መንግስትን በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ እንዲያማክር የተሰየመው 15 አባላት ያሉት የከፍተኛ ባለሙያዎች ቡድን እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ ጠቅላይ ሚንስትሩን አግኝቶ ለማነጋገር አልቻለም ነበር
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በብቸኝነት የሚመሩት የሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ፈተና ተጋርጦበታል
ዋዜማ ራዲዮ- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳስ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ስምንተኛ አመት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚታሰብበት ጊዜ እንደሆነ መንግስት እየተናገረ ነው።የግድቡ ግንባታ በውስብስብ ሙስና ውስጥ አልፎ አሁን ላይ ያለበት ደረጃ ደርሷል። 83 በመቶ የደረሰውን የግድቡን የሲቪል ስራን 25 በመቶ ላይ ካለው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ጋር ለማተካከል የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ከሜቴክ ተነጥቀው ለተለያዩ አለማቀፍ ኩባንያዎች እየተሰጡ ነው።
የህዳሴውን ግድብ ያስጀመሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግድቡ የተጀመረበት ጊዜ ግብጽ ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ የነበረችበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተከትሎም ግንባታው ከተጀመረ ከአንድ አመት ከአምስት ወር አካባቢ ህይወታቸው በማለፉ ከግንባታው መጀመር በሁዋላ ለብዙ ጊዜ የዲፕሎማሲ ውስብስቦሽ ውስጥ ገብተዋል ማለት አይቻልም።
ከመለስ ዜናዊ ቀጥሎ ወደ ስልጣን የመጡት ሀይለማርያም ደሳለኝ ግን በግድቡ ዲፕሎማሲ አያያዝ ላይ ብዙ ሲቸገሩ ይታይ እንደነበር የዋዜማ ራዲዮ የቅርብ ምንጮች ገልጸውልናል።ሀይለማርያም ደሳለኝ በስልጣን በቆዩባቸው ጊዜያት ያልተመከረበት ያልተጠና ውሳኔ በድንገት ያሳልፋሉ ሲሉ በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
ከግድቡ ጋር በተያያዘ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች የከፋ የሚባለው በድንገት ለሚዲያ ቀርበው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ግብጽና ሱዳን የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ከፍለው ግድቡ በሶስቱ ሀገራት ባለቤትነት እንዲያዝ ሀሳብ ያቀርባሉ። ይህን ግብጽና ሱዳን ም ይሰማሉ። ነገሩ በኢትዮጵያ በኩል ባሉ የግድቡን ዲፕሎማሲ የሚከታተሉ ከፍተኛ ሙያተኞችን ያስደነግጣል። ምክንያቱም ግብጽ ግድቡ ላይ የባለቤትነት ድርሻን አገኘች ማለት የግድቡን ግንባታ ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ ለማስኬድ ውሳኔን የማስወሰን እድል እንዲኖራት ስለሚያስችል ነው።
በወቅቱ የሱዳን ሰዎች የሀይለማርያም ደሳለኝ ሀሳብ ሊጠቅማቸው እንደሚችል ቢያስቡም ግብጽን በግድቡ ፕሮጀክት የማስገባት ሀሳብ ጠቃሚ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በወቅቱ የግብጽ መገናኛ ብዙሀን ከህዳሴው ግድብ ሀገራቸው ድርሻ ይኖራታል ብለው ሲዘግቡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ዜናውን የግብጽ የፈጠራ ወሬ ነው በሚል ባለስልጣናትን በማናገር ከካይሮ መገናኛ ብዙሀን የሚነሳውን ወሬ በማስተባበል ተጠምደው ነበር። የነገሩ መነሻ ግን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ነበሩ። ሁዋላ ላይ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሀሳባቸውን ቀይረው ሁሉም ነገር ተዳፍኖ ቀረ።
በሌላ በኩል ከሀይለማርያም ጊዜ አንስቶ እስከ አሁኑ የ አብይ አህመድ አመራር ጊዜ ሊስተካከል ያልቻለ የግድቡ ዲፕሎማሲ አያያዝ አለ። እሱም የግድቡ ግንባታና ከግድቡ ጥናት አካሄድ ጋር የተያያዘ ነው። የሶስቱ ሀገራት መሪዎች በ2007 አ.ም በካርቱም በፈረሙት ስምምነት ላይ ሶስቱ ሀገራት ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ በሚያመጣው ተጽእኖ ላይ ጥናት ያስጠናሉ ይላል። የዚህ አንቀጽ አተረጓጎም ላይ በግብጽና በኢትዮጵያ መሀል ልዩነት አለ። የኢትዮጵያ ባለሙያዎች የግድቡ ግንባታ ማለት ግድቡ እየተገነባ ከስር ከስር ውሀ ይይዛል የሚል ትርጉም እንዳለው ያስባሉ። ግብጾች ደግሞ የግድቡ ግንባታ ማለት አርማታ መሙላት እንጂ ውሀ አሞላሉ አርማታ ተሞልቶ ሲያልቅ ነው በሚል ጊዜ የሚገዙበትን ትርጉም ይሰጡታል። ልዩነቱ ታድያ ግብጽ ለአለማቀፍ ማህበረሰብም የራሳቸውን ትርጉም በድፍረት ማስረዳት ሲችሉ በኢትዮጵያ በልኩል ዝም ማለት መመረጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያላቸው አተያይ ብዙ አወዛጋቢ ነገሮች አሉት። የአብይ አስተዳደር በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክንያት በእጅጉ የዘገየውን የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን የግንባታ ኮንትራት ውሎችን አስተካክሏል። የቀድሞ የኮርፖሬሽኑን አመራሮችን ስለ ግድቡና መዘግየትና ሌሎች ብክነቶች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርገዋል።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ከሁለት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ሲካሄድ ስለሆነው ነገር ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ ግን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በውሀ ዲፕሎማሲው ላይ ያላቸውን አተያይ እንደገና መፈተሽ እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው።
እንደሚታወቀው የአብይ መንግስት የህዳሴው ግድብ በአውሮፓውያኑ 2020 ሀይል ማመንጨት እንደሚጀምርና በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2022 ደግሞ የግድቡን ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጿል።
ታድያ ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፣ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በጠቅላይ ሚኒትር ጽህፈት ቤት በህዳሴው ግድብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሶስትዮሽ ምክክር ያደርጋሉ። ታማኝ ምንጮቻችን እንደነገሩን በዚህ ስብሰባ ላይ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ቆጣ ብለው “ እንዴት እኛን ሳታማክሩ የግድቡን የመጀመርያ የሀይል ማመንጫ ጊዜ እና የአጠቃላይ ግንባታውን ማጠናቀቂያ ጊዜ ትናገራላችሁ ? “ ይሏቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅም ሆነ ሀይል የማመንጨቱ ነገር ኢትዮጵያ የማትደራደርበት የብሄራዊ ጥቅም ጉዳይና ግብጽም በዚህ ጣልቃ መግባት በፍጹም እንደማይገባት አስረግጠው ለአልሲሲ ይነግሯቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ በውይይቱ ላይ ዝምታን መርጠዋል። አብይ አልሲሲን የበለጠ ላለማስቆጣት ይሁን በሌላ ምክንያት ዝምታን መምረጣቸው በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ዘንድ ከፍ ያለ ቅሬታን አስከትሏል። ወትሮ ተደራዳሪዎች ይህ ጉዳይ ሲነሳ ኢትዮጵያ ግንባታውን ለማካሄድ የግብፅ ፈቃድ እንደማያስፈልጋት አስረግጠው በመናገር በሌሎች የድርድር ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት እንዲደረግ ይጠይቁ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለአልሲሲ ቁጣ መሳይ ንግግር ዝምታን መምረጣቸው የግብጹ መሪን አቋም ተቀብለውት ነው ወይ ? ወይስ በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸው የድርድር ልምድ ማነስ ነው ? በዚህ ላይ ያሉ አማካሪዎቻቸው ምንድነው ስራቸው? ጠቅላይ ሚኒስትሩስ ከአማካሪዎቻቸው ጋርስ ግንኙነታቸው እንዴት ነው የሚሉ? ጥያቄዎችን ያስነሳባቸዋል።
አንዲ የዚህ አይነቱ ስህተት ምንጭ ለጉዳዩ ተጠሪ ከሆኑ ዲፕሎማቶችና ተደራዳሪዎች ጋር በቂ ውይይት አለማድረግ ነው ይላሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦች።
መንግስት በህዳሴው ግድብ ዲፕሎማሲ አያያዙ ምክንያት ሀገሪቱን ያለ ክፍያ ለዚህ ስራ ሲያገለግሉ የነበሩ ከፍተኛ ሙያተኞች መሰላቸት ውስጥ መግባታቸውንም ሰምተናል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙርያ የቴክኒክና የዲፕሎማሲ ስራን የሚሰሩ 15 የሚሆኑ ከፍተኛ ሙያተኛ የሆኑ ሰዎች የተካቱበት የብሄራዊ የኤክስፐርቶች ፓናል አለ። የዚህ ፓናል አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደቀድሞ መሪዎች እንዲያናግሯቸው ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ምላሽን አላገኙም ነበር ።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚንስትሩ በሕዳሴ ግድብ ላይ ከተለያዩ ተቋማት የቀረቡ ሪፖርቶችን የገመገሙ ሲሆን የግድቡ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥተዋል። ዲፕሎማሲያችን ያለበትን ፈተና የሚመለከት ሌላ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ