Tewodros Teshome-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት በስሩ ሲያስተዳድራቸው ከነበሩ የልማት ድርጅቶች መካከል በተለያየ ዙር ጨረታ እያወጣ ለግሉ ዘርፍ እያስተላለፈ ቢቆይም የግዮን ሆቴልን ለመሸጥ ያወጣው ተደጋጋሚ ጨረታ ግን ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል።ሆቴሉን ለመሸጥ ከጫፍ የተደረሰባቸው ጊዜያት ቢኖሩም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል።ለቀድሞ ባለቤቶቹ ይሸጣል ተብሎም ነበር።


ግዮን ሆቴል ያለበት ቦታ በብዙ ባለሀብቶች እንደ ዋና ተፈላጊ የንግድ ምቹ ቦታ ቢታይም የሆቴሉ ይዞታ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስት የቆረጠለት ዋጋ የማይቀመስ መሆኑ ላለመሸጡ አንዱ ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል። ሆኖም ከሰሞኑ የዋዜማ ሪፖርተር በሆቴሉ ግቢ ተገኝቶ እንዳስተዋለው መንግስት በተደጋጋሚ ጨረታ አውጥቶ ለመሸጥ ላልተሳካለት ሆቴል አዲስ አካሄድ መከተል ጀምሯል። የሆቴሉ ግቢ የተወሰነው መሬት በጨረታ ተከራይቶ አዲስ ሬስቶራንትና ሲኒማ ቤት እየተገነባበት ነው።


የመሬት ጨረታ ማሸነፉ ተነግሮለት በሆቴሉ ግቢ ውስጥ ሬስቶራንትና ሲኒማ ቤት እየሰራ ያለው የሴባስቶፖል ሲኒማ ባለቤት ቴዎድሮስ ተሾመ ነው።ቴዎድሮስ ተሾመ ቀዝቃዛ ወላፈን በሚለው ፊልሙ የኢትዮጵያን የሲኒማ ስራ እንደ አዲስ እንዳስጀመረ የሚነገርለት ሲሆን ከዚያም በርካታ የሲኒማ ስራዎችን ሰርቷል። አሁን ደግሞ በግዮን ሆቴል በጀርባ አጥር ባለው ስፍራ ላይ ነው ሬስቶራንትና ሲኒማ ቤት በማሰራት ላይ ነው።


ከግዮን ሆቴል አመራሮች መረዳት እንደቻልነው በቴዎድሮስ ተሾመ የሚሰራው ሬስቶራንት ዋናው ግዮን ሆቴል የሚያቀርብለትን ምግብ ነው አትርፎ ለመሸጥ ስምምነት ያለው። ይህ አካሄድ በምን ተመራጭ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ከሆቴሉ ግቢ ምን ያክል ስፋት ያለው መሬት ለጨረታ ቀርቦ እንደነበርና በምን ያህል ዋጋ እንደተከራየ ግን የሆቴሉ አመራሮች ለመናገር ፍቃደኛ አልሆኑም።

በሆቴሉ ግቢ ውስጥ የተለያዩ ነባርና አዳዲስ ተከራዮች ያሉ ሲሆን ለሆቴሉ ደንበኞችና ለሌሎች አገልግሎት ይሰጣሉ።


ቴዎድሮስ ተሾመ በበከሉ ግዮን ሆቴል ግቢ ውስጥ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ለ 14 አመታት ለመንግስት ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረ ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ መቆየቱን ለዋዜማ ራዲዮ ያስረዳ ሲሆን አሁን አዲስ የሆቴሉ አመራር ምጣቱን ተከትሎ በግቢው ውስጥ ለሚደረግ ኢንቨስትመንት ጨረታ ወጥቶ የጨረታው አሸናፊ ሆኖ ወደ ስራ መግባቱንም አክሎ ገልጾልናል።


ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ ወጥቶ በነበረው ጨረታ ሌሎች ተሳታፊዎች ተጫርተዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን ተሳታፊዎች ለዋዜማ ራዲዮ እንደገለጹት በጨረታው ብንሳተፍም የመረጃ አሰጣጥ ላይ ግን የግልጽነት ችግሮች ነበሩ ብለውን : ጨረታውን እንለፍ እንውደቅ እንኳ በግልጽ ሳይነገረን ውጤቱን ማወቅ የቻልነው በሆቴሉ ግቢ ውስጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መኖሩን ስንሰማ ነው ሲሉ ገልጸውልናል። ሌላ አንድ የጨረታው ተሳታፊ ደግሞ ጨረታው ለይስሙላ የወጣ ነው ብለው እንደሚያስቡ ብቻ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።


ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ የግዮን ሆቴል ከፍተኛ አመራር ለዋዜማ እንደገለጹት ከሆነ ግን ጨረታው ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ተጽእኖ ተከናውኖ አሸናፊው የተለየበት እንደሆነ ነው የተናገሩት። [የዋዜማ ራዲዮ የድምፅ ዘገባዎችን ከታች ይመልከቱ]

https://www.youtube.com/watch?v=5V9HMEJPAos