ለመሆኑ እንዴት አላችሁልኝ? እኔ ያው ደህና ነኝ፡፡ የመሐል አገር ሰው ምን ይሆናል ብላችሁ ነው! ምን ቢከፋ ጦሙን አያድር?
ትናንትና ሌሊት አዲሳባን በሕልሜ አየኋት፡፡ “የኔ የምላትን አዲሳባ ለምን በሕልሜ አየኋት?” ብዬ ተገረምኩ፡፡ ይህች አዚማም ከተማ እየኖርኩባትም ትናፍቀኛለች ማለት ነው?
የሸገር ሰማይ ደበሎ በለበሰ ሰነፍ የሰሜን ገበሬ ሲታረስ ነበር ያየሁት፡፡ ከሕልሜ ስነቃ ከአንድ አስፈሪ ጥያቄ ጋር ተላተምኩ፡፡ ‹‹ለመሆኑ አዲሳባ ከሠላሳ ዓመት በኋላ የኔ ናት?›› ይህ ጥያቄ ቀኑን ሙሉ እንደ ቢጫ ወባ ሲያንዘፈዝፈኝ ዋለ፡፡ ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማረዳችሁ ነገር ቢኖር የነገዋ አዲሳባ በፍጹም የኔ እንደማትሆን ነው፡፡
(ይህን ጦማር እዚህ ማዳማጥ ይቻላል)
##########
ከልደታ ተነስቼ የባቡሩን አስቀያሚ ድልድይ ተከትዬ ወደ ሞላማሩ ሳቀና ዳርማር ደረስኩ፡፡ በግራና ቀኝ የቅራቅንቦ ተራራ ተቆልሎ፣ የሰው አሸዋ ሲርመሰመስ ተመለከትኩ፡፡ ‹‹ምንድነው ደግሞ ይሄ?›› ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ‹‹አታውቅም እንዴ? አዲሱ ሱማሌ ተራ እኮ ነው›› ተባልኩ፡፡ ለካንስ ኦሪጅናሏ ሱማሌ ተራ ለልማት በፈረሰች ማግስት ፎርጅዷ ሱማሌ ተራ እዚህ በቅላለች፡፡ ከነስፖኪዮዎቿ፣ ከነክሪኮቿ፣ ከነፍሬቻዎቿ፣ እስከነ ሌቦቿ…ዳግማዊት ሱማሌ ተራን አገኘኋት፡፡
ያዲሳባ ሩቅ የለውም፡፡ ቢሆንም ሩቅ ተሳፈርኩ፡፡ አያት፡፡ ባቡሩ ራሱ በቃኝ ብሎ ወገቡን ይዞ የሚቆምበት ሰፈር ነው አያት፡፡ ባቡሩ ዉስጥ ጋዜጣ ማንበብና ዶሮ ይዞ መግባት ክልክል እንደሆነ ሳላውቅ የገዛሁት ጋዜጣ የፊት ገጽ ‹‹በአዲሱ ዓት ለመልሶ ማልማት 2900 ሄክታር መሬት ይዘጋጃል›› የሚል ዜና ይዟል፡፡ ግጥምጥሞሹ ገረመኝ፡፡ አያት ስደርስ ጋዜጣዬን አጣጥፌ ከባቡር ወርጄ በባጃጅ የአንድ ብር ከ50 መንገድ ሄድኩ፡፡ ለካንስ ከ‹‹አያት መንደር›› ማዶ ‹‹አራት ኪሎ›› የሚባል ሰፈር አለ፡፡ ወትሮም ‹‹አራት ኪሎ›› ሲባል ስሙ ክብድ ይለኛል፡፡ ዩኒቨርስቲ ሳይሆን አምባገነን መንግሥት ነው የሚመጣብኝ፡፡ ትምህርት ሚኒስትር ሳይሆን ዥንጉርጉር የቤተመንግሥት ልዩ ኮማንዶ ነው የሚታየኝ፡፡ ለማንኛውም አያትም ‹‹አራት ኪሎ›› የሚባል ሰፈር አለ፡፡ ጭቁን ይበዛበታል፡፡
ሰፈሩ ስሙን ያገኘው ከመሐል ሸገር ተፈናቃዮች ነው፡፡ ከአራት ኪሎ ተነሺዎች፡፡ በሸገር እምብርት ለዘመናት ለኖሩት ዘመናዮች 72 እና 94 ካሬ መሬት ተሸንሽኖ የተሰጠበት ሰፈር በመሆኑ ነው ዳግማዊ ‹‹4ኪሎ›› የተባለው፡፡ ደግሞም ሰፈሩ ነውጥ አይለየውም አሉኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› አልኩኝ፡፡ ከትውልድ ሰፈራቸው በመፈናቀላቸው የተቆጡ ቦዘኔዎች ቁጣቸውን የሚገልጹት መካከለኛ ገቢ ባለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ነው፤ ‹‹በጠራራ ፀሐይ ጭምር ማጅራት ይመታሉ›› አሉኝ፡፡ ተገረምኩ፡፡ ‹‹የመንግሥት ማጅራት ሲደነድንባቸው ለስላሳ የሕዝብ ማጅራት መምታት ጀመሩ፡፡››
ከዚህ ቀደም በጀሞ ኮንዶሚንየም ‹‹ራሳቸውን እንደመንግሥት የሚቆጥሩ ጎረምሶች ይበዙበታል›› ያለኝን ተከራይ ወዳጄን ‹‹ለምንድነው?›› ብዬው ‹‹የአራት ኪሎ ተነሺዎች ስለሚበዙበት ይሆናላ›› ብሎ አስገርሞኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሩ ለሳቅ የሚጋብዝ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በአንድ እድር ጥላ ስር ለ130 ዓመታት የተዋለደን የባሻ ወልዴ ችሎት ነዋሪ እንዲህ በሁለት የከተማዋ ጽንፍ መበታተን ጽንፈኛ ባይፈጥር ነበር የሚገርመው አልኩኝ፡፡ ዉስብስብ ማኅበራዊ ቀውሱን ሳስብ ደግሞ ከፋኝ፡፡ እኔም ለመፈናቀል ተራዬን የምጠብቅ የሞት ፍርደኛ እንደሆንኩ ተሰማኝ፡፡
እዚያው አያት ነኝ፡፡ እየተገነባ ያለው ‹‹40-60›› ኮንዶሚንየሙ ጋር ሳይደረስ ለመቄዶንያ የተሰጠ ሰፊ መሬት ታጥሮ ይታያል፡፡ ከመቄዶኒያ ጎን ደግሞ ‹‹ቦሌና አካባቢዋን እየናጠ ያለው ‹‹ዩጎ ቸርች›› ይታያል፡፡ የሚቻለውን መሬት ያህል በኤጋ ቆርቆሮ አጥሮ ይዟል፡፡ ወደፊት የሚገነባውን የ‹‹ኢየሱስ ቤት›› ምስልም አናቱ ላይ በጉልህ ሰቅሎት ይታያል፡፡
‹‹ዩጎ ቸርች›› ጋር ሳይደረስ በስተቀኝ ‹‹አዲስ መንደር ሪል ስቴት›› አለ፡፡ የድሮው ፕሮፌሰር፣ የአሁኑ ሽምቅ ተዋጊ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የመሠረተው ሪልስቴት ነው፡፡ የሚያምር አረንጓዴ ግቢ ነው፡፡ እርሱ በረሃ ለበረሃ ሲንከራተት ሰዎቹ ዘናጭ ኑሮ ጀምረውበታል፡፡ ከርሱ በቅርብ ርቀት ያለው ገላጣ ሜዳ ግን እንደጉድ ተሸንሽኗል፡፡ የመሬት እርድ ተካሄዶበታል ማለት ይቀላል፡፡ በስፍራው የበሬ ግንባር የሚያካክሉ መሬቶች በዛጉ ቆርቆሮዎች ታጥረው ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ምን የሚባል ‹‹ሰፈራ›› ነው አልኩኝ፡፡ ‹‹አታውቀውም እንዴ? አዲሱ ቄራ ነው የሚባለው›› አሉኝ፡፡
‹‹ቆይ ግን! ስንት ቄራ ነው እዚች ከተማ ዉስጥ ያለው?›› ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ሸራተን አካባቢ አሮጌው ቄራ አለ፡፡ ከቡልጋሪያ ዝቅ ብሎ ዋናው ቄራ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ምን የሚሉት ቄራ ነው፡፡ እንደቅድሙ ተመሳሳይ መልስ አገኘሁ፡፡ ቦታው ለቡልጋሪያ-ቄራ የልማት ተነሺዎች የተሰጠ ስለሆነ ነው ‹‹ቄራ›› የተባለው ተባልኩ፡፡ የከብት እርድ የማይካሄድባቸው ሁለት ቄራዎች በከተማዋ እንዳሉ የተገለጠልኝ ይሄኔ ነው፡፡ ግዙፍ የተሳለ ካራ ይዞ ከተማዋን ለሁለት እየበለተ ለሀብታምና ለድሀ በአድሎ የሚያከፋፍል አራጅ ከንቲባ እንዳለ የተገለጠልኝም ይሄኔ ነው፡፡
የወደፊቷ አዲሳባ ሁለት ካዛንቺሶች፣ ሁለት ጎላ ሚካኤሎች፣ ብዙ ልደታዎች፣ ሁለት አሜሪካን ጊቢዎች፣ ሁለት ሱማሌ ተራዎች፣ ሁለት አብነቶች፣ ብዙ ባምቢሶች፣ ብዙ ቀበናዎች፣ ብዙ 22ቶች እንደሚኖሯት ገባኝ፡፡ ስለራሴ አሰብኩ፡፡ ስለራሴ ሰጋሁ፡፡ ተለጥጣ ተለጥጣ የኦሮሚያ ድንበሮችን እየነካካች አመጽ የምትቀሰቅሰው የዛሬዋ አዲሳባ በእርግጥ ነገ ለኔ የሚሆን ጥግ ይኖራታል?
###
ስገምት የዛሬ 10 ዓመት የልጅነት ልምሻ ከአፍሪካ ሙሉ በሙሉ ይጠፋ ይመስለኛል፡፡ ስገምት…የዛሬ 30 ዓመት አዲሳባ ሙሉ በሙሉ ከድሀ ነዋሪዎቿ ነጻ የምትሆን ይመስለኛል፡፡ ያዲስአበቤ ድሆች ሀብታም ሆነው አይደለም የሚጠፉት፡፡ እየተገፉ ነው የሚጠፉት፡፡ እራፊ መሬታቸውን አቅም ላለው እየሸጡ፣ አንሸጥም ካሉም በመልሶ ማልማት እየተደለሉ፣ አንደለልም ካሉም ‹‹የልማት ፀር የሆኑ አንዳንድ ዝቅተኛ ነውጠኞች›› እየተባሉ ሸገርን ይሰናበቷታል፡፡
በዚች ምድር ላይ የማይሸጥ ቁስ የለም፡፡ በአዲስ አበባ ዉስጥ የማትሸጥ ስንዝር መሬት አትኖርም፡፡ በየወሩ በባትሪ እየተፈለጉ ኪስ ቦታዎች በሊዝ ይቸበቸባሉ፡፡ ክፍለከተሞች የሚሸለሙት በሥራ አፈጻጸማቸው አይደለም፡፡ በልማት ስም ባፈናቀሉት የሕዝብ ብዛት እንጂ፡፡ እያንዳንዱ የክፍለከተማ ‹‹የከተማ ማደስ ቢሮ›› ሹም ‹‹በቂ መሬት ለመልሶ ማልማት አላቀረብክም›› እየተባለ ይገመገማል፡፡ በሌላ ቋንቋ ‹‹ያፈናቀልካቸው የድሀ ቤተሰቦች ቁጥር አርኪ አይደለም›› እየተባለ ነው የሚተቸው፡፡
ሙሰኞች እሳት የላሱ የመሬት ‹‹ጉዳይ ገዳዮችን›› በየአቅጣጫው አሰማርተዋል፡፡ የዘረፉትን ገንዘብ ወደ ሕጋዊ መስመር ለመክተት የመሬትን ያህል ጥልቅ መቅበሪያ ጉድጓድ አያገኙም፡፡ ‹‹አይሸጥልም አይለወጥም›› የሚባለው መሬት እነርሱ ጋ ቆሎ ነው፡፡ እንደጉድ ይቸበቸባል፡፡ አንድ ሐብታም አንድ ደልቃቃ ካፌ ዉስጥ ከአንድ ደላላ ጋር አንድ ማክያቶ ፉት ባለ ቁጥር አንድ ካሬ የአዲሳባ መሬት ተሸጣለች ማለት ነው፡፡ የእስራኤል ከበርቴዎች የፍልስጤም ገበሬዎችን መሬት እያሳሳቁ ለቅመው በመጨረሻ ‹‹አገር›› በመሬት ዋጋ እንደገዙት ሁሉ የሸገር ድሆችም ለመጤ ቱጃሮች ደሳሳ ጎጇቸው ያረፈባትን መሬት ሽጠው መለመላቸውን ይቀራሉ፡፡
የዛሬ ሠላሳ ዓመት የቀበሌ መዋቅር ይኖር ይሆናል፡፡ የዛሬ ሠላሳ ዓመት የቀበሌ ቤት የሚባል ግን አይኖርም፡፡ የዛሬ ሠላሳ ዓመት ኮንዶሚንየም ይኖር ይሆናል፣ የዛሬ ሠላሳ ዓመት የኮንዶሚንየም እጣ የሚባል ግን አይኖርም፡፡ የዛሬ ሠላሳ ዓመት ሻል ያሉ የጋራ መኖርያ ቤቶች ይገነቡ ይሆናል፣ የዛሬ ሠላሳ ዓመት በነዚህ ሻል ባሉ የጋራ መኖርያ ቤቶች ዉስጥ ድሆች አይኖሩም፡፡ የዛሬ ሠላሳ ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ባለዲግሪዎች ይኖራል፣ የዛሬ ሠላሳ ዓመት በዲግሪና በቀበሌ መታወቂያ መሐል ከፍ ያለ የትርጉም ልዩነት አይኖርም፡፡ ከባለዲግሪዎች ይልቅ የእጅ ባለሞያዎች ከተማ ለመኖር የቀረቡ ይሆናሉ፡፡ ይህንን ስናገር በከፍተኛ የእርግጠኝነት ስሜት ነው፡፡
መሐል አዲሳባ የሞጃዎች ብቻ ትሆናለች፡፡ ጎስቋሎች ወደ መሐል ሸገር የሚዘልቁት ሞጃ ዘመዳቸውን ለመጠየቅ፣ አልያም በሞያቸው ሐብታም ለማገልገል ብቻ ይሆናል፡፡ የዛሬ ሠላሳ ዓመት ብዙ ሺ ሰዎች የጭርንቁስ መንደር ዉስጥ ለመስፈር ይገደዳሉ፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ በከተማ ዳርቻዎች ብቻ ጎጆ ይቀልሳሉ፡፡ በርግጥ በአፍሪካ ትልቁ የጎስቋሎች መንደር በአዲሳባ አጎራባች ከተሞች መፈጠሩ አይቀርም፡፡ እንደ ኬንያው የጭቁኖች ሰፈር ‹‹ኪቤራ›› በመሐል አዲሳባም አንድ ወይ ሁለት ጭርንቁስ መንደሮችም መኖራቸው አይቀርም፡፡ በዚያ መንደር ዉስጥም ሚሊዮን ጎስቋሎች አይጠፉም፡፡ እነዚህ ሚሊዮን ጎስቋሎች ግን እጅግ የሚቀናባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሆናሉ፡፡ መሐል ከተማ ለመኖር በመታደላቸው ብቻ፡፡
እርግጥ ነው እንደ ብራዚሉ የ‹‹ፋቬላ ኮረብታ›› ብዙ ሺ ድሆች ተቃቅፈው የሚኖሩባቸው ጎስቋላ ሰፈሮች በፊሊዶሮ፣ በአራብሳ፣ በቦሌ ለሚ፣ በቂሊንጦ፣ በአቃቂ፣ በማርያም፣ በሱሉልታ ሊፈጠሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ሆኖም መንደሮቹ ከፍ ባለ የግንብ አጥር ሸሸግ ተደርገው ነው የሚቀመጡት፡፡ ራስ ገዝ እስኪመስሉ ድረስ የመሐል ከተማ ሕግ አይገዛቸውም፡፡ ዋልጌነት ይነግስባቸዋል፡፡ ቱሪስት በሩቁ የሚጎበኛቸው መንደሮችም ይሆናሉ፡፡
እርግጥ ነው ጎስቋላ ሰፈሮች ሙሉ በሙሉ ከአዲሳባ አይወገዱም ይሆናል፡፡ ጎስቋሎች ግን ከአዲሳባ መደበኛ ነዋሪነት ይወገዳሉ፡፡ መታወቂያቸው 2ኛ ደረጃ ይሆናል፡፡ የዛሬ ሠላሳ ዓመት እንደከዚህ በፊቱ አዲሳባን አገሬ ብሎ፣ የሞጃ ጎረቤት ሆኖ፣ የእድር አባል ሆኖ፣ ከባለሀብት ጋር ተጋፍቶ በኩራት የሚኖር ጎስቋላ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በመሐል ሸገር አይኖርም፡፡ ይህንን ስናገር በከፍተኛ የእርግጠኝነት ስሜት ነው፡፡
በመሐል አዲሳባ ድሀና ሐብታም የአንድ እድር አባላት ሆነው አይቀጥሉም፡፡ በቀዳዳ የሸራ ድንኳን ዉስጥ ለቅሶ የሚቀመጥ ዜጋም አይኖርም፡፡ የወደፊት እድሮች ዊስኪ በሚሸጡ አዳራሾች ዉስጥ ስብሰባ ያካሄዳሉ፡፡ ድንኳን ጥሎ ሰርግ መደገስ በአዲሳባ አጎራባች ከተሞች እንጂ በመሐል ከተማ የሚታሰቡ አይሆንም፡፡ የእድር ኩባያ ምን እንደሚመስል የሚያውቅ የመሀል አዲሳባ ተወላጅ ጥቂት ይሆናል፡፡
የዛሬ ሠላሳ ዓመት በአዲሳባ ዙርያ ፈንጠርጠር ብለው በተሰሩ ደሳሳ ጎጆዎች ዉስጥ የሚያድሩ ሚሊዮን ጎስቋሎች ይኖራሉ፡፡ ትልልቅ አንበሳ አውቶቡሶች ይመደቡላቸዋል፡፡ እነዚህ ዜጎቸ የሚፈለጉት ወደ መሐል አዲሳባ እየገቡ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ ብቻ ይሆናል፡፡ ያኔ በመሐል አዲሳባ የቀን ሥራ ለመሥራት የሚታደሉት ሞያ ያላቸው ብቻ ይሆናሉ፡፡ ግንበኞች፣ ወዛደሮች፣ አናጢዎች፣ ቀለም ቀቢዎች፣ ወዘተ በጧት ተነስተው ረከስ ባለ ዋጋ አውቶቡስ ይሳፈራሉ፡፡ ከገላን፣ ከቡራዮ፣ከጫንጮ፣ ከቂሊንጦ፣ ከሱሉልታ…፡፡
ይህ ትንቢቴ ቅዠት አይደለም፡፡ እየሆነ ያለ ደረቅ ሐቅ እንጂ፡፡
የዛሬዋ ‹‹ሲኤምሲ›› አዲስ መንደር ናት፡፡ እድሜዋ አስር ዓመት ቢሆን ነው፡፡ ደርግ ለኤምባሲዎች ከገነባው የ‹‹ሲኤምሲ›› ግቢ ዉጭ በአካባቢው ያን ያህልም ነዋሪ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ብዙ ሺ ሞጃና ጥቂት ድሀ በጋራ ይኖርባታል፡፡ በ‹‹ሲኤምሲ›› ድሆች ቁጥራቸው ከእለት እለት እየተመናመነ ነው፡፡ ድሆቹ አዲሳባዊያን ‹‹ሲኤምሲ››ን እንደ ዘላቂ መንደራቸው አያዩዋትም፡፡ ነጋ ጠባ ሐብታሞች እየመጡ ቦታቸውን ሸጠው እንዲወጡ ያግባቧቸዋል፡፡ ብዙዎቹ በዋናው የ‹‹ሲኤምሲ›› መንገድ አካፋይ ሰፊ ደሴት ላይ በግ በመሸጥ ይተዳደራሉ፡፡ የሐብታም መኪና እልፍ ባለ ቁጥር ከሚሸጧቸው በጎች እኩል ድንግጥ ይላሉ፡፡
ሳርቤት ገብሬል 12 ቀበሌ ዘበናይ ቪላዎች ይበዛሉ፡፡ ኤምባሲዎችም እልፍ ናቸው፡፡ በዚያ ሰፈር ብዙ ድሀ ነዋሪ ነበር፡፡ አሁን ያሉት ግን በጣት ይቆጠራሉ፡፡ የት ሄዱ? አሁን በአካባቢው ድሀ ነዋሪዎች ቀርቶ ምጽዋት የሚለምኑ ድሆች እንኳን አይታዩም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ ቄንጠኛ ቤቶች የጋራ መግቢያ በር ተበጅቶላቸዋል፡፡ ምጽዋት ጠያቂው የግለሰቦች ቤት ደጃፍን ሊረግጥ አይችልም፡፡ የተናጥልና የጋራ (compound Guards) ጥበቃዎች እድሉን አይሰጡትም፡፡ ገና ከሰፈሩ መግቢያ ጀምሮ በጥበቃዎቸ የታጠረ መንደር ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት ተመሳሳይ መልክ ያላቸው ሰፈሮች ከቦሌ፣ ከጦር ኃይሎችና ከአትላስ አካባቢ ዉጭ እምብዛምም አልነበሩም፡፡ አሁን ግን ለቁጥር በዝተዋል፡፡ የዛሬ ሠላሳ ዓመት ደግሞ ብዙዎቹ የአዲሳባ መንደሮች የሳርቤትን መልክ ይይዛሉ፡፡ ድሆች በነዚህ ሰፈሮች ለመኖር ቀርቶ ለማቋረጥም የሚቻላቸው አይሆንም፡፡ ‹‹አቤት ወዴት ነው?›› እየተባሉ ቆሌያቸውን ይገፈፋሉ፡፡
የዛሬ 30 ዓመት ለማኞችና ጎዳና ተዳዳሪዎች መሐል ከተማ ዉስጥ መቆየታቸው አይቀርም፤ እነዚህ ወደፊት በሚፈጠሩ የሸገር ‹‹ፋቬላ ኮረብታዎች›› ወይም በባቡር ጣቢያ ፌርማታዎች ወይም በቀለበት መንገድ ድልድዮች ወይም በፍሳሽ ማስወገጃ ትቦዎች ስር መጠለያቸውን ያደርጋሉ፡፡ ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆነ ጎስቋላ የአዲሳባ ነዋሪ ግን ከዚህ በኋላ መሐል አዲሳባ ሊኖር አይቻለውም፡፡ ይህንን ስናገር በከፍተኛ የእርግጠኝነት መንፈስ ነው፡፡
እንዴት እርግጠኛ ሆንክ በሉኝ፡፡ እመልሳለሁ፡፡ ከዛንቺስን አይቼ፣ ልደታን ጎብኝቼ፣ አሜሪካን ግቢን ቃኝቼ፣ ‹‹4 ኪሎ›› ባሻ ወልዴ ችሎትን ታዝቤ፣ ሲኒማራስን ተመልክቼ፣ ከአብነት እስከ 7ኛ ባለው መንደር ዉስጥ ገብቼ፣ አፍሪካ ሕብረትን ዞሬ፣ ሸራተን ማስፋፊያን፣ ሜክሲኮ ደብረወርቅ ሕንጻ ጀርባን፣ የሸበሌ ጓሮን፣ ሰንጋተራን፣ ጎላ ሚካኤልን…ወዘተ ተሸሎክልኪ አይቼ-ገምቼ እላችኋለሁ፡፡ ዛሬ እነዚህ ሰፈሮች ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ነገን ለመተንበይ የሚያስችል ነው፡፡
###
የዛሬን አያድርገውና የአዲሳባ መሬት ቢዘሩበት የሚያበቅል ገራገር መሬት፣ አፈሩም ወርቅ ነበር፡፡ ኢህአዴግ መጣና አልማዝ እንቁ አደረገው፡፡ ሥርዓቱ ሰፊውን ከተሜ ወደ መካከለኛ ገቢ ከማስገባት ይልቅ ጥቂት ‹‹ድንገቴ›› ሐብታሞችን በብዛት ፈጠረ፡፡ ‹‹ድንገቴ›› ሀብታሞች ሳይታሰብ የመጣ ንዋያቸውን የሚከሰክሱት በመሬት ላይ ሆነ፡፡ በንጽሕና የበለፀጉትም ቢሀን ቆመው ማየጥ እንደሌለባቸው ተረዱ፡፡ መሬት በፍጹም የማያከስር ኮኬይን ሆነ፡፡ አሁን ለጊዜው የአንድ ካሬ ዋጋ 305 ሺሕ ብር ደርሷል፡፡
በ14ኛው ዙር የአዲሳባ የሊዝ ጨረታ አቶ ኃይለጊዮርጊስ ታምራት የተባሉ ባለሐብት ለቡ አካባቢ ኪስ ቦታ አዩ፡፡ 664 ካሬ ነው፡፡ ወደዱት፡፡ ለአንድ ካሬ 36ሺ ብር እከፍላለሁ አሉ፡፡ በ8ኛው ዙር ኤስኤንአይ የተባለ ኩባንያ ደሳለኝ ሆቴል ጋር 158 ካሬ የበሬ ግንባር የምታክል ቦታ አየ፡፡ ወደዳት፡፡ ለአንድ ካሬ 65ሺ ብር እከፍላለሁ አለ፡፡ በ12ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ ዘመናይ አልባሳት የተባለ ኩባንያ ኮልፌ 2120 ካሬ የሚሆን የተንጣለለ የእግር ኳስ ሜዳ አየ፣ ለካሬ 65ሺ ብር እከፍልበታለሁ አለ፤ አደረገው፡፡ እብደቱ ቀጥሏል፡፡
35 ዙርን ጨርሶ እንደ አዲስ አንድ ያለው ወርሃዊ የሊዝ እብደት ዛሬ 16ኛ ዙር ደርሷል፡፡ እንዲያውም ለሊዝ የሚቀርቡ ክፍት ቦታዎች እየተመናመኑ ነው፡፡ አሁን አሁን ‹‹የካ ክፍለከተማ›› አልፎ አልፎ ካልሆነ በሊዙ አይሳተፍም፡፡ ሩጫውን እየጨረሰ ነው፡፡ ያለውን መሬት በሊዝ ቸብችቦ ጨርሶታል፡፡ እጁ ላይ መሬት ስለሌለ በልማት ስም የሚያፈናቅለውን ሰፈር እየሰለለ ይገኛል፡፡ ‹‹አራዳ ክፍለከተማ›› ሊዝ ዉስጥ ተሳትፎው የተገደበ ነው፡፡ መሬት ከየት ያምጣ፡፡ አራት ኪሎ ቱሪስት አካባቢ ያሉትን መሬቶች ቸብችቦ ባዶ እጁን ተቀምጧል፡፡ ጉለሌ፣ ቂርቆስ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ለተሳትፎ ያህል ጥቂት መሬቶችን ካልሆነ እምብዛምም ክፍት መሬት የላቸውም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሊዝ መሬት በገፍ የሚያቀርቡት ሁለት ክፍለከተሞች ብቻ ናቸው፡፡ ቦሌና አቃቂ-ቃሊቲ፡፡
የባለጸጎች የመሬት ወረራ ገና ከጅምሩ በሊዝና በሪልስቴት የቁልምጫ ስም በዚህ በሸኖ በኩል ለገጣፉ፣ በዚያ በለቡ በኩል ፉሪ ደርሷል፡፡ መሐል ከተማ ጫጫታው የሚረብሻቸው ሞጃዎች፣ የወፍ ድምጽ መስማት የማራቸው ባለጸጎች፣…‹‹እንዲያውም መሐሉን አንፈልገውም›› ብለው ዳሩን መሐል እያደረጉት ነው፡፡
ፉሪ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወጣቶች ኳስ የሚያንከባልሉበት ገላጣ ሜዳ ነበር፡፡ ፉሪ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አንድ ቪላ ከአስር ሚሊዮን ብር በታች የማይሸጥበት የዲታዎች መንደር ሆኗል፡፡ ከሳምንት በፊት አንድ የ500 ካሬ ስፋት ያለው ባዶ መሬት 3 ሚሊዮን ተኩል ተገበያይቷል፡፡ ፉሪ ታሪክ ሆናለች፡፡ እንደ አቶ ዘነበ አይነት ባለጸጎች ግቢውን ሳይጨምር ቤቱ ብቻ አንድ ሺ ካሬ ላይ ያረፈ፣ ከ20 በላይ መኝታ ክፍሎች ያሉት ቤተመንግስት ገንብተውበታል፡፡ ካፒታሊዝም ‹‹ከለር ብላይንድ›› ነው ይላሉ፡፡ ድሀ የሚባል ቀለም አይታየውም፡፡
ሕዝብን ቀና ብለው መመልከት የሚከብዳቸው ፖለቲከኞችና ባለሐብቶች ከከተማው ወጥቶ መኖርን ፋሽን አድርገውታል፡፡ ለምሳሌ አቶ ልደቱ አያሌው መኖርያ ቤት የት ነው የሚሰሩት ብለን እንጠይቅ? ደብረዘይት የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ ለያዉም ወደ ሐይቅ የሚያይ ቪላ፡፡ ደግሞም ‹‹አንድ ያጣላል›› ብለው ነው መሰለኝ እዚያው በቅርብ ርቀት በልዩ የእንጨት ጥበብ ያጋጤ ባለ አንድ ፎቅ ድንቅ መኖርያ እያጠናቀቁ ነው፡፡ እርሳቸውስ የአዲሳባ ሕዝብ ከ97ቱ ክስተት በኋላ የጎሪጥ እያያቸው ተቸግረው ነው ከከተማ የራቁት እንበል፡፡ የአዲሳባ ሕዝብ እንደ ጻድቅ የሚቆጥረው ቴዲ አፍሮ ለምን ወደ ለገጣፉ ሸሸ?
ቴዲ ከመሐል ከተማ ሸሽቷል፡፡ ቦሌ ‹‹ጃፓን›› አካባቢ ይኖርበት ከነበረው ቤት ከወጣ ዘመን የለውም፡፡ ቴዲ ‹‹ሲኤምሲ›› መኖር ይረብሸዋል፡፡ በርግጥ ‹‹ሲኤምሲ›› ቤት ተከራይቶ ኖሯል፡፡ ሰው በመግጨት እስከተከሰሰባት እለት ድረስ የ‹‹ሲኤምሲ›› ልጅ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቤቱ ‹‹ቃሊቲ›› ሆነ፡፡ ከእስር ከተፈታ በኋላም እዚያው ‹‹ሲኤምሲ›› 500 ካሬ ሜትር ቦታ ገዝቶ የኔ የሚለውን ቤት ማዝገንባት ጀምሮ ነበር፡፡ ሆኖም ሰፈሩን ቆሌው አልወደደውም መሰለኝ ሳይጨርሰው በጅምር ትቶታል፡፡ ቴዲ አሁን የሚኖረው ለገጣፉ ነው፡፡ ለዚያውም ተከራይቶ፡፡
ቴዲን በ‹‹ሰይፉኛ›› ላቆላምጠውና ‹‹ቴዲሻ›› በቅርቡ የለገጣፉ ኪራይ ቤቱን ጨርሶ ወደራሱ ቤት ይዛወራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እዚያው ለገጣፉ ነው ታዲያ፡፡ ‹‹ካንትሪ ክለብ ሪልስቴት›› ነው ለዚህ ሞገስ የሚያበቃው፡፡ ወደ ጎልፍ ክለብ የሚያይ፣ የጧት ፀሐይ የሚያገኘው፣ ዜማና ግጥም እንደጅረት የሚያዘንብለትን ምን የመሠለ ቪላ ቤት በጣፉ የሞጃዎች ሠፈር እያጣደፉለት ነው፡፡ በአንድ ሺ ካሬ ላይ፡፡ ‹‹ሲሲዲዎች›› የተባረኩ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ ኮርነር ላይ ጥሩ ቦታ መርጠው ነው እየሰሩለት ያሉት፡፡ ታዲያ በችሮታ አይደለም፡፡ የካሳሁን ግርማሞ ልጅ ቴዲሻ 6.5 ሚሊዮን ብር ሆጭ አድርጎ ነው ይህ ቤት እየተሠራለት ያለው፡፡ ‹‹ዳህላክ ላይ ልስራ ቤት›› ያለው ብላቴና ወዶ አይደለም፡፡
እንግዲህ የሞቢል ሰፈሩ ልጅ ቴዲ በሁለት አስርተ ዓመታት ዉስጥ ከመሳለሚያ-ቦሌ ጃፓን፣ ከቦሌ ጃፓን-ሲኤምሲ፣ ከሲኤምሲ- ለገጣፉ ያደረገው ጉዞ ስለ ወደፊቷ አዲሳባ ብዙ የሚናገረው ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡መሐል ከተማ የሰፊው ሕዝብ ጫጫታ የሚረብሻቸው ሞጃዎች፣ የወፍ ድምጽ መስማት ያማራቸው ባለጸጎች…‹‹እንዲያውም መሐሉን አንፈልገውም›› ብለው እየራቁ ነው፡፡ ወደ ፉሪ፣ ወደ ጣፎ፡፡ እነርሱ ከመሐል በራቁ ቁጥር ዳሩን መሐል እያደረጉት ነው፡፡ እነርሱ ከመሐል በራቁ ቁጥር ጎስቋላ አባወራዎች እጅግ በጣም መራቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ካፒታሊዝም ‹‹ከለር ብላይንድ›› ነው ይላሉ፡፡ የድሀ ቀለም አያውቅም፡፡
በለገጣፉ የ‹‹ሲሲዲ›› መንደር ቴዲን ጨምሮ የናጠጡ ሐብታሞችና ባለሥልጣናት ሁሉ ቤት አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ባይኖሩበትም ቤት አላቸው፡፡ አንዳንዶች እንዳላቸውም ዘንግተውትም ቤት አላቸው፡፡ ጀግናው አትሌት ኃይሌን ጨምሮ ሁሉም የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና የሆኑ አትሌቶች ለገጣፉ ቤት አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹አላቸው›› ተብሎ የተነገረኝ የአትሌቶችን ዝርዝር እዚህ ላይ ለመግለጽ መሞከር ታላቁ ሩጫ ላይ የሚሳተፈውን ሰው በስም እንደመዘርዘር አሰልቺ ይሆንብኛል፡፡ ‹‹አላቸው›› ተብሎ የተነገረኝን ባለሥልጣናት እዚህ መዘርዘር የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን የመዘርዘር ያህል ያደክማል፡፡
እነዚህን ቅንጡ የ‹‹ሲሲዲ›› ቤቶች በጎበኘሁበት ወቅት ግቢ ዉስጥ የቆሙ 2 ‹‹ሀመር›› መኪኖች፣ ሌላ አንድ ‹‹ፖርሽ››፣ ሌላ አንድ ‹‹ኢንፊኒቲ›› ሌላ አንድ ለጊዜው ስሙን ያልደረስኩበት በአይነቱ ለየት ያለ መኪና፣ ብዙ ቶዮታ ራቫፎሮች፣ ጥቂት ካዲላኮች በተለያዩ ሰዎች ግቢ ዉስጥ ቆመው መመልከቴ ድንጋጤን ፈጥሮብኛል፡፡ ግቢ ዉስጥ የቆሙትን መኪኖች አለመመልከት ደግሞ አይቻልም፡፡ ምክንያቱ አጭር ነው፡፡ ሁሉም ቤቶች አጥር አልባ ናቸው፡፡
በለገጣፎ የ‹‹ሲሲዲ›› መንደር ቤት የሚታጠረው እጅግ በጣም በአጭሩ ነው፡፡ ማንኛውም ነዋሪ ቤቱን በረዣዥም የኮንክሪት ግንብ መለበጥ፣ በኮሽምና ባሕርዛፍ መደበቅ፣ በኤሌክትሪክ አጥር ማስፈራራት አይችልም፡፡ እንኳን ረዣዥም አጥር ማጠር ቀርቶ የአንድን ድንክ ሰው ቁመት የሚያክል አጥርም አይፈቀድም፡፡ ከግማሽ ሜትር ዘለግ ያሉ ነጫጭ የጣውላ ርብራቦች ብቻ ለአመል ያህል ይተከላሉ፡፡ ላያቸው በአበባ ይዋባል፡፡ በዚህ የተነሳ ሁሉም ሰው የሁሉንም ቤት ግቢ ማየት ይቻለዋል፡፡
ለነገሩ በዚህ መንደር ረዥም አጥር ለምን ያስፈልጋል? ቴዲ አፍሮ የኃይሌን ቱታ እንዳይሰርቅ ነው? ቀነኒሳ የአባዱላን ካልሲ ይዞ እንዳይሮጥ ነው? እውነትም በዚህ መንደር አጥር ለምን ያስፈልጋል? የአጥር አገልግሎት ድሮም ቡዳና ድሀን መከላከል ነው፡፡ በዚህ የጣፎ መንደር ደግሞ ሁለቱም የሉም፡፡ (ሙሔ ሐዘን ጨርቆስ ለዋዜማ ራዲዮ)