ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ-መር የሆነውን ዕድገቷን ለማፋጠን ትኩረቷን ወደ ጥጥ እርሻ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና ስፌት ምርት በማዞር ላይ ትገኛለች፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ሀገሪቱን በ2025 ዓ.ም የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የተያዘው ጥረት አንድ አካል ሲሆን ባለፈው ዐመትም ሀገሪቱን በጥጥ አምራችነት አሁን በአፍሪካ ካለችበት አስረኛ ደረጃ ወደ አንደኛ ደረጃ ለማሳደግ የ15 ዐመት መርሃ ግብር ቀርፃለች፡፡ አሁን አሁን መንግስት ጥጥና ጨርቃ ጨርቅን የMade In Ethiopia ትርክቱ ማጠንጠኛ እያደረገው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ባጭር ጊዜ ውስጥ የተጋነኑ ግቦቹን ለማሳካት በሚያደርገው ጥድፊያ ሀገሪቱ ምን ያህል ከባድ ዋጋ ትከፍል ይሆን? የሚለው ጥያቄ ግን ስጋት መደቀኑ አልቀረም፡፡ የጥጥ እርሻ እና ሀገር በቀል ጥጥን የሚጠቀሙ የውጭ ኩባንያዎች ቢያንስ በዐለም ዐቀፍ ደረጃ በሚታወቁ የሰብዓዊ መብት እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ጋር በቀጥታ መላተማቸው የማይቀር ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ ደሞ መንግስትንም ሆነ የውጭ ኩባንያዎችን ውልውል ውስጥ የሚከት መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡
በምስራቅ እስያ የጉልበት፣ የጥሬ እቃ እና የምርት ሰንሰለት ወጭው በመጨመሩ ቀላል የጨርቃ ጨርቅና ስፌት ፋብሪካዎች ፊታቸውን ወደ አፍሪካ በተለይም ወደ ምስራቅ አፍሪካ እያዞሩ ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኢንቨስትመንት ሳቢ የሆኑ ፖሊሶዎችን በመቅረጻቸው፣ የአሜሪካ እና አውሮፓ ጨርቃ ጨርቅገበያ ልዩ ተጠቃሚ መሆናቸው፣ መሰረተ ልማት በማሻሻላቸው እና የጉልበት ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ የምስራቅ እስያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችን እየሳቡ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ለጥጥ እና ጨርቃ ጨርቅ ላኪዎች ሰፊ የቀረጥ እፎይታ ጊዜ መስጠቱ፣ ኢንዱስትሪ ዞን ማዘጋጀቱ፣ ርካሽ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረቡ እና ሌሎች አጓጊ ማበረታቻዎችን አቅርቧል፡፡ መሬት በመንግስት የተያዘ መሆኑን እንደ ጥሩ እድል የቆጠሩ ኩባንያዎችም በብዛት በጥጥ እርሻ በመሰማራት ላይ ናቸው፡፡ አብዛኛው የሀገሪቱ አየር ንብረት ለጥጥ እርሻ ተስማሚ መሆኑ ለምርት ሰንሰለቱ የሚወጣውን ወጭ ዝቅተኛ ስለሚያደርገው ኩባንያዎቹን የሳባቸው ይመስላል፡፡
መንግስት ለውጭ ጥጥና ጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያዎች ሰፊ የቀረጥ እፎይታ ጊዜ እና ሌሎች ማበረታቻዎችን ጭምር ከማቅረቡ ሌላ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ምርት African Growth and Opportunity Act (AGOA) በተሰኘው ልዩ የገበያ እድል ተጠቃሚ በመሆኑ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ገበያዎች ከቀረጥ ነጻ ማስገባት መቻሉ የእስያ ኢንዱስትሪዎችን አስጎምጅቷቸዋል፡፡ በርግጥ አጎዋ ስራ ላይ የዋለው ከአስራ ስምንት ዐመታት በፊት ቢሆንም የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ መነቃቃት የጀመረው ግን ባለፉት አምስት ዐመታት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የረጅም ጊዜ ጥጥ እና ጨርቃ ጨርቅ ኢንቨስትመንት ግን በርካሽ የጉልበትና የምርት ወጭ ወይም በቀረጥ እፎይታ ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የውጭ ኩባንያዎች ሙዓለ ንዋያቸውን በሚያፈሱባቸው ሀገራት ሰላምና መረጋጋትን፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን፣ ሰብዓዊ መብት ጥበቃን፣ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄን፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እና አካባቢ ጥበቃን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ፡፡ ለማስገባትም ይገደዳሉ፡፡ በዘመነ ግሎባላይዜሽን የአመራረት፣ የምርትና የገበያ ሰንሰለቱ የተሳሰረ እና ለልዩ ልዩ ቁጥጥሮች የተጋለጠ በመሆኑ ማንኛውም ኩባንያ በዐለም ዐቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ገዥ የኢንቨስትመንት ሞራላዊ እና ህጋዊ መርሆዎችን ከሞላ ጎደል ማክበሩ ግዴታ እየሆነ መጥቷል፡፡
ቨሪስክ ማፕሌክሮፍት የተሰኘው ዐለም ዓቀፍ የገበያ አዋጭነት አጥኝ ድርጅት አምና ባካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ በመጭዎቹ አምስት እና አስር ዐመታት የጥጥ እርሻ ልማትንና እና ጨርቃ ጨርቅ ኢንቨስትመንትን ለአደጋ የሚያጋልጡሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅሷል፡፡ በዋናነት የጠቀሳቸው የኢንቨስትመንት ስጋቶችም የለም መሬት ቅርምት፣ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ፣ ከመሬት በግዴታ በመፈናቀል ሰበብ የሚነሱ ግጭቶች፣ የሕጻናት እና ሌሎች ሠራተኞች ጉልበት ብዝበዛ፣ አካባቢ ጥበቃ እና ፖለቲካዊ አመረጋጋት ዋና ዋና አድርጎ አስቀምጧቸዋል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በመሬት ቅርምት ምክንያት የሚገጥማት የአደጋ ተጋላጭነት ከአሜሪካ፣ ህንድና እና ብራዚል ጋር አወዳድሮ ከአስሩ 1.3 ውጤት ነው የሰጣት፡፡ ይሄ ደሞ በጣም ዝቅተኛው በመሆኑለ ኩባንያዎቹ ማስጠንቀቂያ ደወል መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
በዚህ ረገድ በተለይ በዐለም የታወቀው የስዊድኑ H&M የተሰኘው ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኩባንያ የሚረከባቸው ጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በደቡብ ኦሞ ሸለቆ በመሬት ቅርምት በተያዘ መሬት ላይ ከተመረተ ጥጥ የተገኙ መሆናቸው ከሦስት ዐመታት በፊት በዐለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙሃን መጋለጡ ለከፍተኛ የዝና መጠልሸትና ኪሳራ ነው የዳረገው፡፡ ኩባንያው ከመሬት ቅርምት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ቢያስተባብልም የደቡብ ኦሞን ጥጥ በስፋት ከሚጠቀመው የሼክ መሃመድ አላሙዲን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ጋር ሽርክና እንዳለው መገለጹ ውግዘት አስከትሎበታል፡፡ H&M በኢትዮጵያ ሦስት ጨርቃ ጨርቅ ምርት አቅራቢ ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን አንዱ ይኸው በትግራይ የሚገኘው የሼክ አላሙዲን ፋብሪካ እነደሆነ ነው የታወቀው፡፡
ኩባንያዎች በምርታቸው ዑደት ውስጥ ያሉት ሀገሮች ወይም ሸሪክ ኩባያዎች በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስማቸው የሚነሳ ከሆነ ደሞ ምርታቸውን በውጭ ገበያ ሲሸጡ ማዕቀብ እንደሚገጥማቸው ጥርጥር የለውም፡፡
H&M ኩባንያ በቅርቡ አንድ ጥቁር ትውልደ ኬንያዊ የሆነ ሞዴል ህጻን በለበሰው ሹራብ ላይ የሰራው ማስታወቂያ ዘረኝነትን የሚያንጸባርቅ ሆኖ ተገኝቶበታል፡፡ ሹራቡ የተመረተው ደሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የኩባንያው ምርት አቅራቢ ሸሪክ ፋብሪካዎች እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡ ይህም ከመሬት ቅርምት ውንጀላው በተጨማሪ ዘረኝነት ታክሎበት በH&M ላይ ውግዘቱ በርትቶበታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ኩባንያው ራሱ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በጨርቃ ጨርቅ ምርት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው መግለጽ ከጀመረ ቆይቷል፡፡
መረጋጋት ያቃተው ሀገር ማን ገንዘቡን ያፈሳል?
የሀገሪቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሌለው የጥጥና ጨርቃ ጨርቅ ኢንቨስትመንቱን አስበርጋጊ ምክንያት እንደሆነ ነው እየታየ ያለው፡፡ እንደ አበባ እርሻዎች ሁሉ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችም ላለፉት ሦስት ዐመታት በቀጠለው ህዝባዊ አመጽ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ እንደ ዐለም ዐቀፍ አማካሪ ድርጅቱ ጥናት ከሆነ ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት መጠቁም ያገኘችው ነጥብ ህዝባዊ አመጹ ሲቀሰቀስ ከነበረበት አራት ነጥብ ወርዶ ባለፈው ዐመት መገባደጃ ወደ 2.7 አሽቆልቁሏል፡፡ ፖለቲካዊ ቀውሱ አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ ደሞ ዐለም ዐቀፍ ሜዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ስላደረገው ወደፊት ለመምጣት በሚያስቡ ኩባንያዎች ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም፡፡
መንግስት አሁንም ለህዝቡ ጥያቄዎች ሁነኛ መፍትሄ አልሰሰጠም፡፡ የውጭ ፋብሪካዎች መንግስት በመሬት ሰበብ የተነሱ ቅሬታዎችን እና ግጭቶችን በሃይል ሲጨፈልቃቸው ነው የሚያዩት፡፡ የጥቃት ሰለባ የሆኑትም በተለይ ለበደቡብ ኦሞ እና ኦሮሚያ ክልል ለእርሻ እና ሌሎች ኢንቨስትመንቶች የተሰጡ ሰፋፊ መሬቶች በርካታ አርብቶ አደሮችን ያለ ግጦሽ መሬት በማስቀረት የተገኙ በመሆናቸው እንደሆነ ኩባንያዎቹም ሆኑ በዐለም ዙሪያ ያሉ የምርት ገዥዎቻቸው ተረድተውታል፡፡ በተለይ በሀገር ውስጥ ጥጥ የሚያመርቱ ወይም ሀገር በቀል ጥጥን ለጥሬቃነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ወደፊት ለሚነሱ ብጥብጦችና ሁከቶች ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያደረባቸው ስጋት አልተቀረፈም፡፡ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት የሚፈልጉ ፋብሪካዎች ደሞ ለጸጥታና መረጋጋት ቅድሚያ መስጠታቸው የማይቀር ነው የሚሆነው፡፡
የውጭ ኩባንያዎች በባህሪያቸው ጠንካራ መንግስት ያላቸውን ሀገሮች የሚመርጡ በመሆኑ መሬት በመንግስት ቁጥጥር ስር መሆኑን እንደ መልካም እድል ቆጥረውት ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከመሬት መፈናቀል እና መሬት ቅርምት ጋር የተያያዙ ደም አፋሳሽ ግጭቶች መደጋገማቸው በኩባያዎቹ ተስፋ ላይ በረዶ ነው የቸለሰበት ማለት ይቻላል፡፡
ርካሽ ጉልበትና የኢንደስትሪ ፓርክ ግንባታ
በአሉታዊ መልኩ ሲታይ ደሞ የኢትዮጵያ የሠራተኛ ሕግ እና የቁጥጥር ደንቦች ልል መሆናቸው ፋብሪካዎች የሕጻናት ጉልበት ለመበዝበዝ እና ሠራተኞችን ከጸረ ተባይ እና ሌሎች የፋብሪካ ኬሚካሎች በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ወጭ እንዳያወጡ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በርግጥም በዚህ ክፍተት ተማርከው የገቡ ማህበራዊ ሃላፊነት የማይሰማቸው ኩባንያዎች እንዳሉ ዐለም ዐቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ፡፡ የስዊድኑ H&M ራሱ ለሠራተኞቹ በወር 40 ዶላር (ወይንም አንድ ብዝበ ሺህ ሁለት መቶ ብር) ብቻ እንደሚከፍል ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡
እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ባለፉት ጥቂት ዐመታት የቱርክ፣ ቻይና፣ ስዊድን እና አሜሪካ ትላልቅ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዘርፉ ተሰማርተዋል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊትም “ውክሲ ቁጥር አንድ” የተሰኘ ግዙፍ የቻይና ኩባንያ በ220 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመገንባት መሰረት ድንጋይ ማስቀመጡ ተገልጧል፡፡ ባለፉት ሦስት ዐመታት ብቻ የጨርቃ ጨርቅ የውጭ ሙዓለ ንዋይ ፍሰት ከ160 ሚሊዮን ብር ወደ 36 ቢሊዮን ብር እንደተመነደገ ነው የመንግስት አሃዞች የሚያሳዩት፡፡
መንግስት የውጭ ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብ እየተጠቀመበት ካለው ዘዴ ዋነኛው የጨርቃ ጨርቅ ምርትን ማዕከል ያደረጉ ኢንዱስትሪ መንደሮች ማቋቋም እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዐመታትም በኮምቦልቻ፣ አዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ጂማ፣ ሻሸመኔ፣ ናዝሬት ኢንዱስትሪ መንደሮቹ ተቋቁመዋል ወይም በመቋቋም ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢንዱስትሪ መንደሮች 60 በመቶው ግብዓታቸው ጥጥ እንደሆነ ነው መንግስት የሚናገረው፡፡
ላለፉት ዐመታት መንግስት ስለ አበባ አምራች የውጭ ኩባንያዎች እና በዘርፉ ኢንቨስትመንት ስለተገኘው ስኬት ሲሰክክ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን ዘርፉ መሰናክል ስለገጠመው አሁን ደሞ ወሬው ሁሉ ስለ ጥጥና ጨርቃ ጨርቅ ኢንቨስትመንት ከሆነ ሰነባበተ፡፡ ችግሩ ግን የውጭ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች በብዛት እየገቡ ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ጥሬ እቃ ምርት ማለትም የጥጥ ምርት በመጠን በቂ አይደለም፡፡ በያዝነው ዐመት የሀገሪቱ አጠቃላይ ጥጥ ምርት 44 ሺህ ቶን እንደደረሰ ነው አሃዞች የሚሳዩት፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ከውጭ ገበያ ገዝተው የሚያመርቱት፡፡ በተለይ መንግስት ሀገረ በቀል ፋብሪካዎችን ለማበረታታት በሚል ምክንያት የተዳመጠ ጥጥ ወደ ውጭ በሚልኩ ነጋዴዎች ላይ ለስድስት ዐመታት እገዳ ጥሎ ስለነበር ጥጥ አምራቾች ወደ ሌላ ዘርፍ መዞራቸው ላሁኑ እጥረት የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ መንግስት ይህንኑ እገዳ ያነሳው ገና ታች አምና ነው፡፡
የሀገር በቀሉ ጥጥ ምርት የጥራትም ችግር ያለበት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ዐለም ዐቀፍ ጥራቱ የተረጋገጠ ሀገር በቀል የተፈጥሮ (organic) ጥጥ ለማምረት በደቡብ ኦሞ በሺዎች የሚቆጠር ሄክታር ለም መሬት ለውጭ ኩባንያዎች ሰጥቷል፡፡ እንደ ሁመራ እና ተንዳሆ ካሉት የመንግስት ሰፋፊ እርሻዎች ሌላ በአነስተኛ አምራቾች ተይዞ የኖረው የጥጥ እርሻ ልማት ከቅርብ ዐመታት ወዲህ ወደ ስድስት ክልሎች እንደተስፋፋ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ስጋት
በርግጥ በመርህ ደረጃ ዘላቂ ልማትን መሰረት ያደረገውንና የተፈጥሮ ጥጥ አመራረት ዘዴን መከተል አንዱ መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል፡፡ በዚህ ዘዴ የሚመረተውም ጥጥ በዐለም ገበያ ተፈላጊ ነው፡፡ በያዝነው ወር በአርባ ምንጭ ዘሪያ 200 አነስተኛ ጥጥ አምራች ገበሬዎች ከውጭ ድርጅቶች ባገኙት ስልጠና በዘላቂ አመራረት ዘዴ ደረጃውን የጠበቀ የተፈጥሮ (oganic) ጥጥ ማምረት ለመቻላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ያገኙት ገና ከአንድ ወር በፊት ነው፡፡ ምርታቸውም ከድሮው ጋር ሲነጻጸር በመቶ እጅ የጨመረላቸው ሲሆን ለአካባቢ ጥበቃ ደሞ ተስማሚ ነው፡፡ እንደ H&M ያሉ ኩባንያዎችም ትኩረታቸው እዚሁ ላይ እንደሆነ ይሰብካሉ፡፡
ያም ሆኖ አነስተኛ አምራቾች ከእሴት ሰንሰለቱ ተጠቃሚ ባለመሆናቸውና በሌሎች ምክንያቶች በዐለም ዐቀፍ ደረጃ እንዲህ ያለው ምርት ሲዋዥቅ ነው የሚታየው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ባሁኑ አያያዙ አዝጋሚ በሆነው ዘዴ በአነስተኛ አምራቾች ላይ ተስፋውን ጥሎ ሌሎች አቋራጭ አማራጮችን ችላ ይላቸዋል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡
ለዚህም ይመስላል መንግስት የሀገሪቱን የጥጥ አቅርቦት ለማርካት ሲል ሌላ ያልተጠበቀ የፖሊሲ ለውጥ ደያረገው፡፡ ይኸውም የአካባቢ ጥበቃ ሚንስቴር በሚያወጣው መስፈርት መሠረት የጥጥ ልውጥ ህያውያን (ዘር መል) ዝርያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፓርላማውም ከሦስት ዐመት በፊት በአዋጅ መፍቀዱ ነው፡፡ አዋጁን መነሻ በማድረግም መንግስት ሀገር በቀሉን ምርታማ የሆኑ እና በሽታን መቋቋም የሚችሉ የተባለላቸውን ልውጠ ሕያውያን (Genetically Modified-GMO) ዝርያዎች ከውጭ አስገብቶ ሙከራ እያደረገ ነው የሚገኘው፡፡
ለጊዜው ከጥጥ ውጭ ሌሎች ዝርያዎች ወደ ሀገር እንዳልገቡ ቢታመንም የአካባቢ ጥበቃ እና አዝርዕት ባለሙያዎች ግን የመንግስት የፖሊሲ ለውጥ ወደፊት ዘር መል የሆኑ የምግብ እህል ዝርያዎች ጭምር ወደ ሀገሪቱ ገብተው ነባሮቹን ሀገር በቀል ዝርያዎች እንዲበክሉ በር የሚከፍት ነው በማለት ከወዲሁ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የጥጥ ምርታማነትን በፍጥነት በማሳደግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማፈስና የአህጉሪቱ ጨርቃ ጨርቅና ስፌት ማዕከል ለመሆን ለቋመጠው መንግስት ግን እንዲህ ያለውን ክርክር ለመስማት የሚፈቅድበት ጊዜ ያለፈ ይመስላል፡፡
ሀገሪቱ 2.6 ሚሊዮን ሄክታር የሚገመት ለጥጥ ምርት ተስማሚ የሆነ መሬት እንዳላት ነው የሚገመተው፡፡ መንግስት የኢንዱስትሪ ልማት እቅዶቹን ለማሳካት በያዘው ጥድፊያ ከገፋበት ደሞ ለም መሬት እየቸበቸበ ሊቀጥል እንደሚችል ይታመናል፡፡ ያ ማለት ደሞ ቢያንስ የመሬት ፖሊሲ ለውጥ እስካተደረገ ድረስ በቀጣዮቹ ዐመታት በጥጥ ምርት ሰበብ በመሬት ቅርምት፣ መፈናቀል፣ በካሳ ክፍያ፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እና አካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ግጭቶች እየበዙ ሊሄዱ እንደሚችሉ ግምት ማሳደር አያስቸግርም፡፡ ከመንግስት ፖሊሲ ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ድርቅ፣ ደን መመናመን እና የህዝብ ቁጥር መጨምር ደሞ ወደፊት በመሬት ላይ የሚነሳውን ግጭት እንደሚያባብሱትና የረዥም ጊዜ የጥጥ እርሻ ኢንቨስትመንትን አስቸጋሪ እንደሚያደርጉትም መጠበቅ ይቻላል፡፡[የድምፅ ዘገባ ከታች ያድምጡ]
https://youtu.be/XX7J8p9wspI