ዋዜማ ራዲዮ-የዞን ዘጠኝ ጦማር ፀሃፊ በፍቃዱ ኅይሉ በኮማንድ ፓስቱ እንደሚፈለግ ተነግሮት ዛሬ አርብ ህዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም ባልታወቁ ሁለት ሰዎች ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዷል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በፍቃዱን ለማናገር እንደሚፈልግ ተነግሮት ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ከሚገኛው መኖሪያ ቤቱ ከጠዋቱ አስራ ሁለት ተኩል ገደማ የተወስደው በፍቃዱ በአሁኑ ስዓት ዜሮ ስድስት ፖሊስ ጣቢያ ይገኛል።
በፍቃዱ በሽብር ክስ በሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ተከሶ የነበረ ሲሆን ከአንድ አመት ከስድስት ወር የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ አመፅ በማነሳሳት ክስ ራሱን እንዲከላከል ፍርድ ቤት ወስኖበት ነበር።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የበፍቃዱን ክርክር ከሰማ በኋላ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም በፍቃዱ ከሌሎች የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች (አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣አጥናፍ ብርሃኔ እና ሶሊያና ሽመልስ)ጋር በተመሳሳይ ክስ በድጋሚ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ማክሰኞ ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም የአቃቤህግ ይግባኝ ላይ ብይን ለመስማት ቀጠሮ ተይዞለታል።
በፍቃዱ በሽብር ክስ ተጠርጥሮ በ ሚያዚያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም ታስሮ ከአንድ አመት ከስድስት ወራት እስራት በኋላ ከአገር እንዳይወጣ የፍርድቤት እግድ ተጥሎበት በሃያ ሺህ ብር ዋስ መፈታቱ ይታወሳል።