ዋዜማ፡ በመንግስትና በተወሰኑ የፋኖ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተደረገው የመጀመሪያው የድርድር ማመቻቸት ሙከራ የተሳካ እንደነበረ በጉዳዩ የተሳተፉ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለዋዜማ ተናግረዋል።
ስለውይይቱ ዝርዝር ይዘትና አንዳንድ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎችን መናገር እንደማይፈልጉ የገለፁት የዲፕሎማቲክ ምንጫችን ከፋኖ ታጣቂዎች አንድ አንጃ ከወከላቸው አባላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
ከሌሎች ሁለት የፋኖ አንጃዎች ጋርም ውይይት ለማድረግ ጅምሮች መኖራቸውን ግን ደግሞ በውይይቱ ለመግፋት መደነቃቀፎች እንዳጋጠሙ ከምንጫችን ተረድተናል።
ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት የመጀመሪያው የድርድር ቅድመ ውይይት የተካሄደው በአቶ እስክንድር ነጋ ከሚመራው “የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት” ተወካዮች ጋር እንደነበረ መረዳት ችለናል።
የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የአፍሪቃ ሕብረትና የኢጋድ ተወካዮችን ያካተተው የዲፕሎማቲክ ልዑካን “የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት” ተወካዮችን ያነጋገረው በመንግስት ዕውቅናና ታጣቂዎቹ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ተገኝቶ መሆኑን መሆኑንም ተገንዝበናል።
የዲፕሎማቲክ ቡድኑ ሁሉንም የፋኖ ታጣቂዎች አንድ ላይ ለማነጋገር ፍላጎት ቢኖረውን ለውይይቱ ፍላጎት ካሳዩና ተወካዮቻቸውን ካሳወቁ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ተሳትፏቸውን ያቆሙ አንጃዎች መኖራቸውን ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል። አንዳንድ አንጃዎች ጉዳዩ መልክ እስኪይዝ ድረስ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት በምስጢር እንዲያዝ እንደሚፈልጉም አመልክተዋል።
በመንግሥት በኩል የፋኖ ታጣቂዎች አንድ ሆነው ለድርድር መቀመጥ ካልቻሉ በተናጠልም ቢሆን የድርድርን ሀሳብ ከተቀበሉ ቡድኖች ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው ቀደም ብሎ ማሳወቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በኩል የተናጠል ንግ ግሩ የክልሉን ግጭት ማስቆም ይችል እንደሆነ ገምግሞ ስለ ቀጣይ ድርድር ውሳኔ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ስምተናል።
የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የፋኖ ታጣቂዎችን ለማነጋገር ፍላጎት ያሳየው በአማራ ክልል ሰላም ካውንስል በኩል ነው።
ከኹለት ወራት ገደማ በፊት በምክር ቤቱ በኩል ሁሉንም የፋኖ ክንፎች ያካተተ ተወካይ ቡድን፤ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር እንዲነጋገር ሙከራ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ በተለያየ የአደረጃጀት ክንፍ የተከፋፈሉት የፋኖ ታጣቂዎች በጋራ ለመነጋገር ባለመስማማታቸው ሳይሳካ መቅረቱን የምክር ቤቱ የዋዜማ ምንጮች ገልጸዋል።
መንግሥት እና የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ድርድር እንዲመጡ የማመቻቸት ሚና ለመጫወት የተቋቋመው የአማራ ክልል ሰላም ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴውን አቁም ሁኔታዎችን በአንክሮት እየተከታተለ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።
ምክር ቤቱ እንቅስቃሴውን ለመግታት የተገደደው በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በኩል አለመተማመን እና ድርድርን በቁርጠኝነት የመቀበል ቸልተኝነት ስለገጠመው ነው ተብሏል።
ምክር ቤቱ እንደ አሜሪካን ጨምሮ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም፣ የተቋቋመለትን ኹለቱን ወገኖች ወደ ድርድር የማምጣት አላማ ባለፉት ሰባት ወራት ማሳካት አልቻለም።
የፋኖ ታጣቂዎች መሪዎችን እና ዲፕሎማቲክ ማኅበረቡን ለሚገናኘት ያደረገው ጥረት ያልተሳካለት ምክር ቤቱ አሁን የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ተወካዮች ያደረጉትን “ሚስጥራዊ ውይይት” በማመቻቸት ሂደቱ እንደሌለበት ዋዜማ ከምክር ቤቱ ምንጮቿ ተረድታለች።
የአማራ ክልል ሰላም ምክር ቤት ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጋር መነጋገርና ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቅ ከጀመረ በኋላ በመንግስት በኩል “በበጎ እንደማይታይ” ና “በር እንደተዘጋበት” ተወካዮቹ ነግረውናል።
ይሁንና መንግስት የምክር ቤቱን የበታች የወረዳ አደረጃጀቶች ተጠቅሞ ታጣቂዎችን በሽምግልናና በመደለያ ወደ መንግስት እጅ እንዲሰጡ እየተጠቀመባቸው መሆኑን አንዳንድ አባላቱ ያስረዳሉ። [ዋዜማ]