ዋዜማ ራዲዮ- የፀጥታው ምክር ቤት የሶማሊያና የኤርትራን ጉዳይ የሚቆጣጠረው ኮሚቴ ኤርትራ ባለፈው አንድ አመት ለአልሽባብ ድጋፍ ስለማድረጓ ማስረጃ ማግኘት አልቻልኩም አለ።
ኮሚቴው ኤርትራ ለሌሎች ተቃዋሚዎች በተለይም ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የገንዘብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን በስፋት ያትታል።
ተቆጣጣሪ ቡድኑ ባለፉት ዓመታት ሶስት ሪፖርቶቹ ኤርትራ ለሶማሊያው ሸማቂ ቡድን ድጋፍ ማድረጓን ከሁለተኛ ደረጃ ምንጮች በተገኘ መረጃ አስደግፎ ሲያቀርብ ቢቆይም በዘንድሮ ሪፖርቱ ግን ኤርትራን ለመወንጀል የሚያበቃ ምንም ማስረጃ እንዳላገኘ ለፀጥታው ምክር ቤት ሪፖርት አድርጓል።
በዚሁ ሪፖርት ላይ ኤርትራ አምስት ለሚሆኑ የኢትዮጵያና ለአንድ የጅቡቲ ታጣቂ ቡድኖች የስልጠና የገንዘብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን አብራርቶ ይህም በጎረቤት ሀገራት በኩል ክስ የቀረበበት መሆኑን አስረድቷል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የቤንሻንጉል ነፃ አውጪ ድርጅት፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጦር መሳሪያና ገንዘብ ከኤርትራ መንግስት በመቀበል ስማቸው ተዘርዝሯል።
ኮሚቴው በዋናነት ኤርትራ በሶማሊያ ጉዳይ የተጣለባትን ማዕቀብ ማክበርና አለማክበሯን የመቆጣጠር ሀላፊነት የተሰጠው ነው።
ኢትዮጵያ የምትደግፋቸውን የኤርትራ ተቃዋሚዎችንም ይህ ሪፖርት የዘረዘረ ሲሆን ማዕቀብ ያልተጣለባት ኢትዮጵያን በክፉ አላነሳም።
ኤርትራ ማዕቀቡንም ሆነ የሚቀርብባትን ውንጀላ “ፍርደ ገምድል ነው” በሚል ስትከራከር ብትቆይም ስሚ አላገኘችም።
ከአስር አመታት በፊት የጦር መሳሪያ እንደጫነ የተገመተ አነስተኛ አውሮፕላን ከአስመራ ተነስቶ ሞቃዲሾ በማረፍ ለአልሸባብ ድጋፍ አቀብሏል በሚል የተጀመረው ክስ በአስመራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። በተመሳሳይ ወቅት ሁለት የኤርትራ የመንግስት ሚዲያ ጋዜጠኞችና አራት የደህንነት ሰራተኞች ሶማሊያ ውስጥ መያዛቸው በኤርትራ ላይ የሚቀርበውን ውንጀላ አጠናክሮታል።