ዋዜማ- “ የጉራጌን ህዝብ እየደረሰበት ካለው አስተዳደራዊ በደል እና ስጋት ለመታደግ” መደራጀት አስፈልጎኛል ያለ ብሄረተኛ ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲ ይፋ ሊደረግ ነው ።
”ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ” የሚል ስያሜን የያዘው አደረጃጀት እሁድ መጋቢት 03 /2015 ዓ. ም የምስረታ ጉባኤውን በማካሄድ የፖርቲውን የስራ አስፈጻሚዎችንና ማዕከላዊ ኮሚቴዎችን ይመርጣል።
”ጎጎት” የጉራጊኛ ቃል ሲሆን የጉራጌ አባቶች ህዝቡ በ18 መቶ ክፍለ ዘመን ከጥሞት ከነበረው የመበታተን አደጋ ለመውጣት ቃልኪዳን ያሰሩበት ስፍራ መሆኑንና አሁንም ከእንዲህ አይነቱ ስጋት ለመዳን በማሰብ ስያሜው መመረጡን ዋዜማ ሰምታለች።
በተለይ ጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ካነሳ በኋላ እየደረሰበት ያለው እንግልትና አፈና ለፓርቲው መመስረት አንዱ ምክንያት መሆኑን አስተባባሪዎቹ ነግረውናል። ።
ከዚህ በተጨማሪ በፓርቲ መደራጀት ያስፈለገው የጉራጌ ህዝብን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማስጠበቅ ነው።
ፓርቲው የክልልነት ጥያቄን አንድ ጉዳይ አድርጎ የሚመለከተው ሲሆን፤ የጉራጌ ህዝብ በሀገረ መንግስት ግንባታውና በታሪክ የነበረውን ሚና አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚታገል መሆኑን የፖርቲው አደራጅ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ጀሚል ሳኒ ለዋዜማ አስረድተዋል።
የጉራጌን ህዝብ በመላ ሀገሪቱ ተበታትኖ የሚኖር ሆኖ ሳለ በእንዲህ አይነት የብሔር አደረጃጀት ውስጥ ማስገባቱ ለምን አስፈለገ? ስትል ዋዜማ ላነሳችው ጥያቄ
እንዲያውም እስካሁን የጉራጌ ህዝብ ” ኢትዮጰያ” ብቻ እያለ በመዝለቁ በብሔር በተደራጁ የፓለቲካ ሀይሎች ዱላው በርትቶበት ዘልቋል ሲሉ መልሰዋል።
ፓርቲው በመላ ሀገሪቱ ተበትኖ ያለውን የጉራጌ ህዝብ በደሉ እና ድምፁ እንዲሰማ ለማድረግ እሰራለሁ ብሏል።
እስካሁን የጉራጌ ህዝብ ለተቀበለው በደል ሀገራዊ ፓርቲ ነን ብለው ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሳይቀር እዚህ ግባ የሚባል ትኩረት አልተሰጠውም የሚል እምነት አላቸው የፓርቲው አደራጆች። በእነዚህና በሌሎች ምክኒያቶች መደራጀቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ ነግረውናል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዞኑ በክልል የመደራጀትን ምክረ ሀሳብን በ2011 ዓ.ም ማጽደቁ ይታወሳል። ቀጥሎም ነሃሴ 05/2014 ከመንግስት የቀረበለትን በክላስተር የመደራጀት ውሳኔን ውድቅ አድርጓል።
ይህን ተከትሎ በአካባቢው በመንግስት እና የራስ ገዝ መብት በሚጠይቁ ነዋሪዎች መካከል ተከታታይ ግጭቶች የታዩ ሲሆን በቅርቡም በርካታ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል። [ዋዜማ]