One of the insurgent leader Jal Merroo

ዋዜማ ራዲዮ -የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍ ከማናቸውም የኦነግ የፖለቲካ አመራሮች ጋር አብሮ እንደማይሰራ በማስታወቅ ከእንግዲህ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በሀይል ለመፋለም መወሰኑን አስታውቋል።

የወታደራዊ ክንፉ አመራሮች ለዋዜማ እንደገለፁት በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውም ሆነ ማናቸውም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፖለቲካዊ ድርጅት ጋር አብረው መስራት ካቆሙ ወራት ተቆጥረዋል።


ከዚህ በኋላም “የኦሮሞ ህዝብ የታገለለት ዓላማ” ከግቡ እንዲደርስ መንግስትን በሀይል ለመፋለም መወሰናቸውን ወታደራዊ አንጃዎቹ ይገልፃሉ።


በምዕራብ ኦሮምያ ያለው ሽምቅ ተዋጊ ቡድን የሚመራው በጃል መሮ ሲሆን በደቡብ ምዕራብ ኦሮምያ (ቦረናና ጉጂ) ያለውን ክንፍ የሚመራው ደግሞ ጃል ጎልቻ ዳንጌ ነው። በስራቸውም አነስተኛ ቡድኖችን አደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።


የመከላከያ ሰራዊት በነዚህ ሸማቂዎች ላይ ተከታታይ እርምጃ ወስዶ ጉዳት ቢያደርስባቸውም ተዋጊዎቹም በመንግስት ወታደሮች ላይ ተመጣጣኝ ጉዳት አድርሰናል ብለዋል።
አማፅያኑ በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል ተዋጊዎች እንዳላቸው ዋዜማ ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻለችም። በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎችም ምልመላ በማድረግ የተዋጊዎቻቸውን መጠን ለማሳደግ እየሞከሩ መሆኑን ስምተናል።


ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግስት በምዕራብ ኦሮምያ በሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ህይሎች ላይ እርምጃ ወስዶ አካባቢውን መረጋጋቱንና ከሰላማዊ መንገድ ውጪ ለሚመጣ ሀይል የአፀፋ ሀይል እንደሚጠቀም አሳስበዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የፖለቲካ አመራር ራሱ ሁለት ተከፍሎ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ለስልጣን ለመወዳደር እየተዘጋጀ መሆኑን ከሰሞኑ መዘገባችን ይታወሳል። [በጉዳዮ ላይ ዝርዝር መረጃ ከታች በድምፅ ማግኘት ይችላሉ]

https://youtu.be/g6SqvZ5Rwbs