ዋዜማ- የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሆኑ ከአራት መቶ ሃምሳ በላይ ሰራተኞች “ያልተፈቀደ መሬት ለግል ጥቅማችሁ አርሳችኋል” በሚል ተወንጅለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ዋዜማ ከቅርብ ምንጮቿ ተገንዝባለች።
ታሳሪዎቹ የሱሉለ ፊንጫ ወረዳ እስር ቤት ሞልቶ ከአቅም በላይ በመሆኑ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ኢ-ሰብዓዊ በሆነ አያያዝ እየተንገላቱ ይገኛሉ ሲሉ የፋብሪካው ሠራተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉለ ፊንጫ ወረዳ የሚገኘው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ከታሰሩ ከአንድ ወር በላይ ማስቆጠራቸውንና፣ “የፋብሪካው ይዞታ የሆነውን መሬት አርሳችሁ ለግል ጥቅማችሁ አውላችኋል“ በሚል ተወንጅለው ለእስር መዳረጋቸውን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ምንጮች ጠቁመዋል።
ታሳሪዎቹ አብዛኞቹ በአካባቢው ቤተሰብ የሌላቸው፣ ጊዜያዊ ወይም የቀን ሠራተኛ መሆናቸውን የገለጹት ምንጮች፣ የእለት ጉርስ የሚያገኙት የአካባቢው ማኅበረሰብ አዋጥቶ ከሚወስድላቸው ምግብ መሆኑን አስረድተዋል።
እስረኞቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በዚሁ ሁኔታ ውስጥ ከአንድ ወር በላይ በሱሉለ ፊንጫ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያና ቀሪዎቹ ደግሞ በወረዳው በሚገኘው ወታራዊ ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል።
ታሳሪዎቹ በብዛት ፋብሪካው በሰጣቸው ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ እንደሆኑ የገለጹት ምንጮች አብዛኞቹ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ በመሆናቸው ፋብሪካውን ያለውን ባዶ መሬት በእጃቸው እየቆፈሩ በቆሎና ሰሊጥ በመዝራት የተወሰነ ጥቅም ሲያገኙበት እንደነበር ገልጸዋል።
ሆኖም የወረዳው አሥተዳደር ድርጊቱን እንዲያቆሙ በተደጋጋሚ አሳውቋቸው እንደነበርና፣ ሰራተኞቹ ድርጊቱን ባለማቆማቸው “ስለ ሥራ ጉዳይ ውይይት እዳደርጋለን“ ብሎ ከጠራቸው በኋላ ሰብስቦ እንዳሰራቸው ምንጮች አክለዋል።
ሰራተኞቹ፣ “ፋብሪካው የሚተዳደረው በፌዴራሉ መንግሥት ነው“ በማለት የወረዳው አሥተዳደር የወሰደውን እርምጃ መኮነናቸው የተነገረ ሲሆን መሰል እርምጃዎችን መውሰድ ካስፈለገም መውሰድ ያለበት ፋብሪካውን የሚያስተዳድረው የፌዴራሉ መንግሥት መሆን እንዳለበት ማስረዳታቸውን ጠቁመዋል።
ሆኖም የወረዳው አሥተዳደር፣ “የፌዴራሉ መንግሥት የሚመለከተው ስለ ፋብሪካው ቴክኒካዊ ጉዳዮች እንጂ ስለ መሬቱና ስለአካባቢው የሚመለከተው እኔን“ ነው ማለቱን ገልጸዋል።
የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በመለዋወጫ እቃ ችግር፣ በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ በሸንኮራ አገዳ ማሳውና በማሽኖቹ ላይ በተለያዩ ጊዜያት በሚደርስ የእሳት ቃጠሎ ለብዙ ጊዜያት ምርት የማቆም ችግር እንደሚያጋጥመው ዋዜማ በተደጋጋሚ መዘገቧ ይታወሳል።
አሁን ላይ ፋብሪካው የመለዋወጫ እቃዎች እየገቡለት መሆኑን የፋብሪካው ሠራተኞች ለዋዜማ ያስረዱ ሲሆን፣ በተደረገለት ጥገናና በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ በአንጻራዊነት በመሻሻሉ ወደ ምርት ሥራ ሊገባ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ዜና እየተጠናቀረ ባለበት ዛሬ አርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም ቀትር ላይ የሸንኮራ አገዳ ወደ ፋብሪካው እየገባ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት የስኳር ምርት ወደ ገበያ ሊያወጣ እንደሚችል ሰምተናል።
ይህንኑ ሥራ የደረሰበትን ሁኔታ ለማየት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር አወሉ አብዲ ጥር 3 ቀን ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል። [ዋዜማ]