ዋዜማ ራዲዮ- የዩናይትድስቴትስ የውጪ ጉዳይ መስሪያቤት የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ሀላፊ ቲቦር ናጊ እና የሲውዲን የልማት ትብብር (SIDA) ዳይሬክተር ካሪን ዩምቲን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ ያመራሉ።
የአሜሪካው ቲቦር ናጊ ለአስር ቀናት ያህል ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ዕቅድ ይዘዋል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸው በሀገሪቱ በቅርቡ ከመጣው ለውጥ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ። በፀረሽብር ትብብር፣ በንግድና ክፍለ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የውይይት አጀንዳ መያዙን ስምተናል።
የሲውዲን አለማቀፍ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ካሪን ዩምቲን በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማሳደግ በሚረዱ ሀሳቦች ላይ እንደሚወያዩ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ጠቁሟል።
ባለስልጣኗ በህዳር ወር የመጨረሻ ሳምንት በአዲስ አበባ የተዘጋጀ የመገናኛ ብዙሀን የውይይት መድረክ ላይ ይሳተፋሉ።
ውይይቱ የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሀን ሚና በሽግግር ወቅት ምን መሆን አለበት በሚለው ሀሳብ ዙሪያ የጋዜጠኞችንና የሲቪል ማህበረሰቡን ሀሳብ ለማሰባሰብ ያለመ ነው። የስውዲን መንግስት ፎዮ ከተባለ የሚዲያ የአቅም ግንባታ ተቋም ጋር በጋራ ስልጠናውን ማዘጋጀታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ስዊድን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ከሚያደርጉ የልማት አጋሮች አንዷ ስትሆን ባለፉት አመታት ድጋፏን በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ያደረገችበት ወቅት ነበር። አሁን በስዊድን በኩል ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የሀገሪቱ አምባሳደር ቶርቡዩን ፓተርሰን ከቀናት በፊት ተናግረዋል።