Eritrea President Isayas Afeworkie

ዋዜማ- በሳምንቱ መጨረሻ ለብቸኛው የሀገራቸው ቴሌቭዥን ጣቢያ ቃለምልልስ የሰጡት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በርከት ያሉ ክሶችን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ አቅርበዋል። ዋዜማ የፕሬዝዳንቱን ቃለምልልስ ዋና ዋና ይዘት እንደሚከተለው አቅርባለች

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በላከው ደብዳቤ በኤርትራ ላይ ያቀረበው ክስ፣ አስገራሚ የውሸት ክስ ነው በማለት አጣጥለውታል።

ክሱ ርካሽ ውሸት ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ክስ ያቀረበው የጦርነት ዝግጅቱን ለመሸፈን ነው በማለት ከሰዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው፣ ኢትዮጵያ በብዙ የውስጥ ግጭቶች እና ቀውሶች እየታመሰች መሆኑንና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡባቸው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ይታይ የነበረው ተስፋ በግድየለሽነት መጥፋቱን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በሕወሃት መካከል የግጭት ማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በአገሪቱ የተፈጠሩትን ነገሮች ለመረዳት አስቸጋሪ መሆኑንና የግጭት ማቆም ስምምነቱ በቅን ልቦና እንዳልተተገበረ የገለጡ ሲኾን፣ መንግሥት በአማራ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች ላይ በግድየለሽነት ለምን ጦርነት ተከፈተ? በማለትም ጥያቄ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ብልጽግና፣ በአገር ውስጥ በተከሰቱ ችግሮች ላይ ከማተኮርና ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ፣ በኤርትራ ላይ ጦርነት ለመቀሰቅስ ለምን ይፈልጋል? በማለት ጭምር የጠየቁት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጦርነት አጀንዳው የአሜሪካ፣ የፈረንሳይና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ድጋፍ እንዳለው ቢያስመስልም ይህ ግን ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም ብለዋል።

የኢትዮጵያው ገዥ ብልጽግና ፓርቲ የገዛቸውን ድሮኖች እና የረጅም ርቀት ሚሳዔሎችና ታንኮች እየጠቀሰ በኤርትራ ላይ ስለሚያደርሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት በመፎከረ ላይ ይገኛል በማለትም ፕሬዝዳንቱ የከሰሱ ሲሆን፣ ይህን ዓይነቱን ዛቻ ማስተናገድ የሚችሉት ግን ታሪክን ባግባቡ የማያውቁ ሰዎች ብቻ ናቸው በማለት አጣጥለውታል።

ሆኖም የሞኝ ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ ሊደረጉ አይችሉም ብሎ ማሰብ አይቻልም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በእኛ በኩል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እናደርጋለን ብለዋል።

የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት ያለው ምክር፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ ከንቱ ጦርነት ውስጥ አታስገቡት የሚል እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ራዕይ መልካም የሁለትዮሽ ትብብርንና ጠንካራ ትስስር መፍጠር እንደነበር ፕሬዝዳንቱ የጠቀሱ ሲኾን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በኤርትራ ላይ የጦርነት ቀስቃሽ ቀስቃሽ ንግግር በማድረግ ተጠምዷል ብለዋል።

የጦር መሳሪያ የሚያጋብስና በየጊዜው በጦር ኃይል ማስፈራሪያ የሚያካሂድ መንግሥት ኤርትራን በምን አግባብ ይወነጅላል? ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ይህ አካሄድ ከተስፋ መቁረጥ የመነጨ፣ አደገኛ እና መቆም ያለበት ነው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ያም ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ጎረቤት አገራት የኢትዮጵያ መንግሥትን አካሄድ በጥንቃቄ ሊመለከቱት እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያነሳው የባሕር በር ጥያቄ ግድየለሽና ጀብደኝነት የተሞላበት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ ከዚህ አጀንዳ ጀርባ ሌሎች የውጭ ኃይሎች እንዳሉበት ግልጽ መሆኑ ጠቁመዋል። ከዚሁ አጀንዳ ጀርባ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት በቀጣናው የሚገኙ ወደቦችን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ያላቸው ሕልም እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ የኢምሬቶችን ፕሬዝዳንት ፍላጎትም ቅዠት በማለት አጣጥለውታል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ኤርትራ በ1940ዎቹ ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዳወትጣ መብቷን የነፈጋት፣ በተመሳሳይ የጅዖፖለቲካ ስሌት ነበር በማለትም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው፣ ስለ ጅቡቲ ወደብም አንስተዋል። የኢትዮጵያው የብልጽግና መንግሥት ኢትዮጵያ የጂቡቲ ወደብን ለገቢና ወጪ ንግዷ መጠቀም ትታ፣ ጅቡቲ በዓመት ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ የምታገኝበትን የወደብ አገልግሎት ወደ ኤርትራዋ አሰብ ወደብ ለማዞር ዝግጁ መሆኗን ባንድ ወቅት አንስቶት እንደነበርና የኤርትራ መንግሥት ግን ጎረቤት ጅቡቲን የመጉዳት ዕቅድ እንደሌለው ገልጦ ምላሽ እንደሰጠም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሌላንድ በኩል የባሕር ኃይል ጦር ሠፈርና የባሕር በር ለማግኘት ያደረገውን ጥረት፣ “ከፋፋይ”፣ “ጠብ ጫሪ” እና “የግድ የለሽነት ድርጊት” በማለት ወቅሰዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ኤርትራ በጎረቤቶቿ ላይ አንዳችም የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ወይም ምኞት ኖሯት እንደማያውቅ በመጥቀስም፣ ከሌሎች አገራት ጥቃት ሲደርባት ግን ሉዓላዊነቷን እንዴት እንደምታስጠብቅ ታውቃለች ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ የኤርትራ መንግሥት ከአሜሪካው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጋር ግንኙነቱን ለማደስ ማሰቡንና ይህ ግን ከአሜሪካ ልዩ ጥቅም ለመጠየቅ ሳይሆን በናይል ወንዝ ተፋሰስ፣ በቀይ ባሕር እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድና በባሕረ ሠላጤው ቀጠናዎች ዙሪያ ገንቢ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል ግንኙነት ለመመስረት ስለምንፈልግ ነው ብለዋል።

ኤርትራ ዋነኛ አጀንዳዋ ቀጠናዊ መረጋጋትና ጸጥታ ማስፈን መሆኑና እነዚህ አጀንዳዎች ደሞ ከአሜሪካና አውሮፓ ኅብረት ጋር ገንቢ ግንኙነት ለመፍጠር ቁልፍ እንደሆኑ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል። [ዋዜማ]