ዋዜማ- በጥቅምት ወር ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ በመላ ሀገሪቱ ባሉ መንግስታዊ ተቋማት ተግባራዊ ሳይደረግ ሁለተኛው ወር ተገባዷል። ዋዜማ ባደሬችው ማጣራት ደግሞ ቢያንስ የሶስት ተቋማት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ አግኝተዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች ጥቅምት ወር ላይ የደሞዝ ጭማሪ እንደማይከፈላቸው እና ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል ተብለው ነበር።

ሆኖም ከዚያ በኋላም መቼ ሊከፈል እንደሚችል በትክክል እንደማያውቁ እና የኅዳር ወር ደሞዛቸውም ያለጭማሪ እንደተከፈላቸው ለዋዜማ ተናግረዋል። 

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች የተጨመረላቸውን ደሞዝ የሚገልጽ ይፋዊ ደብዳቤ እስካሁን በእጃቸው እንዳልገባ ገልጸው፣ አሁን ላይ ስለጭማሪው ምንም መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚሁ ጋር በተገናኘ በጥበቃ እና መሰል የሙያ ዘርፎች ከአንድ ተቋም በላይ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን በአንድ ተቋም ብቻ የሥራ ውል እንዲኖራቸው እያደረገ መሆኑንም ዋዜማ ሰምታለች። ይህም የደሞዝ ጭማሪ ከመደረጉ በፊት ከተማ አስተዳደሩ በሰራተኞቹ ዙሪያ እያደረገ ካለው የመረጃ ማጥራት ጋር የሚገናኝ ነው መባሉን የነገሩን አንድ ሰራተኛ፣ ኃላፊዎቻችን በቃል ደረጃ የደሞዝ ጭማሪ  በታህሳስ ወር ተግባራዊ ይደረጋል እያሉን ነው ብለዋል። 

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንድ የወረዳ ፋይናንስ ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያ ደግሞ፣ የደሞዝ ጭማሪው ወሬውም ተረስቷል፣ መቼ እንደሚከፈልም እናውቅም ብለውናል። አክለውም፣ ከዞንም ሆነ ከክልል የደሞዝ ጭማሪውን የሚመለከት መመሪያ ለወረዳዎች አለመላኩን ገልጸው፣ ጥቅምት ወር ላይ የሰራተኞችን መረጃ ተጣርቶ ለዞኑ አስተዳደር ተልኮ እንደነበር ነግረውናል። 

በአማራ ክልል በተመሳሳይ ኹሉም የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪውን እስካሁን አላገኙም። በደቡብ እና ሌሎች ክልሎችም እንዲሁ መንግሥት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ አደርገዋለሁ ያለው የደሞዝ ጭማሪ ለተከታታይ ኹለት ወራት አልተከፈላቸውም።   

ሆኖም የሠራተኞቻቸውን መረጃ አጠናቅረው በጨረሱ በጣም ጥቂት በሆኑ የፌደራል ተቋማት የደሞዝ ጭማሪው መከፈሉን ዋዜማ ተረድታለች። ለአብነትም የፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል እንዲሁም የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ተከፍሏቸዋል። ሆኖም ሰራተኞቹ ተጨምሮ የተከፈላቸው ደሞዝ ከነባሩ ደሞዝ ጋር ልዩነት የለውም ማለት ይቻላል በማለት የደሞዝ ጭማሪው አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የሁለት ወራት ውዝፍ ክፍያን ጨምሮ ጭማሪውን በዚህ ሳምንት ተግባራዊ ማድረጉንም ሰምተናል።   

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ በጀቱን ለክልሎች ልከናል በማለት ክፍያ ያልተፈጸመው ክልሎች የሚያጣሩት ነገር ኖሯቸው ሊሆን እንደሚችል ባለፈው ወር ላይ ለዋዜማ ተናግረው ነበር።  ከጥቅምት ጀምሮ ያለውን የደሞዝ ጭማሪም ወደፊት ሊከፍሉ እንደሚችሉም ነበር የገለጹት።

የገንዘብ ሚንስትር አህመድ ሽዴ ከወር በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው ነበር። 

ሚንስትሩ፣ የደመወዝ ጭማሪውን ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ ሚንስቴር እና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኹሉንም ቅድመ ዝግጅቶች አድርገዋል ብለውም ነበር። 

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከአንድ ወር በፊት ለሕዝብ እንደራሴዎች በሰጡት ማብራሪያ ለደሞዝ ጭማሪው 91 ቢሊዮን ብር ስለተመደበ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ማለታቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]