ዋዜማ ራዲዮ- የግል ንግድ ባንኮች ለምርት አስመጭ ደንበኞቻቸው የውጭ ምንዛሬን ለመፍቀድ በአንድ የአሜሪካ ዶላር እስከ 30 ብር ኮሚሽን እያስከፈሉ መሆኑን ዋዜማ ሬዲዮ ያሰባሰበችው መረጃ ያሳያል።
ያነጋገርናቸው አስመጭዎች እንደነገሩን በተለያዩ የግል ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬን ለማስፈቀድ የአንድ የአሜሪካ ዶላር ይፋዊ የመሸጫ ዋጋው 52 ብር ከ64 ሳንቲም እንዳለ ሆኖ ኮሚሽን 30 ብር በመጨመር ለእያንዳንዱ የአሜሪካ ዶላር 82 ብር ይከፍላሉ።
የውጭ ምንዛሬ ሽያጩ እየተከናወነ ያለውም የምንዛሬ ፈላጊዎችን ምርት ወደ ውጭ ልከው የውጭ ምንዛሬ ካላቸው ሌሎች የባንክ ደንበኞች ጋር በማገናኘት ነው። ለእያንዳንዱ የውጭ ምንዛሬ የሚከፈለው ኮሚሽንም ባንኮቹ እና የውጭ ምንዛሬ ያላቸው ሰዎች የሚከፋፈሉት ይሆናል።
ለአንድ የአሜሪካ ዶላር የሚከፈለው ኮሚሽን ከምንዛሬው ይፋዊ ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ መሆኑም በሀገሪቱ የተፈጠረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያሳየ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶውን ገቢ እንዲያደርጉለት ካዘዘ በኋላም በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ይህ ነው የሚባል የውጭ ምንዛሬን አለማቅረቡም ሌላኛው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፈጣሪ ሆኗል።
በዚህ በጀት አመት ያለው የክፍያ ሚዛን ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት የከፈለችው በእጅጉ እንደሚበዛ የሚያሳይ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም(UNDP) መጋቢት ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ የመጀመርያ አምስት ወራት የክፍያ ሚዛኗ የ5.2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ጉድለት እንዳለበት ያሳያል።
በዓለማቀፍ ደረጃ የተከሰተው የአቅርቦት መስተጓጎል እንዲሁም የሰሜኑ ጦርነት ያስከተለው ጫና ተደማምረው የፈጠሩት የውጭ ምንዛሬ እጥረት የዶላር ኮሚሽኑን ገበያ እንዳደራው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ይናገራሉ።
ከጥቂት ወራት በፊት የውጭ ምንዛሬ ፈላጊዎች ለአንድ አሜሪካ ዶላር ይጠየቁ የነበረው ኮሚሽን 16 ብር አካባቢ ነበር። ባለሙያዎች እንደሚሉት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚጠየቀው ኮሚሽን በዚህ ደረጃ ጭማሬን ማሳየቱ የገቢ እቃዎችን በማስወደድ ተጨማሪ የዋጋ ንረትን ማስከተሉ አይቀርም።
መንግስት ቀድሞም እየተከተለ ያለው ብርን በፍጥረት የማዳከም የምንዛሬ ፖሊሲ ከፖለቲካ ቀውሱ እና ከአለም አቀፍ የአቅርቦት መስተጓጎል ጋር ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን አድርጎታል።
ከባንክ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ፍቃድ ውጭ ማለትም የውጭ ምንዛሬ ያላቸው ነጋዴዎች መሰረታዊ ቁሶችን በፍራንኮ ቫሎታ እንዲያስገቡ ከተፈቀደም በኋላ በመሰረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ ላይ የሚታይ ለውጥ አልመጣም። የሚያዝያ ወር የማእከላዊ ስታቲስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው አጠቃላይ የዋጋ ንረት 34 በመቶ እንዲሁም የምግብ ዋጋ ተለይቶ ሲታይም 42 በመቶ ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]