ዋዜማ ራዲዮ- በሕወሓትና በማዕከላዊው መንግስት መካከል ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በአማራና በትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው የወልቃይት ፣ሁመራና ራያ አካባቢዎች በአማራ ክልል ሀይሎች መያዛቸው ይታወቃል።
በነዚሁ አወዛጋቢ አካባቢዎች የራሱን መንግስታዊ መዋቅር ያደራጀው የአማራ ክልል ማህበራዊና የፀጥታ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የአማራ ክልል አንዳንድ ባለስልጣናት አካባቢዎቹ ከዚህ ቀደም በሀይል የተወሰዱበትና ያስመለሳቸው መሆኑን ይናገራሉ።
አካባቢዎች ህወሀት መራሹ መንግስት ህገ መንግስቱም ሳይጸድቅ በህገ ወጥ መንገድ ከአማራ ህዝብ የነጠቃቸውና ; ቀድሞ የአማራ ህዝብ የነበሩ ናቸው ; ህወሀት በህገ ወጥ መንገድ ከወሰዳቸው በሁዋላም በህዝባችን ላይ ሰፊ ጭቆናን ካሳረፈባቸው አካባቢዎች ዋነኞቹ ናቸው በሚልም ዋነኛ የአማራ ተወላጆች የትግል ማጠንጠኛም ነበሩ።
በአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ዕጣ ፈንታ ላይ በአማራ ክልልም ሆነ በፌደራል መንግስቱ በኩል እስካሁን ጥርት ያለ አቋም መያዝ አለመቻሉን ተገንዝበናል። በጉዳዩ ላይ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መካከል የሀሳብ ልዩነቶች እንዳሉ ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። የሀሳብ ልዩነቶቹ መነሻም የአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሳባቸው አካባቢዎች ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ የአካባቢው ነዋሪዎች ከየትኛው ክልል መካለል እንደሚፈልጉ ይወስኑ በሚለውና ; ቦታዎቹ በፊትም በህገ ወጥ መንገድ ነው ከአማራ ህዝብ ላይ የተወሰዱት አሁንም ያለ ምንም ተጨማሪ አካሄድ በአማራ ክልል መተዳደር ይቀጥሉ በሚሉ ሀሳቦች መካከል ነው።
ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ የአካባቢዎቹ እጣ ፈንታ ይወሰን የሚለው አቋም አማራጭ በፌደራሉ መንግስትና እና በጥቂት የአማራ ብልጽግና አባላት መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። በጉዳዩ ላይ ከምን አይነት የተጠቃለለ አቋም ላይ ስለመደረሱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን ህዝበ ውሳኔ ይደረግ ቢባል ራሱ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ የማህበረሰብ አባላት ፍቃደኝነት አጠራጣሪ መሆኑን እንደሚያምኑ ምንጮቻችን ነግረውናል።
ቀድሞ የትግራይ ክልል ያስተዳድራቸው የነበሩት የወልቃይት ፣ሁመራና ራያ አካባቢዎች በመጪው ምርጫ ያልተካተቱ መሆኑን ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወልቃይት ራያና መሰል አካባቢዎች እስከ ቅርብ ወራት በትግራይ ክልል ስር የነበሩ በመሆኑ ትግራይ ክልል ደግሞ በዚህ አመት ምርጫ የማድረግ እቅድ የሌለ መሆኑንም ስምተናል። [ዋዜማ ራዲዮ]