ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ የኮንደም ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ተከትሎ ለተላላፊ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰቡ አባላትን ለአደጋ ከማጋለጥ አልፎ የሀገሪቱን የኤች አ ይ ቪ ስርጭት ያባብሰዋል የሚል ስጋት አንዣቧል።
ዋዜማ በቅርቡ በአዲስ አበባ በቀን እና በምሽት ከመደበኛ መድሃኒት መደብሮች እስከ ምሽት የአደባባይ ጀብሎዎች ድረስ ባደረገችው የገበያ ዳሰሳ በኮንዶም ላይ እጅግ ከፍ ያለ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን መረዳት ችላለች፡፡
ኮንዶም በብዛት በሚሸጥባቸው መድሃኒት መደብሮች አንድ በውስጡ ሦስት ኮንዶሞችን የሚይዝ እሽግ ከሁለት ወር በፊት ከሦስት ብር እስከ አምስት ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ በተጠናቀረበት ቀን ግን ከ25 ብር እስከ 35 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሆነ ዋዜማ በዳሰሳዋ ተረድታለች። የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤቻይቪ ሥርጭት መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ቢሮ የኮንዶምን ዋጋ መናር እንዳስተዋለ ለዋዜማ አረጋግጧል፡፡
ዋዜማ የኮንዶምን ዋጋ ለማወቅ ዳሰሳ ካደረገችባቸው ቦታዎች መካከል፣ ፒያሳ፣ ቦሌ፣ ቦሌ መድሃኒያለም፣ በብዛት የመንገድ ላይ የምሽት ሴተኛ አዳሪዎች በሚበዙባቸው ዳትሰን ሠፈር፣ ጣይቱ ሆቴል ፊት ለፊት፣ ሲኒማ አምፒር እስከ ራስ መኮንን ድልድይ እስከ ሃያ ሁለት አደባባይ ባሉት ሥፍራዎች፣ አንድ እሽግ ኮንዶም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ቀን ላይ ከሚሸጥበት 25 ብር ወደ 50 ብር ከፍ እንደሚል መታዘብ ተችሏል። እኩለ ሌሊት ላይ ደሞ ዋጋው ወደ 70 ብር ያሻቅባል።
በከተማዋ በብዛት ተጠቃሚ ያላቸው እና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምባቸው የኮንዶም ዓይነቶች ሕይወት ትረስት እና ሰንሴሽን የሚባሉት ናቸው፡፡ ሕይወት ትረስት ከሁለት ወራት በፊት አንዱ እሽግ 3 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ሰንሴሽን ደሞ እንደ ዓይነቱ ከ5 ብር እስከ 10 ብር ይሸጥ እንደነበር ዋዜማ ካነጋገረቻቸው የመድሃኒት መደብር ባላቤቶች ማረጋገጥ ችላለች፡፡
የተሻለ ገቢ ያለው ማኅበረሰብ ይጠቀምብታል የሚባለው እና በመድሃኒት መደብሮች የሚገኘው የታይላድ አገር ምርት የሆነው ዱሬክስ ኮንዶም ነው። ዱሬክስ ከሁለት ወራት በፊት አንዱ እሽግ ከ50 ብር እክ 60 ብር ዋጋ የነበረው ሲሆን፣ ይህ ዘገባ በተጠናቀረበት ሰሞን ግን ዋጋው ከ82 እስከ 90 ብር ደርሶ ነበር።
ለኮንዶም ዋጋ ማሻቀብ ምክንያቱ በአለማቀፍ ደረጃ የተከሰተው አቅርቦት ቀውስ፣ የምንዛሪ ዕጥረትና ኮቪድ ያስከተለው የጤናው ዘርፍ መዛባት እንደሆኑ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በመንግስት በኩል ግን ስለ ችግሩ መንስዔ እስካሁን የተብራራ ነገር የለም።
በኮንዶም ዋጋ መናር ዙሪያ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ዳይሬክተር የሆኑትን ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌን አነጋግረን ነበር። በኢትዮጵያ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ አሁን ባለበት ሁኔታ በቁጥጥር ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለዋዜማ የገለጹት ሲስተር ፈለቀች፣ ይህ ማለት ግን እንዲህ ዓይነቱን ችግር ዝም ብለን ማለፍ አለብን ማለት አይደለም ይላሉ።
“ መንግሥት ዘርፉን መደገፍ አለበት። ሴተኛ አዳሪዎች ባሉባቸው እና ለኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ኮንዶም በነጻ ማቅረብ ችግሩን እንዲሁም ዋነኛ ተጋላጮችን ለመርዳት ያግዛል” ሲሉ ለዋዜማ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተቋሙ በኮንዶም ሥርጭት እና ተደራሽነት ላይ በ2013 ዓ.ም ጥናት እንዳደረገ ለዋዜማ የተናገሩት ሲስተር ፈለቀች፣ ጥናቱ በከፊል ወደ ትግበራ እንደገባ እና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ቢሆን ደሞ የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል። ጥናቱ እንዲጸድቅ ወደ ጤና ሚንስቴር የተመራ ቢሆንም እስካሁን ግን ከሚንስቴሩ ምንም ምላሽ እንደሌለ ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ጤና ሚንስቴር ግን ስለተባለው ስትራቴጂ የማውቀው ነገር የለም ሲል ለዋዜማ ምላሽ ሰጥቷል።
እንደ ሲስተር ፈለቀች አገላለጽ፣ ተጠና የተባለው “የኮንዶም ስትራቴጂ ሰነድ” የሚል ስያሜ ያለው ጥናት፣ ሦስት ስትራቴጂዎችን በውስጡ የያዘ ነው። የመጀመሪያው “ኮንዶም ፍሪ ማርኬት” የተባለ ሲሆን፣ ይህ ስትራቴጂ መንግሥት ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የኮንዶምን ሙሉ ወጪ ሸፍነው ለማኅበረሰቡ በነጻ እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ ነው።
ሁለተኛው “ሶሻል ማርኬቲንግ ስትራቴጂ” የተባለው ደሞ፣ ለወሲብ ተጋላጭ በሆኑ የማኅረሰብ ክፍሎች መኖሪያ አካባቢዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ኮንዶሞችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማሰራጨት እና መቆጣጠርን ይይዛል።
ሦስተኛው የጥናቱ ስትራቴጂ “ኮሜርሻል ማርኬቲንግ ሰትራቴጂ” የተባለው ሲሆን፣ ይህ ስትራቴጂ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ኮንዶምን ከውጪ በማስገባት ለገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ዕድል የሚፈጥር ስትራቴጂ ነው፡፡
የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው የቫይረሱ ሥርጭት ጎልቶ የሚታየው ከ15 እስከ 49 ዓመት እድሜ ክልል ባሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሲሆን፣ በአገር ዓቀፍ ደረጃ የቫይረሱ ሥርጭት መጠን 0.86 በመቶ ነው። ጋምቤላ ክልል በሥርጭት መጠን በ4.13 በመቶ ከአገሪቱ ቀዳሚ ሲሆን፣ ሱማሌ ክልል 0.15 ከመቶ እንዲሁም አዲስ አበባ 3.2 ከመቶ እንደሆነ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡
ግብረ ሰናዩ ቤዛ ፖስተሪቲ እና ልማት ድርጅት ላለፉት 20 ዓመታት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ምክንያት ከማኅበረሰቡ ለተገለሉ ሴቶች ኮንዶም በነጻ ያድላል። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የድርጅቱ የክትትል እና ግምገማ ክፍል ሃላፊ ዘመን ቴዎድሮስ፣ ኮንዶም በብዛት ጥቅም ላይ በሚውልባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ለግብረ ስጋ ግንኙነት ዝግጁ የሆነ የማህበረሰብ ክፍል በሚገኝበት ስፍራ ሁሉ በቀላሉ ሊገኝ የሚገባው እንደሆነ ይገልጣሉ።
ኮንዶም በአዲስ አበባ ጤና ጣቢያዎች በነጻ ለተገልጋዮች እንደሚቀርብ የከተማዋ ጤና ቢሮ ለዋዜማ የገለጸ ሲሆን፣ ዋዜማም ከሦስት በላይ በሚሆኑ የጤና ጣቢያዎች ተዘዋውራ ይህንኑ መረጃ አረጋግጣለች።
የችግሩን መኖር አምኖ የተቀበለው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ እና ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሰጪ ክፍል፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በመንግሥት ደረጃ ክፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል የሚል እምነት እንዳለው ለዋዜማ ተናግሯል። ኮንዶም በነጻ በማደልም ሆነ በመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጎማ ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ማደረስ እንዳልተቻለ የገለጠው ክፍሉ፣ እንደማንኛውም ሸቀጥ በርካታ ባለሃብቶች ተሳትፈውበት መፍትሄ ማምጣት ይሻላል ብሏል።
ዋዜማ ኮንዶምን ከውጪ ከሚያስገቡት ቀዳሚው ከሆነው፣ የወሊድ መቆጣጠሪያን ከሚያስመጣው እና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ከሚሰራው ዲኬቲ ኢትዮጵያ ለዚህ ዘገባ የሚሆን መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት በድርጅቱ ዳተኝነት አልተሳካም። [ዋዜማ ራዲዮ]