- አቶ ገብረዋሕድ በአጠቃላይ በስርዓቱ ዉስጥ አብረዋቸው ስለቆዩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሐብት መጠን ሲዘረዝሩ ይቆዩና ‹‹እኔ መቼ ሙስና አሳሰረኝ፡፡ የማይሆን ክር ባልመዝ ኖሮ ጫፌን የሚነካኝ እንዳልነበረ ከእኔ በላይ የሚያውቅ አልነበረም፡፡›› ሲሉ በቁጭት እንደሚናገሩ ጽፏል፡፡
- የዉብሸት ታዬ የግዞት ወጎች መጽሐፍ አታሚውም ሆነ አሳታሚውም በዉል አይታወቅም
ዋዜማ ራዲዮ- ከዛሬ አምሰት ዓመታት በፊት ሰኔ 12፣ 2003 ከሁለት ዓመት ሕጻን ልጁ ፊት በካቴና ታስሮ ወደ ማረሚያ ተወረወረ፡፡ ሽብርተኛ በሚልም የ14 ዓመት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ በ2006 ዓ.ም. ‹‹የነጻነት ድምጾች›› የሚል መጽሐፉን ለንባብ አበቃ፡፡ ከ2 ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ደግሞ ትናንት ረፋድ ላይ ‹‹ሞጋች እውነቶች›› የተሰኘውን መጽሐፍ ለአንባቢ አቀረበ፡፡ ጋዜጠኛ ዉብሸት፡፡
የመጽሐፉ ዋጋ 71 ብር መሆኑን የሚገልጽ መረጃ ከሽፋኑ ማግኘት ይቻላል፡፡ ‹‹ሞጋች እውነቶች›› የትኛው ማተሚያ ቤት እንደታተመ የሚገልጽ መረጃ ግን ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጠነከረ ከመጣው አፈና ጋር ተያይዞ ማተሚያ ቤቶች ስማቸው ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው መጽሐፎች ላይ እንዳይገለጽ አጥብቀው ይማጸናሉ፡፡
‹‹ሞጋች እውነቶች›› የቀድሞው የአውራምባ ታይመስ ምክትል ዋና አዘጋጅ የዉብሸት ታዬ የግዞት ወጎች የተሰባሰቡበት ባለ 224 ገጽ መጽሐፍ ሲሆን እንደ አታሚው ሁሉ አሳታሚውም በዉል አይታወቅም፡፡
በመጽሐፉ የሽፋን ምስል ላይ ዶሮና አንበሳ በፍጥጫ ምልክ ሲጮኹ የሚያሳይ ፎቶ የሚታይ ሲሆን ይህንኑ ለማብራራ ይመስላል በመጀመርያው የመጽሐፍ ቅጠል እንዲህ የሚል መግለጫ ሰፍሯል- ‹‹ሁለቱም ቡድናቸውን ይመራሉ፤ ሁለቱም ለቡድናቸው ይፋለማሉ፡፡ አንዱ ጥሮ አዳሪ፣ ሌላው ሰብሮ አዳሪ ናቸው፡፡››
ዉብሸት ታዬ በእስር ሳለ አባቱን ማጣቱ መሪር ሐዘን እንዳደረሰበት ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ ባለቤቱን ብርሃንን ደግሞ ስለጥንካሬዋ አመስግኗታል፡፡ ብርሃን ተስፋዬን ‹‹በግዞት ስባክን ድካሙንና ሰቆቃውን ችላ፣ ሰብአዊ ፍላጎቶቿንና ሌላኛውን መንገድ ትታ ለሆነችልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ (ባንቺ) ብርሃን ምንጊዜም የማይቀየር የማንነት መንፈስ ዉስጥ አገሬን ኢትዮጵያን አያታለሁ፡፡›› ሲል በምስጋና ገጽ ላይ ጽፏል፡፡
ዉብሸት ግዞት ከመሄዱ 2 ዓመት ቀደም ብሎ ከባለቤቱ ያፈራውን ወንድ ልጅን ስም ‹‹ፍትህ›› ሲል ሰይሞታል፡፡ የ2012 የ‹‹ሂውማን ራይትስ ዎች ሄልማን ሃሜት›› እንዲሁም የ2013 የ‹‹ሲኢኤንኤን አፍሪካን ጆርናስት አዋርድ›› አሸናፊ ዉብሸት በመንግሥት ተቋማት ላይ አደጋ ለማድረስ አሲረሀል በሚል ነበር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡ አንድም ከጋዜጠኝነት ሥራው ጋር በተያያዘ የታሠረ ጋዜጠኛ የለም›› የሚለው መንግሥት አያሌ ጋዜጠኞችን በተመሳሳይ ክስ ማሰሩ ይታወቃል፡፡
ይዘት
በዉብሸት መጽሐፉ ጀርባ አጭር አስተያየታቸውን የሰጡት የቀድሞው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ገብሩ አስራት በኢትዮጵያ የሕዝብ ብሶትና ተቃውሞ በርትቶ የፖለቲካ ሁኔታው መስቀለኛ መንገድ ላይ ባለበት ሁኔታ ጋዜጠኛ ዉብሸት ለመፍትሄ ይበጃል ያላቸውን በርካታ የፖለቲካ አቅጣጫዎች በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅቶ ካለበት ዝዋይ ወህኒ ቤት ማቅረቡን አድንቀዋል፡፡ ‹‹…ይህን ማድረጉ ሰዎች በአካል እንዳይንቀሳቀሱ ቢገደቡም ሐሳባቸው የታሰሩበትን አጥርና ጠባቂዎቻቸውን አልፎ ሕዝብ ዘንድ ሊደርስ እንደሚችል አረጋግጦልናል፡፡›› ሲሉም አክለውም፡፡
አቶ ገብሩ ‹‹ዉብሸት በእስር ላይ እያለ ይህን ከቂም በቀል የጸዳና የሰከነ መጽሐፍ በማቅረቡና ከጨለማው ቤት ብርሃን በመፈንጠቁ ደግሜ አመሰግነዋለሁ›› ሲሉም አስተያየታቸውን ይቋጫሉ፡፡
የዉብሸት መጽሐፍ የግዞት ገጠመኞቹን አስታኮ ሥርዓቱን የሚተች ሲሆን ኢህአዴግ የብሔረሰቦችን ታረክ የበዳይና የተበዳይ ታሪክ አድርጎ በማቅረብ ዜጎችን የሚያራርቅ ተግባር እንደሚፈጽመው ይጠቅሳል፡፡
‹‹…ግንኙነታቸውን በሙሉ በአጥፊና በጠፊ የተቃኙ፣ እንደ ገዥ መደብ ሳይሆን እንደ ሕዝብ ተቃርኖ የነበረባቸው በማስመሰል ዙርያዉን የሀሳብ ገደል ከፈጠሩ በኋላ መፍትሄው ደግሞ በእነሱ የስልጣን ዘመን ዘላለማዊነት ላይ የተመሰረተ (ያደርጉታል)፡፡አሁንስ በቃችሁ እንበል፡፡››
ዉብሸት መጽሐፉን በሚጽፍበት ወቅት ተደጋጋሚ ፈተናዎች እንዳጋጠሙት የገለጸ ሲሆን ረቂቆቹን ከማረሚያ ቤት ለማውጣት ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታም ጠቁሟል፤ በተለይም በየሳምንቱ የሚካሄደው ድንገተኛ ፍተሻን እንደ አብነት በመጥቀስ፡፡
‹‹ብዙዉን ጊዜ የምንጽፋቸው ጽሑፎች በድንገት ‹‹ይማረካሉ››፤ ጽሑፎች ከእስር ቤት ከስር ከስር መውጣት ስላለባቸው በሚልኩት ጽሑፍና በሚቀረው መካከል የሀሳብ ክፍተት፣ የሐሳብ ያለመያያዝ የስሜት መዋዥቅ ይከተላል፡፡ ጽሑፉን ለአሳታሚዎች የሚወስደው ፖሊስ ‹‹በቀደም የላከኝ ጽሑፍ እኮ ባለቤቴ ሳታውቅ ከልብሴ ጋር አብራ አጠበችውው፡፡›› ብሎ ኩም ያደርጋል፡፡››
ዉብሸት ፈተናውን ካስረዳ በኋላ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ይህ ጽሑፍ የተጻፈው በድብብቆሽ፣ በደብዛው የብርሃን ጥላ ዉስጥ ነው፡፡ ሆኖም በጠራ አስተሳሰብና ግልጽ አላማ ነው፡፡››
የእስር ቤት ተረኮች
‹‹የደርግ ዉርስ›› በሚለው ንኡስ ክፍል ማጎርያው ዉስጥ በሚደርስባቸው ድብደባ በጆሯቸው ላይ የመስማት ችግር የተፈጠረባቸውን የአንድነቱን ናትናኤል መኮንንና የመኢዴፓን አበበ ቀስቶን ጠቅሷል፡፡ ኢህኤዴግ ከደርግ የወረሳቸውን ጨለማ ቤቶች በተለይም 8 ቁጥር ምርመራ ክፍል ‹‹ከደርግ የተወረሰ ቅርስ›› ሲል ይገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ ፍራሽ ከማዘርጋት ያለፈ ስፋት የሌላቸውና ፍጹም ጨለማ ሲሆን መርማሪዎች ሊቋቋሙት የማይቸሉት ሕመም ይፈጥራሉ›› ሲል ያብራራና የዛሬዎቹ መሪዎች ደርግን ጨፍጫፊ አድርገው እኛ እንሻላለን የማለት ሞራል እንደሌላቸው ይሞግታል፡፡
‹‹እኩይ ድርጊት በመልካም ካልተተካ የግፍ መጠንን እያሰሉ ራስን ማመጻደቅ ለመጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ያጋልጣል›› ሲልም ዉብሸት ሐሳቡን ያጠናክራል፡፡
ዉብሸት በዚህ መጽሐፉ የተለያዩ የእስር ቤቶቹን ዞኖች ከዘረዘረ በኋላ ዋይታ ስለሚባለው ክፍል ዘለግ ያለ ማብራሪያን ሰጥቷል፤
‹‹ዋይታ›› ተብሎ የሚታወቀው ልዩ ጥበቃ የሚደረግበት ጭለማ ቤት ሲሆን የሚገኘውም በእስር ቤቱ ኃላፊ ቢሮና በሴቶች ዞን መካከል ላይ ነው፡፡ አንደኛው ክፍል ሶስት ትናንሽ ቤቶች ያሉበት ሲሆን ዉብሸት ለኩላሊት ሕክምና ከዝዋይ በሪፈር በመጣበት ወቅት ቆይታ አድርጎበታል፡፡ ምንም እንኳ ሕክምናው እንዳይሰው አለቆች በመጨረሻ የከለከሉት ቢሆንም፡፡
‹‹ዋይታ›› ቀደም ሲል የደህንነት ሚኒስትር የነበሩትን የአቶ ክንፈ ገብረ መድህንን የገደለው ሻለቃ ፀሐዬ የነበረበት ቦታ ሲሆን በኋላ ደግሞ ብርቱካን ሚደቅሳ ለሁለት ዓመት የታጎረችበት ግቢ ነው፡፡ ‹‹እኔ ስመጣ በዉስጡ የነበሩት በኦነግ አመራርነት ተከሶ እድሜ ልክ የተፈረደበት ኢንጂነር መስፍን አበበና አቶ ገብረ ዋህድ ናቸው፡፡›› ይላል ዉብሸት፡፡ ‹‹ሌላው የኦነግ ተጠርጣሪ ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳ በሌላ ክፍል ብቻውን ለአመታት ተዘግቶበት ከቆየ በኋላ ራሱን ገደለ ተብሏል›› ሲልም ‹‹ዋይታ›› ስለሚባለው ሥፍራ መረጃ ይጨምርልናል፡፡
ዉብሸት ዋይታ ግቢ ዉስጥ አግኝቶት ወዳጅ ሳለደረገው እስረኛ የጉምሩኩ ገብረዋእድ የሚያዝናኑ ጥቂት አንቀጾችን በዚህ መጽሐፉ አካቷቸዋል፡፡
‹‹ዋይታ ዉስጥ ያገኘኋቸው ሁለት እስረኞች ቆይታዬን የተዋበ እንዳደረጉልኝ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡›› የሚለው ዉብሸት ‹‹አቶ ገብረዋሕድ በርካታ የሙስና ክሶች ቀርበውበት፣ በመቶ የሚቆጠሩ ምስክሮች ሳምንቱን ሙሉ የሚደመጡበትን ችሎት ሲጋተር ዉሎ ማታ ላይ የሚመጣ ‹‹በችሎት ላይ ወይ ምስክሮቹን ወይ አቃቤ ሕጉን ካላበሳጫሁ የተከራከርኩ አይመስለኝም›› የሚል በዚህም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው እስረኛ ነው፡፡›› ነው ሲል የቀድሞውን የጉምሩክ ከፍተኛ ሹም ይገልጻቸዋል፡፡
አቶ ገብረዋሕድ የፍትህ አካላትን ቢያበሳጭም፣ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም የሚሰጡት ማስጠንቀቂያዎች እንደማይተገበሩ ዉብሸት ይናገራል፡፡ ምክንያቱን ሲገልጽም ‹‹ አቶ ገብረዋሕድ ማስጠንቀቂያን እንተግብር ሲሉ እንደዚህ ከሆነ ክርክሩን እተወዋለሁ፣ የፈለጋችሁትን ፍረዱ›› ስለሚልና እነርሱ ደግሞ ጉዳዩን የፖለቲካ መጠላለፍ ያመጣው ጦስ ሳይሆን የፍትህ ጉዳይ ብቻ እንዲመስል ስለሚጠነቀቅ የአቶ ገብረዋሕድ ‹‹ክርክሩን እተዋለሁ፣ የፈለጋችሁትን ፍረዱ‹‹ ዛቻ ታሸብራቸው እንደነበር ማታ ማታ ይነግረኝ ነበር፡፡›› ሲል ያብራራል፡፡ አቶ ገብረዋሕድ ስለእነርሱ የሚገልጸው ‹‹በደንብ እንተዋወቃለንኮ›› በሚል ነው፡፡
‹‹ስለ አቶ ገዋህድ የቱን አንስቼ የቱን እንደምተው ይቸግረኛል፡፡›› የሚለው ዉብሸት በቆይታቸው በወዳጅነት የተጫወቷቸውን ግላዊ ጉዳዮች የማንሳት መብት እንደሌለው ጠቅሶ ይህም የሆነው ‹‹የሞራል፣ የእምነትና የእውነት ብዙ ጥያቄዎች›› ስላሉበት ነው ሲል በደምሳሳው ያልፈዋል፡፡
ኾኖም ሰውየው በአጠቃላይ በስርዓቱ ዉስጥ አብረዋቸው ስለቆዩት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሐብት መጠን ሲዘረዝሩ ይቆዩና ‹‹እኔ መቼ ሙስና አሳሰረኝ፡፡ የማይሆን ክር ባልመዝ ኖሮ ጫፌን የሚነካኝ እንዳልነበረ ከእኔ በላይ የሚያውቅ አልነበረም፡፡›› ሲሉ በቁጭት እንደሚናገሩ ጽፏል፡፡ ‹‹የፈሰሰ ዉኃ አይታፈስ የሆነባቸው ይመስላል፡፡›› ሲልም አስተያየቱን ያክላል፡፡
ዉብሸት አቶ ገብረዋሕድ በገንዘብ ላይ ያላቸውን አመለካከት ሳቅን በሚያጭር መንፈስ አስፍሮታል፡፡
‹‹አቶ ገብረዋህድ ፊት ስለ መቶ ሺዎች ካወራችሀ ፊታቸውን ወደ ግድግዳ ያዞራሉ፡፡ ጆሯቸውን ሺዎች በሚሉት መናኛ ቁጥር ማወክ አይፈልጉም፡፡ እኔና ኢንጂነር መስፍን እንጠቃቀስና ስለ ሃምሳና መቶ ሚሊዮን ብር ፕሮጀክቶች እናነሳለን‹‹ ያኔ ትንሽ ጆሮ ይሰጡናል›› ይላል፡፡
‹‹ጓደኞቼ መጥተው የሻይ የሰጡኝ ቀን ‹‹በሉ ዛሬ ለስላሳ ጋባዥ እኔ ነኝ፣ አምስት መቶ ብር አግኝቻለሁ›› ካልኩ ‹‹እዚያ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ቁጥር አያስተምሯችሁም እንዴ፣ ዉቤ?›› ሲሉ ሸንቆጥ ያደርጉኛል፡፡ አንድ ቀን ግን ይህ አባባላቸው የምራቸው እንደሆነ የሚያሳይ ክስተት ተፈጠረ፡፡››ሲል ክስተቱ እሳቸው እንደታላቅ ሊመክሩት ሲሉ የተናገሩትን አስቀምጧል፡፡
‹‹ዉቤ ስትወጣ ሁሉን ነገር ትተህ ቢዝነስ ላይ ተሰማራና ቤተሰብህን እርዳ›› ይሉኛል፡፡
‹‹አቶ ገብረዋሕድ፣ ሃሳቡንስ እንደ ሀሳብ ልቀበለው፡፡ ግን ቢዝነስ ሲባል እኮ የገንዘብ አቅምም ይጠይቃል›› ያቋርጡኛል፡፡
‹‹ዉቤ! በትንሹ ጀምር፡፡ ሱሉልታ ላይ በሶስት ሚሊዮን ብር ቦታ ግዛ፡፡ አምስት ሚሊዮን ብር መጠባበቂያ ባንክ አስቀምጥና በአምስት ሚሊዮን ብር ተንቀሳቀስ…››
‹‹እና እነዚህ (የአቶ ገብረዋሕድ) ቃላት እስካሁን ጆሮዬ ላይ ያቃጭላሉ፡፡›› ሲል ጽፏል
‹‹ከነዚህ አባባሎች ጀርባ አንድ ትልቅ ምስጢር አለ›› የሚለው ዉብሸት ‹‹ለምን እየታሰርን፣ ለምን በየጎዳነው እንደምንገደል፣ ለምን ስልጣን ወይም ሞት እየተባለ እንዳለ አሳባቂ አባባሎች ናቸው፡፡ ሲል ምልከታውን ያስቀምጣል፡፡
ስለ አቶ ገብረዋሕድ በተረከበት የመጽሐፉ ክፍል ዉብሸት ሰውየው በተደጋጋሚ ‹‹መለስ በሕይወት ቢኖር አንነካም ነበር›› እያሉ እንደሚቆጩ ጽፏል፡፡