ዋዜማ- የአማራና የኦሮሚያ ክልል በሚዋሰኑበት የሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሁለት ፅንፍ የያዙ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑንና በርካቶችም ለመፈናቀል እንደተገደዱ ለዋዜማ ሪፖርተር ተናግረዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን አጠቃላይ የጸጥታ ችግር መኖሩ የሰነበተ ቢሆንም፣ የደራ ወረዳ ግን ከሁሉም የከፋና ሁለት የታጠቁ ኃይሎች ማለትም፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱባቸው ናቸው።
በተለይም በወረዳው ገጠራማ በሆኑት ሰረርኩላና ቱቲንን በመሳሰሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ ዜጎች፣ እንደ ትምህርት እና ጤናን የመሳሰሉ ማኅበራዊ ግልጋሎቶችን ማግኘት ቅንጦት ሆኖብናል ሲሉ ለዋዜማ አስረድተዋል።
የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጆች በስፋት በሰላም በኖሩባቸው ቀበሌዎች፣ በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ ብሔር ተኮርና በወሰን ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ተደጋጋሚ ግጭትን ሲያስተናግድ ቆይቷል ሲሉ የወረዳው ዋና መቀመጫ ጎንዶ መስቀል ከተማ ነዋሪዎች ለዋዜማ ነግረዋታል።
የደራ ወረዳ በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የሚገኝ እንደመሆኑ፣ ከአማራ ክልል ተሻግረው የሚመጡት ታጣቂዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚያደርሱና ንብረት እንደሚያወድሙ ዋዜማ ከነዋሪዎቹ ሰምታለች።
እነዚሁ ታጣቂዎች ረቡዕ ግንቦት 14/2016 ዓ.ም. በሰረርኩላ፣ ቱቲ፣ ብርጄ፣ ሰንቀሌ እንዲሁም አባዶን በመሳሰሉ የገጠር ቀበሌዎች በተመሳሳይ ሰዓት በፈጸሙት ጥቃት በሰው ሕይወትና ለጊዜው ግምቱ ባልታወቀ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የዐይን እማኞች ገልጸዋል።
እነዚህ ስፍራዎች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ላይ ያሉ እንደመሆናቸው፣ ለበርካታ ዓመታት የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውና፣ በዚሁ ምክንያት በሚነሳ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየጊዜው ከቤት ንብረታቸው የሚፈናቀሉበት እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት “ፋኖ ነን” የሚሉት ታጣቂዎቹ በሚፈጽሙት ድርጊት እና በአካባቢው በስፋት የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በሚወስዱት የአጸፋ ጥቃት የተነሳ ሰላማዊው ነዋሪ እየከፈለ ያለው ዋጋ አሳዛኝ ነው ብለውናል።
ታጣቂዎቹ በብዛት መነሻቸውን ከአማራ ክልል ጅሩ፣ ሃሮ ቆኔ፣ ወገሎ ሚካኤል፣ ሃቼ፣ ኩሳዬ እና ጬካ ከተባሉ ስፍራዎች እንደሆነ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። እነዚሁ የታጠቁ ኃይሎች “የደራ ማንነት አስመላሽ ኃይል” የሚል ስያሜ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ ዋዜማ ስምታለች።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች በወረዳው የተለያዩ ስፍራዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚሞክሩበት ወቅት “ እኛ ንጹሃን ዜጎች በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል” ሲሉም ጭንቀታቸውን አጋርተውናል።
በወረዳው እንደ ትምህርትና ጤና ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በታጣቂዎቹ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውና አብዛኞቹ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል። ለአብነትም በወረዳው የትምህርት ሽፋን ከ50 በመቶ በታች መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞኑ ትምህርት መምሪያ ለዋዜማ ገልጿል። አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶችም ዝግ መሆናቸውንና፣ የትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱም ካለው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የተቆራረጠና ተከታታይ ያልሆነ እንደሆነ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስረድቷል።
በአንጻራዊነትም ቢሆን ትምህርት እየተሰጠ ባለባቸው የወረዳው አካባቢዎች ያሉ ብሔራዊ እና ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ፍቼ፣ እንዲሁም ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሄደው እንዲፈተኑ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የትምህርት መምሪያው ገልጿል።
መምሪያውም አክሎም፣ ካለው የጸጥታ ችግር የተነሳ ከወረዳው አመራሮች ጋር በአካል መገናኘት እንደማይችልና የተለያዩ ውይይቶችን በስልክ ብቻ ለማድረግ መገደዱንም። እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ከሆነም በመከላከያ ሰራዊት ታጅበው ወደ ዞኑ በመምጣት ውይይቱን እንደሚያደርጉ፣ ይህም በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ከፍተኛ ጫና እንደፈጠረ መምሪያው አስረድቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱም የታጠቁ ኃይሎች ከመኪና በማስወረድ ከገበያ ስፍራ፣ ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሰርግ እና ለቅሶ ቦታዎች ንጹሃንን አፍኖ በመውሰድ “ይህን ያህል ብር አምጡና እንለቃችኋለን” የሚል ተደጋጋሚ ድርጊት እንደሚፈጸም ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ዋዜማም በጉዳዩ ላይ የወረዳው ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑትን አለባቸው ኃ/ማርያምን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችን ለማነጋገር ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ባለመሳካቱ ሃሳባቸውን ማካተት አልቻለችም። [ዋዜማ]