ዋዜማ ራዲዮ- የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት እና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅርቃር ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ሰሞኑን የሀገሪቱ በርካታ አካባቢዎች በመጠነ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲናጡ ሰንብተዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፎች ከድሮው በተለየ በተመሳሳይ ዕለት በሁለቱም ትላልቅ ክልሎች ማለትም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ብዙ ከተሞች ተካሂደዋል፡፡ ፀጥታ ኃይሎች በወሰዷቸው የጭፍለቃ ዕርምጃዎች በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፤ ንብረትም ወድሟል፡፡
መንግስት ግን ዛሬም የውጭ ኃይሎችን ተጠያቂ ከማድረግ እና ጥያቄዎቹን ወደ መልካም አስተዳደር ዕጦት አውርዶ ከማቃለል አልቦዘነም፡፡
ቻላቸው ታደሰ ያዘጋጀውን ዝርዝር ዘገባ እነሆ ያድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ
በኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ላይ እየተነሱ ያሉት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተከታታይ እየሆኑ ነው፡፡ በጅኦግራፊያዊ ሽፋናቸውም ሆነ በብሄር ስብጥራቸው መጠነ-ሰፊ መሆን ጀምረዋል፡፡ ተቃውሞዎቹ በፖለቲካ ፓርቲ ያልተጠሩ በተራው ህዝብ ተነሳሽነት የተካሄዱ ናቸው፡፡ ሰሞኑን በሁለቱ ትላልቅ ክልሎች በተመሳሳይ ዕለት መጠነ-ሰፊ እና ግብታዊ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸው ያልተለመደ ነበር፡፡ የጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ የኦሮሞ ብሄርን እና የሙስሊሞችን ጥያቄዎች ማካተቱም ሁሉን ዓቀፍ ጥያቄ ብቅ እያለ መሆኑን ያሳያል፡፡
በህዝባዊ ተቃውሞዎቹ የሚነሱት አጀንዳዎች መንግስት እንደሚለው የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሳይሆኑ መዋቅራዊ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች መሆናቸው እየታየ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ኢህአዴግ የቆመበትን ብሄር-ተኮር ፖለቲካ መሰረትም የሚገዳደሩ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ በይዘታቸው ከሙስና፣ አስተዳደራዊ አከላለል፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መገፋት፣ ሃብት ባለቤትነት እና ክፍፍል፣ የስርዓቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሰረት የሆነው መሬት ባለቤትነት እና ብሄር ማንነትን ያካተቱት ስለሆኑ መዋቅራዊ ናቸው፤ መፈታትም የሚችሉት በመዋቅራዊ መፍትሄ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ባለፉት ዓመታት የህዝብ ጥያቄዎች በየጊዜው ሲቆለሉ እና ሲንከባለሉ ቆዩ እንጂ መንግስት አንዳቸውንም ለመፍታት አወንታዊ ዕርምጃ ሊወስድ አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ አንጋፋ ምሁራን ሀገሪቱ ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ እያመራች መሆኗን ማስጠንቀቅ ከጀመሩ ቢሰነባቱም ኢህአዴግ ግን እዚህም እዚያም በፈረቃ የሚነሱ ተቃውሞዎችን መቆጣጠር እንደሚችል የተማመነ ይመስላል፡፡ ከውይይት ይልቅ ኃይል መጠቀምንም አዋጭ ስልቱ አድርጎ ቀጥሎበታል፡፡ የኦሮሚያው ህዝባዊ አመፅ በመንግስታዊ እና ፓርቲ መዋቅሩ መኮላሸቱን ቢያሳይም ገዥው ግንባር ለስንጠቃ አለመጋለጡን ግን ጥንካሬ አድርጎ ያየው ይመስላል፡፡
ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚንስትሩ በኦሮሚያው ህዝባዊ አመፅ “የውጭ ኃይል ተጠያቂ ማድረግ ማቆም አለብን” ብለው ነበር፡፡ መንግስታቸውም ብሶቶቹ በመልካም አስተዳደር ዕጦት የተፈጠሩ መሆናቸውን እንቅበላለን፣ በአስቸኳይም እንፈታለን ሲል ከርሟል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጠነከረ የመጣውን የወልቃይት ህዝብ ማንነት ጥያቄም ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ለማያያዝ ሞክሯል፡፡ ተቃውሞው አድማሱን ሲያሰፋ ግን ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ያልቻለው ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ከውጫዊ ኃይሎች ሴራ ጋር ወደማያያዝ ተመልሷል፡፡ በተደጋጋሚ እየታየ ያለው ዕውነታ መንግስት በብልጣብልጥነት ጊዜ ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ለየትኛውም ህዝባዊ ጥያቄ የሰከነ ዘላቂ ፖለቲካዊ እና ህጋዊ ምላሽ መስጠት አለመፈለጉ እና አለመቻሉ ነው፡፡
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ለህዝባዊ ጥያቄ አያያዝ፣ ለግጭት ማስወገጃ ወይም ቀውስ መፍቻ የሚሆን ግልፅ ስትራቴጂ የለውም፡፡ አፋጣኝ አስተዳደራዊ ምላሽ የሚሰጡ ሲቪል ህገ መንግስታዊ እና አስተዳደራዊ ተቋማቱም መፍትሄ ሲሰጡ አይታዩም፡፡ መንግስት ከምንጊዜውም በበለጠ ህዝባዊ ጥያቄዎችን በእሳት አደጋ ስልት ወይም ወታደራዊ ኃይል ነው እያስተናገደ ያለው፡፡ የሰሞኑ ኃይል የተሞላበት ጭፍለቃው የሚያሳየውመም በቅርቡ ለህዝብ ያቀረበው ይቅርታ ከልብ አለመሆኑን ነው፡፡
ህገ መንግስቱ እና ፌደራላዊ ስርዓቱ የቆመበት አንዱ ምሰሶ የሆነውን ብሄር ማንነት ኢህአዴግ ለራሱ ጥቅም ሲመቸው ያንቆለጳጵሰዋል፤ ህዝቡ መጠነ-ሰፊ ጥያቄ ሲያነሳ ግን የህዝቦችን አንድነት የሚንድ ህገ ወጥ ጥያቄ አስመስሎ ያጥላለዋል፡፡ የወልቃይ ህዝብ አማራ ማንነት ጥያቄ የተነሳበት ትግራይ ክልል አዲስ ካልሆነበት በስተቀር ተመሳሳይ ጥያቄዎች በደበብ ክልል በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ግን በአንፃራዊነት በሰላማዊ መንገድ የፈታው የስልጤን ማንነት ጥያቄ ብቻ ነው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጠንክሮ የመጣው የወልቃይት ጥያቄም ቢሆን አስተዳደራዊ አከላለልን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የማንነት ጥያቄም ጭምር ነው፡፡ ኮሚቴው “ህዝባችን በስነ ልቦናው፣ አለባበሱ፣ ለቅሶ እና ሰርግ ስነ ስርዓተ የአማራ ብሄር አካል ሆኖ ሳለ ትግሬኛ ቋንቋ ስለተናገረ ብቻ በብሄሩ “ትግሬ ነህ” መባሉ ህገመንግስታዊ አይደለም” በሚሉበት ሁኔታ ጥያቄው አስተዳደራዊ ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ “ስነ ልቦናችን በፈቅደው አማርኛ ቋንቋ ትምህርት መማር እና ዳኝነትም ማግኘት እንፈልጋለን” የሚል ጥያቄ መሰረታዊ ህግ መንግስታዊ ጥያቄ እንጂ ወደ አስተዳደራዊ ጥያቄ የሚገፋ ተራ ጥያቄ አይሆንም፡፡
በርግጥ የወልቃይት ማንነት ጥያቄ በዋናነት በትግራይ ክልል ውስጥ የተነሳ ጥያቄ ነው፡፡ ሌላውን ትተን የማንነት ጥያቄ መሆኑ ብቻ ግምት ውስጥ ቢገባ ግን ጥያቄው አጎራባቹን የአማራ ክልል ህዝብም የሚመለከት መሆኑ አይካድም፡፡ ለዚሀም ይመስላል ትግራይ ክልል ተገቢውን ምላሽ እንዳጣ የሚገልፀው ተሟጋች ኮሚቴ ሰሜን ጎንደርን ዋነኛው ማዕከል ያደረገው፡፡
ከህገ መንግስቱ አንፃር ከታየ የወልቃይት ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በቀጥታ ፌደሬሽን ምክር ቤትን ይመለከታል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሃላፊዎች ግን “እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ለምክር ቤቱ ከመቅረባቸው በፊት መጀመሪያ በየክልላቸው ያለውን መዋቅር አሟጠው መጠቀም አለባቸው” የሚል ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተው እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠዋል፡፡ ችግሩ ግን በክልሎች እንዲህ ዓይነት ግዙፍ ህገ መንግስታዊ ጥያቄን በገለልተኝነት ማስተናገድ የሚችሉ ህገ መንግስታዊ ተቋማት አለመኖራቸው ነው፡፡ ስለሆነም የወልቃይት ህዝብ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎችም ከትግራይ ክልላዊ ምክር ቤት ወይም ፕሬዝዳንቱ ፅህፈት ቤት ብቻ መፍትሄ ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡ ይህ አሰራር ጥያቄውን ለፖለቲካዊ ተፅዕኖ እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡ አንድ ጥያቄ ቅራቢ ህዝብ ክልላዊ መዋቅሮችን አሟጦ መጠቀሙን ፌደሬሽን ምክር ቤት አምኖ መቼ ጥያቄውን ማስተናገድ እንደሚጀምር ግልፅ ማድረግ አልቻለም፡፡
ፌደሬሽን ምክር ቤት በወልቃይቱ ጥያቄ ሳቢያ ግጭት መከሰቱን፣ ህይወት መጥፋቱን፣ ሲቪል ዜጎች መፈናቀላቸውን እና ንብረትም መውደሙን አስመልክቶ አቤቱታ እየቀረበለትም እንኳ ጉዳዩን የሚያጣራ ልዑክ አዋቅሮ ወደቦታው ሳይልክ ለዕረፍት ተበትኗል፡፡ ጥያቄው የብዙሃኑ ህዝብ ጥያቄ መሆን አለመሆኑን መሬት ላይ ወርዶ አላጣራም፡፡ ለውሳኔ ሃሳብ መነሻ የሚሆን ዳሰሳ ጥናትም አካሂዶ አያውቅም፡፡ አሁን መንግስት በህገ ወጥነት ፈርጆት እያሳደደው ያለው ኮሚቴም መሬት ላይ ምን ያህል የህዝብ ውክልና እንዳለው አላረጋገጠም፡፡ ይህ ሁሉ ምክር ቤቱ ህገ መንገስታዊ ግዴታውን አለመወጣቱን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ወገንተኛነቱንም ጠቋሚ ነው፡፡
መንግስት ዋናውን ጥያቄ ገሸሽ አድርጎ በጎንደር በቅርቡ የተካሄደው ሰልፍ ዕውቅናም ሆነ ባለቤት የሌለው መሆኑን፣ ንብረት ውድመት መከሰቱን፣ የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ ዕውቅና የሌለው መሆኑን፣ ሰልፈኞች ሰንደቅ አላማ መቀየራቸውን እና ህገ መንግስቱን የሚፀረሩ መፈክሮች መሰማታቸውን እያጋነነ ተቃውሞ ሰልፉን ለማጣጣል ሞክሯል፡፡ መንግስት ጆሮ ቢኖረው ኖሮ ግን እነዚህ ጉዳዮች መሰረታዊ ባልሆኑ ነበር፡፡ የጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ ቢያንስ በይፋ ባለቤት አልባ የሆነባቸው ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡ ያለ ማንም ቅስቀሳ ግብታዊ ተቃውሞ ማሰማት መጀመሩን ሊያሳይ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደሞ በፖለቲካ ድርጅት ወይም ጊዚያዊ ኮሚቴ የሚመራ ተቃውሞ ዕውቅና ስለሚነፈገው እና ለጭፍለቃም ስለሚመች ስለሆነም ይሆናል፡፡
የሆነው ሆኖ የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ አለኝ ካለ ጥያቄውን ለማቅረብ ሦስት ህጋዊ አማራጮች አሉት፡፡ አንድም በክልል ደረጃ በትግራይ ክልል ምክር ቤት ውስጥ ባሉ ተወካዮቹ አማካኝነት ማቅረብ ይችላል፡፡ በፌደራል ደረጃ ደሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉ ተወካዮቹ በኩል ማቅረብ መብቱ ነው፡፡ የወልቃይት ህዝብ የትግራይ ብሄር አካል ተደርጎ ስለተቆጠረ በፌደሬሽን ምክር ቤት ተወካይ የለውም፡፡ በሌላ በኩል በምርጫ የወከሉትን ትቶ ጊዜያዊ ተወካዮች መምረጥም መብቱ ነው፡፡ ጥያቄው እየቀረበ ያለውም በዚሁ መንገድ ነው፡፡ በቅርቡ ግን መንግስት ህገ ወጥ እና ውክልና የሌላቸው ያላቸውን ኮሚቴ አባላት ማሳደድ እና ማሰር ጀምሯል፡፡
የትግራይ ክልል መንግስትም ሆነ ፌደሬሽን ምክር ቤት ቀደም ሲል በኮሚቴው ሲቀርቡላቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ሲቀበሉ መቆየታቸው ግን ለኮሚቴው ህጋዊ ዕውቅና መስጠታቸውን ያሳያል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞው ሲበረታ ኮሚቴውን በህገ ወጥነት መወንጀል ተጀመረ፡፡ የትኛውም መንግስታዊ አካል ግን ጥያቄው የቀረበበት አግባብ ምን ግድፈት እንዳለበት ወይም ግድፈቱ እንዴት መስተካከል እንደሚገባው አፍታቶ ሲናገር አልተሰማም፡፡
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በመጠኑም ቢሆን ከአማራ ክልል መንግስት ተለይቶ ንብረት ውድመቱ አንድን ብሄር ዒላማ ያደረገ መሆኑን ፈጥኖ መግለፁ ሌላኛው ሃላፊነት የጎደለው ድርጊቱ አድርገው ያዩት ታዛቢዎች ቀላል አይደሉም፡፡ ብሄር ማንነትን መሰረት ያደረጉ ትንኮሳዎች መኖራቸውን በደፈናው መግለፅን እንደ ሰላማዊ ተቃውሞ መጨፍለቂያ መሳሪያ ለመጠቀም አዝማሚያ እንዳለው ጠቋሚ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በገለልተኛ ወገን ባልተጣሩ ክስተቶች መንግስት ከሳሽም ፈራጅ እየሆነ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ጎንደር ከተማ ላይ ግብታዊ ግዙፍ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዶ አንዳችም ሁከት አለመፈጠሩ ግን የመንግስትን ውንጀላ ባዶ ያስቀረ ሆኖል፡፡
ፌደራል መንግስቱ ከሳምንታት በፊት በጎንደር ከተማ በወሰደው የኃይል ዕርምጃ ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ የክልሉ መንግስት ፌደራል መንገስቱ ሳያማክረው የወሰደው ዕርምጃ መሆኑን አምኗል፡፡ ያም ሆኖ ችግሩ የተፈጠረው ከመናበብ ገድለት ነው ብሎ አቃሎታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ግን ግዙፍ ህገ መንግስታዊ ጥሰት መሆኑን ማንም ይረዳዋል፡፡ ህዝብ ለሚያነሳው ሰላማዊ እና ህጋዊ ጥያቄ ምላሽ የማይሰጠው ፌደራል መንግስት በክልሎች ሰላማዊ ተቃውሞ ሲነሳ ፀጥታ ኃይሎቹን በክልሎች አሰማርቶ በመጨፍለቅ የሚቀድመው የለም፡፡ የትግራይ ክልል የወልቃይት ማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ ጥያቂያቸው በትግራይ ክልላዊ መንግስት እንደተጓተተባቸው ብሎም ዜጎች በተደጋጋሚ መንገላታታቸውን፣ የደረሱበት መጥፋታቸውን፣ ንብረታቸውም መውደሙን ሲገልፁ ግን በክልሉ ላይ አንዳችም ጥያቄ አላነሳም፡፡
በህዝባዊ ተቃውሞዎች በኩል ግን ብቁ አመራር የሚሰጥ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ብቅ አለመኖሩ ዛሬም ያልተፈታ ጉድለት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ህዝባዊ ሰልፎች ተጠናክረው የሚካሄዱት ተቃዋሚ ድርጅቶች በተዳከሙበት ወቅት ላይ መሆኑ ደሞ ክፍተቱን አባብሶታል፡፡ ስለሆነም ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ ግብታዊ ሆነው ለመቀጠል ተገደዋል፡፡ ከህዝባዊ ተቃውሞው የሚወለድ አዲስ አመራር ካለ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡
በጠቅላላው በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው ህዝባዊ ተቃውሞ ምን ዓይነት አዲስ መልክ እንደሚይዝ፣ ተቃውሞው ምን ውጤት እንደሚያመጣ፣ የኃይል ጭፍለቃው በዚሁ ከቀጠለ የሀገሪቱ ዕጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን አሁን መተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡