ዋዜማ ራዲዮ- ባለፉት ዓመታት ለገቢና ለወጪ ንግድ አገልግሎት በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ሲወሰዱ የነበሩና ተመጣጣኝ ምርት ወደ ሀገር ቤት ያላመጡ እንዲሁም ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውን ምርቶች ወደ ውጪ ልከው ገንዘቡን ወደ ሀገርቤት ያልመለሱ 240 ድርጅቶች ዝርዝር መዘጋጀቱን ከብሔራዊ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ህግ መሰረት የትኛውም አስመጪ ከየትኛውም ንግድ ባንኮች በተፈቀደለት የውጭ ምንዛሬ ተመጣጣኝ ምርትን ካላስገባ ሌሎች ተጠያቂነቶች እንዳሉበት ሆነው ላስወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመጣጣኝ ምርት ካላስገባ በድጋሚ ምንም አይነት ምንዛሬ አይፈቀድለትም ፣ ምርትም መላክም አይችልም። ብሄራዊ ባንክም እንዲህ አይነት ችግር የተገኘባቸው ነጋዴዎች ምንዛሬን ከየትኛውም ባንክ እንዳያገኙ የማድረግ ስልጣን አለው።


ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው ግን ይህን አሰራር በጣሰ መልኩ በርካታ ነጋዴዎች እንደልብ የውጭ ምንዛሬ ሲፈቀድላቸው ነበር።
ባለፉት አስራ አራት ዓመታት በርካታ አስመጪዎች የተለያዩ ምርቶችን እንዲያስመጡ ከተለያዩ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶላቸው ነገር ግን ምርቱን ሳያስመጡ እንዲሁም ምርት ልከው ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬን ሀገር ውስጥ ሳያስገቡ በመንግስት በተደረገ ጫና ከብሄራዊ ባንክ እገዳቸው ተነስቶላቸው ተጨማሪ ምንዛሪ መውሰዳቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


ከባለስልጣናት ጋር በነበራቸው የጥቅም ትስስር እና የልማት ፕሮጀክቶችን ከለላ በማድረግ እንዲሁም በሀገሪቱ በአቅርቦት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረግ ጥረት የመፍትሄ አካል ሆነው በመቅረብ ከባንኮች ያለገደብ ምንዛሪ ሲወስዱ የነበሩ ድርጅቶች በርካታ ናቸው።


እነዚህን ድርጅቶች ተጠያቂ ለማድረግ በተሞከረባቸው ጊዜያት በአድማ የሸቀጥ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ ፖለቲከኞችን ከለላ በማድረግ የፋይናንስ ተቋማት ተገቢውን እርምጃ እንዳይቀስዱ ሲያደርጉ እንደነበረም ስለ ጥናቱ ከሚያውቁ ባለሙያዎች ነግረውናል።


በዚህ ድርጊት ውስጥ የ240 አስመጪና ላኪዎች ዝርዝር የተካተተ ሲሆን ዋርካ ትሬዲንግ የተባለ ሰሊጥ ላኪ ኩባንያ ፣ አብዱል ሰመድ ቡና ላኪ ምርቶችን በላኩ ቁጥር በትንሹ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሀገር ውስጥ የማያመጡ መሆናቸው ታውቋል።


በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ፣ መሰቦ ቢውልዲንግ ማቴሪያል ፣ አስገዶም አብርሀ እና ኤዜድ ፒኤልሲ እንዲሁም ጎላጎል ትሬዲንግ ብረትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በተለያየ ጊዜ ለማምጣት ምንዛሬ ተፈቅዶላቸው ነገር ግን ምርቶቹ መምጣታቸው ሳይረጋገጥ እንደገና የውጭ ምንዛሬ ተጠቃሚ ሆነዋል።


አይካ አዲስና ኢቱር የተባሉት የጨርቃጨርቅ ኩባንያዎች ደግሞ ጥሬ እቃ ለማምጣትና ምርት ሲልኩም ምንዛሬ ማስቀረታቸው በዝርዝሩ ላይ ተጠቅሷል። ሆኖም ሁሉም ኩባንያዎች ለዚህ ተግባራቸው ተመጣጣኝ ርምጃ አልተወሰደባቸወም።
እጅግ ጥቂት ድርጅቶች በኣአስገዳጅ ሁኔታና በመንግስት ፖሊሲ ግትርነት ሳቢያ የወሰዱትን ያህል ምንዛሪ ወይም ሸቀጥ ያላቀረቡ እንዳሉም በዝርዝሩ ተመልክቷል።

መንግስት ይህን ዝርዝር ይዞ ሊወስድ ስለፈለገው እርምጃ የሚታወቅ ነገር የለም።
ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት እስከ አስራ አንድ ቢሊየን ዶላር ህጋዊ ባልሆነ መልኩ ከሀገር ወጥቶ እንዲሸሽ የተደረገባት ሀገር መሆኗን አለማቀፍ የፋይናንስ ወንጀሎች የጥናት ይገልፃል። [ዋዜማ ራዲዮ]