ዋዜማ- መንግሥት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ያለው የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ፣ በዚህ ወር ተግባራዊ አለመሆኑን ዋዜማ ተረድታለች።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ መንግሥት ሠራተኞች በተወሰኑ ወረዳዎች ከሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን እና ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል መባላቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
ቢሮው፣ ለከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ሰራተኞች ጭማሪው የሚከፈልበት ጊዜ የተራዘመው የሰራተኞችን መረጃ ለማደራጀት ጊዜ ስለሚያስፈልግ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል ።
ሆኖም ሰራተኞቹ ቢሮው እስካሁን ምን ያህል የመንግስት ሰራተኛ እንዳለ እና ሌሎች ከደሞዝ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን አያውቅም ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
ሰራተኞቹ እስካሁን የተጨመረላቸውን ደሞዝ የሚገልጽ ይፋዊ ደብዳቤ አልደረሳቸውም።
በተጨማሪም ከተማ አስተዳደሩ አዲስ የመዋቅር ማሻሻያ አደረጃጀት ጥናት አድርገው የብቃት መመዘኛ ፈተና ለሰጡት ተቋማት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪው ይዘገያል መባሉንም ዋዜማ ተገንዝባለች። ጭማሪው የሚዘገየው ተቋማቱ የሰራተኞችን የሥራ ደረጃ ምደባ ገና ስላልጨረሱ ነው ተብሏል።
ከተማ አስተዳደሩ በመጀመሪያው ዙር የብቃት ምዘና ፈተና የተሰጠው ለቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት፣ የሥራ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ፅሕፈት ቤት፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ፅሕፈት ቤት፣ ኅብረት ሥራ ፅሕፈት ቤት እና የመሬት ልማት አስተዳደር ፅሕፈት ቤት መሆኑ ይታወሳል።
ዋዜማ በክልሎች የተወሰኑ ቦታዎች ባደረገችው ማጣራትም፣ የፋይናንስ ተቋማት እስካሁን ስለደሞዝ ጭማሪው የደረሰን መመሪያ የለም በማለት የዚህን ወር ደሞዝ በነባሩ መደብ እንደሚከፍሉ መናገራቸውን ተገንዝባለች።
የፋይናንስ ቢሮዎቹ ደሞዝ ጭማሪው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ያለው ወደፊት ሊከፈል ይችላል የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውም የጠየቅናቸው የመንግሥት ሠራተኞች ነግረውናል።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚኖሩ አንድ የመንግሥት ሰራተኛ ነባሩ የጥቅምት ወር ደሞዝ እንደተከፈላቸው ገልጸው፣ ጭማሪው የሰራተኞች መረጃ ወደ ዞን ተልኮ ክልል ከደረሰ በኋላ ኅዳር ላይ ሊመጣ ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ነግረውናል።
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ በጀቱን ለክልሎች ልከናል በማለት ክፍያ ያልተፈጸመው ክልሎች የሚያጣሩት ነገር ኖሯቸው ሊሆን እንደሚችል ለዋዜማ ተናግረዋል። ከጥቅምት ጀምሮ ያለውን የደሞዝ ጭማሪም ወደፊት ሊከፍሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚንስትር አህመድ ሽዴ ጥቅምት 09/2017 ዓ. ም ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው ነበር።
ሚንስትሩ፣ የደመወዝ ጭማሪውን ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ ሚንስቴር እና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኹሉንም ቅድመ ዝግጅቶች አድርገዋል ብለውም ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ እንደራሴዎች በሰጡት ማብራሪያ ለደሞዝ ጭማሪው 91 ቢሊዮን ብር ስለተመደበ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ማለታቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]