚያሰራ አካል በመጥፋቱ ደበበና ወጋየሁ በግላቸው በተለያየ ቦታ በመዘዋወር ትርኢት ያቀርቡ ጀመር፡፡ ከዚያ በፊት በሀገሪቱ “ፓንቶ ማይም” የተሰኘ ድምጽ አልባ ትርኢት ማቅረብ አይታወቅም ነበርና ሁለቱ ይሕንን በማቅረብ ፈር ቀዳጅ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም ተውኔቶችን በማቅረብ በወቅቱ ተወዳጅነትና ዝና አትርፈዋል፡፡ በኋላም ደበበ ዜና ማንበብና የመዝናኛ ሙዚቃዎችን አቅራቢ ሆኗል፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከዙፋናቸው ሲወርዱ በቀዳሚነት ዜናውን የቀረጸውና ያቀረበው ደበበ እሸቱ እንደነበር ታሪክ ያስታውሰዋል፡፡

ደበበ እሸቱ በቴአትር አዘጋጅነት ችሎታው የደራሲ መንግስቱ ለማን “ጠያቂ”፣ የተስፋዬ ገሰሰን “ተሐድሶ”፣ የአያልነህ ሙላቱን “ሻጥር በየፈርጁ”፣ የነጋሽ ገብረማርያምን “የአዛውንቶች ክበብ”፣ የዊሊያም ሼክስፒርን (የመስፍን አለማየሁ ትርጉም) “ሊር ነጋሲ” (በኋላም “ንጉሥ ሊር”) ከሽኖ አቅርቧል፡፡ በተዋናይነትና ተርጓሚነት ከተሳተፈባቸው በርካታ የመድረክ ሥራዎቹ ውስጥ ያላቻ ጋብቻ፣ ሮሚዎና ዡልየት፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ የበጋ ሌሊት ራዕይ፣ አንድ ዓመት ከአንድ ቀን፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ በቀይካባ ስውር ደባ፣ ተሓድሶ፣ ኪንግ ሊር፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የወፍ ጎጆ፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ ናትናኤል ጠቢቡ፣ ድብልቅልቅ፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ጠያቂ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ (በእንግሊዝኛ)፣ አዳ ኦክ አራክል (በእንግሊዝኛ)፣ ኦቴሎ (በእንግሊዝኛ) ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ኃላፊ፣ የራሥ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በሃገር ፍቅር ቴአትር የኪነ ጥበብ አገልግሎት ኃላፊነት አገልግሏል፡፡

በዓለም አቀፍ የሲኒማ ጥበብ ትወና በብዛት ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ቀደምት የሆነው ደበበ ከሪቻርድ ራውንድትሪና ከሠር ፍራንክ ፊንሊ፣ ከቴሬንስ ስታምፕ፣ ከጃን ሞንሮና ከሂዩ ግሪፍዝ፣ ከሶፊያ ሎሬን ጋር የተወነባቸው ፊልሞች “ሻፍት ኢን አፍሪካ”፣ “ዘ አፍሪካን ስፓይ”፣ ”ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር”፣ “ኤ ሲዝን ኢን ሔል”፣ “ዜልዳ”፣ “ዘ ግሬቭ ዲገር”፣ “ዘ ግራንድ ሪቤሊየን”፣ “ጉማ” ናቸው፡፡

ደበበ ከመድረክና ፊልም ስራዎቹ ባሻገር ተማሪዎችም አሰልጥኗል፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በብሔራዊ ቴአትር የተዋንያን ስልጠና ማዕከል ሲያቋቁሙ ከመምሕራኑ አንዱ እሱ ነበር፤ ለተማሪዎቹም መማሪያ ይሆን ዘንድ የተረጎመው የስታንስላቭስኪ “የተዋናይ ሀሁ” መጽሐፍ ለበርካታዎች ተዋንያን የሙያቸው ፊደል መቁጠሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከትርጉም ሥራዎቹ የሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “የደም እንባ” መጽሐፍ፣ ከተውኔት “ድብልቅልቅ እና “ያልታመመው በሽተኛ”ን ማውሳት ይቻላል፡፡ ከሬዲዮ ጋዜጠኛነቱ ባሻገር በ1960ዎቹ አጋማሽ የቁም ነገር መጽሔት ዋና አዘጋጅም ሆኖ ሠርቷል፡፡ ከእስር ቤት መልስ ከምርጫ 97 አንስቶ እስከ ቃሊቲ ወሕኒ ያለውን ማስታወሻ ያካተተበት “የእምነቴ ፈተና” የተሰኘ መጽሐፉንም ለንባብ አብቅቷል፡፡ 

ደበበ በራሱ ማመልከቻ የጡረታ መብቱ ተከብሮለት ከቴአትር ቤት ቋሚ ሠራተኛነት ራሱን እስካገለለበት ጊዜ ድረስ ዕድሜ ዘመኑን ከቴአትር ሙያ አልወጣም ነበር፡፡ ጡረታ ለመውጣት ያስገደደው ነጻነቱን የማሳጣት የመብት ረገጣ ድርጊቶች፣ ከሌሎች መጥፎ አጋጣሚዎች ጋሮ ተደማምረው የኋላ ኋላ የራሱን ነጻነት እንዲያስከብር ቀጥሎም ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ እንዲገባ ሠበብ ሆነውታል፡፡

በ1990 ዓ.ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በንግድ ምክር ቤት አስተባባሪነት የእርዳታ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ሲካሄድ ፕሮግራሙን ደበበ ነበር የሚመራው፡፡ በወቅቱ ከሁለት ቦታ ደሞዝ እንደሚበላ ተደርጎ በቀረበበት ሪፖርት የተነሳ የሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት ሥራ አስኪያጅ ከነበረው ሠው ጋር በፈጠረው አለመግባባት ደበበ በፈቃዱ በጡረታ ለመሠናበት አመልክቶ ወጣ፡፡ 

…ከዚያ በኋላ ደበበ ለጦርነቱ ዕርዳታ የሚያሰባስብ የአርቲስቶች ቡድን አዋቀረ፡፡ ብዙ ከተለፋና ከተደከመ… በርካታ ገንዘብም ካሰባሰቡ በኋላ… በሜጋ ማዕከል በተጠራ ድንገቴ ስብሰባ እነ ደበበ ሥራቸውን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ታዘዙ፡፡ ሥራቸውን ተነጥቀው ለአዲስ አበባ መስተዳድር አስረክብ የተባለው ደበበ ከጓደኛው ጋር በመሆን ስላዋቀረው “የአርቲስቶች ገንዘብ አሰባሳቢ ቡድን” ለማስረዳት ቢጥሩ የሚሰማቸው ባለማግኘቱ ትዕዛዙን አሻፈረኝ ብለው ሳይቀበሉት ወጡ፡፡ ደበበ ቁጭት አደረበት፡፡  

ነጻነቱን ፍለጋ እንዲያማትር የገፋፋው ሌላኛው ምክንያት ከሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት ጋር የተያያዘ ፕሮጀክት ነበር፡፡ 

አንድ የጃፓን ድርጅት በነጻ የሃገር ፍቅር ቴአትር ቤትን በባለ ሶስት ፎቅ ሕንጻ የመገንባት ሀሳብ ይዞ ይመጣል፤ ምድር ቤቱ ለሱቅ፣ ላውንደሪ፣ ጸጉር ቤትና መሠል አገልግሎት፤ ሁለተኛው ፎቅ ምግብ ቤትና የቤት ውስጥ ጨዋታ (እንደ ከረንቡላ፣ ፑል፣ ጠረጴዛ ኳስ…)፤ ሶስተኛው ፎቅ ሁለት አዳራሽ (አንደኛው ከ800 – 1000፣ ሁለተኛው ከ300 – 500 ሰዎች የሚይዝ) እንዲሆን ተደርጎ ለመስራት የሚያስችለው ንድፍ ለደበበ ይነገረውና፣ እሱ በለገሰው ምክር በመመራት የጃፓኑ ኩባንያ ዕቅዱን ለቴአትር ቤቱ ያሳውቃል፡፡ ሆኖም ለዥም ጊዜ ምላሽ ሳያገኙ በመቅረታቸው እንደገና ጉዳዩን ለደበበ ያስታውሳሉ፡፡ እሱም አመራሩን ጠይቆ የሚሰጠውን ምላሽ እንደሚነግራቸው ያሳውቃል፡፡ የሀገር ፍቅር ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኃላፊ ግን ይሕ ጉዳይ በተደጋጋሚ የሚነሳው ከደበበ በመሆኑ ብቻ  የረባ ምላሽ ለመስጠት ባለመፍቀዳቸው ፕሮጀክቱ ወደ ሌላ ሀገር እንዲዛወር መደረጉ ደበበን ክፉኛ አበሳጨው፡፡

የጃፓኑን ፕሮጀክት እንዲቋረጥ ያደረገው ሥራ አስኪያጅ የብአዴን ዕጩ አባል፣ የሜጋ ማዕከሉን ትዕዝዝ ያስተላለፉት ደግሞ የሕወሐት ሹም መሆናቸውን የተረዳው ደበበ “ጥላ ያጣሁትና የተጎዳሁት ነጻ ስለሆንኩ ነው” ብሎ እንዲያምን፣ ወደ ፓርቲ ፖለቲካ እንዲገባ ከገፋፉት በርካታ በደሎችና ሠበቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

“…ገዢው ፓርቲ ሲናገረው ያጨበጨብንለት ጉዳይ በሌሎች ሲነገር የሚያሸማቅቀን፣ አካባቢያችንን በጥርጣሬ ከማየት በፊት ወደመጣንበት መመለስ የምንፈራው ፈሪ ስላደረጉን ብቻ ነው” የሚል እምነት ያሳደረው ደበበ “…የፈራ ሕብረተሰብ ከፍርሃቱ እንዲላቀቅ ካላደረግን ለውጥ ማምጣት አንችልም፤ ይሕን ለማድረግ ደግሞ እኔ ቀድሜ ፍርሀቴን አራግፌ መጣል አለብኝ” የሚል ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ በ1997 ቀስተ ደመና የተሰኘ ፓርቲ መመስረቱን… ዛሬ በሕይወት የሌሉት ጓደኛው ዶክተር ሽመልስ ተክለጻድቅ ሲነግሩት ወዲያው በአባልነት ተመዝግቦ መሳተፍ ጀመረ፡፡ በአገዛዙ ለ20 ወራት ታስሮ ከመለቀቁ አስቀድሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነትን ተረክቦ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

አንዳርጋቸው ጽጌ ደበበ በቅንጅት ውስጥ የነበረውን ሚና እና አስተዋጽኦ በተመለከተ ባሠፈረው ማስታወሻ እንዲህ ጽፏል፡

“…በምርጫ 97 ወቅት በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ የመንግሥት ጋዜጣ፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ በእጁ ስለነበረ 24 ሠዓት ሙሉ የፓርቲውን ፕሮፓጋንዳ ሲነፋበት፣ ተቃዋሚዎችን ሲያጥላላበት፣ ሲከስስበትና ሲያወግዝበት ቢውል ተቆጣጣሪ አልነበረውም፤ ደበበ ደግሞ በቀን ውስጥ በገዢው ፓርቲ መልካም ፈቃድ ተቆንጥራ የምትሰጠውን የደቂቃዎች የአየር ጊዜ አብቃቅቶ፣ የገዢውን ፓርቲ ጥቃት መክቶ የቅንጅትን መልዕክት ማስተላለፍ ነበረበት፡፡ ትግሉ የጎልያድና የዳዊት ዓይነት ነበር፤ ደበበ እንደ ዳዊት ጎልያድን ዘርሮታል፡፡ የአርቲስት ሙያተኛነቱ የሰጠውን የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለሠዓታት የሚካሄደውን የገዢውን ፓርቲ የቸከ ፕሮፓጋንዳ ዶግ አመድ አድርጎታል፤ ለምርጫ 97 ድል በደበበ ተጽፎ፣ በእሱ ተነብቦና ተቀናብሮ በሬዲዮና ቲቪ የተላለፈው የቅንጅት መልዕክት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡”

አንደኛው የመላው ጥቁር ሕዝቦች በዓል በአልጄሪያ፤ ሁለተኛው በናይጄሪያ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ለመካፈል በተጓዘችበት ወቅት የቡድኑ አባል የነበረው ደበበ አኩሪ ተግባር መፈጸሙን በወቅቱ አብረውት የተጓዙ ይመሰክራሉ፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1985 ዓ/ም በርሊን ላይ በተካሄደው የዓለም አቀፍ ቴአትር ኢኒስቲቲዩት (ITI) የኢትዮጵያ ሰብሳቢና የአፍሪካ አስተባባሪ ሆኖ ተመርጧል፡፡ በኢንተርናሽናል ቴአትር ኢኒስቲቲዩት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ በመገኘት፣ በአፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያው ፕሮፌሽናል ቴአትር ቤት የሃገር ፍቅር ቴአትር መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ 

በዚያው ዘመን በዚምባብዌ በተካሄደ ቴአትር ለልማትና ዕድገት ወርክሾፕ ላይ በዩኔስኮ ተወክሎ ተገኘ፡፡ ለብዙ ጊዜ ተሞክሮ ሲወድቅ ሲነሳ የነበረውን የአፍሪካ የመድረክ ባለሙያዎች ማሕበርን አስተባብሮ በማቋቋም የማሕበሩም መስራች ፕሬዚዳንት ሆኖ ለ12 ዓመታት መርቷል፡፡ በዩኔስኮ አማካይነት የዓለም የኮንቴምፖራሪ ቴአትር ኢንሳይክሎፒዲያ ሲዘጋጅ የኤዲቶሪያል ቦርድ አባል ሆኖ ሠርቷል፡፡  ደበበ በኪነ ጥበብብ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከውጪ ሀገራት የተለያዩ መሪዎች እጅ በርካታ ሽልማቶች ተበርክቶለታል፡፡ በአትላንታ ጆርጂያ ኖቬምበር 24 “የደበበ እሸቱ ቀን” ተብሎ እንዲሰየም የከተማው ምክር ቤት ባጸደቀው መሰረት ዕለቱ በየዓመቱ ይከበራል፤ ከሀገር ውስጥም ኢትዮ ፊልምስ የሚያዘጋጀው “የጉማ አዋርድ” የዕድሜ ዘመን ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ደበበ ከትዳር አጋሩ አልማዝ ደጀኔ አራት ልጆች እንዲሁም አምስት የልጅ ልጆች አፍርተዋል፡፡ [ዋዜማ]