ዋዜማ ራዲዮ- በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ዘመን የቴሌቭዥን ድራማ አባላት ለቀረፃ ስራ በተሰማሩበት በሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን በክልሉ ፖሊስ ድብደባና እስራት ተፈፅሞብናል ሲሉ ተናገሩ።
የድራማውን የስደት ታሪክ የሚቀርፁት የካሜራ ባለሙያዎችንና ተዋንያንን ጨምሮ በቦታው የነበሩት የቡድኑ አባላት ዓርብ ዕለት ሰኔ 30 አመሻሹን በአራት ፒክ አፕ የተጫኑ 30 ያህል የፖሊስ አባላት ከበው እንደደበደቧቸውና በማያውቁት ቋንቋ ስድብና ማዋከብ እንደደረሱባቸው ተናግረዋል።
“መሳሪያ ተደግኖብን በከፍተኛ ጩኸት በሶማሊኛ ስንዋከብ ምን መመለስ እንዳለብን ግራ ገብቶን ነበር። በአማርኛ ለማስረዳት ስንሞክር እነሱ ለመስማት ፈቀደኛ አልነበሩም” ትላለች ከቡድኑ አባላት አንዷ።
“በወታደር ጫማ ከጉልበቴ ስር ተመታሁ ሌሎችም ወታደሮቹ በያዙት ዱላ ባገኙት ነገር ወንድ ሴት ሳይሉ እየተማቱ በከፍተኛ እንግልት ፒካፕ መኪናቸው ላይ ወረወሩን ……..ወታደሮቹ ፒካፕ መኪና ላይ ከጫኑን በኃላ 12 ኪሜ እርቀትን በ160 የመኪና ፍጥነት በፒስታ መንገድ ላይ እየከነፉ ወደ አንድ ግቢ አስገቡን። ግቢ ውስጥ እንደገባን ከመኪናው ላይ እየጉተቱ ከወረዱን በኃላ የያዘነው እቃ ፊት ለፊት እንድናስቀምጥ ካደረጉን በኃላ በየተራ እያስቆሞ እያመናጨቁ ፈተሹን ወንዶች ለብቻ ሴቶች ለብቻ ካደረጉን በኃላ የመጡት ወታደሮች ሁሉ ከ10 ጊዜ በላይ ቆጠሩን። ይሄ ሁሉ ሲሆን እንድናወራ አልፈቀዱልንም እራሳቸው ይጠይቃሉ እራሳቸው ይመልሳሉ ደግሞ ይጮሀሉ” ብሏል የቡድኑ አባል ታሪኩ ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገፁ።
የሶማሌ ክልል የፀጥታ ባለስልጣናት በስልክ ስለቡድኑ ከሌላ አካል ካረጋገጡ በኋላ እንደለቀቋቸው አባላቱ ተናግረዋል።
“ከድሬዳዋ አስተዳደር የተፃፈ ደብዳቤና ሌሎች መረጃዎችን ለማሳየት እንኳን ጊዜ አልስጡንም፣ እኔ ፀሎቴ የያዙትን መሳሪያ እንዳይተኩሱብን ነበር” ከአባላቱ ሌላዋ።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ቢሮ ተፈጠረ የተባለው ችግር ተራና ለሚዲያ የሚበቃ እንዳልሆነ ለዚህም ምላሽ መስጠት እንደማይፈልግ በቃል አቀባዩ በኩል ለዋዜማ ገልጿል።
“ማንም ቢሆን ተደብቆ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ለማድረግ ወደ ክልላችን ቢገባ ከዚህ የባሰ ችግር እንደሚገጥመውና ያለ ፌደራል መንግስት ወይም የክልሉ ፕሬዝዳንት ሳያውቁ ሚዲያ ወደ ክልሉ መግባት አይችልም” ብለዋል በማሳረጊያቸው።
ዘመን ድራማ ያላፉትን ወራት በቴሌቭዥን በመቅረብ ላይ ያለ አበበ ባልቻ ፣ስዩም ተፈራ ፣ሰለሞን ቦጋለና ዘውዱ አበጋዝን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ተዋንያንን ያካተተ ተከታታይ ድራማ ነው።