ዋዜማ – መንግስት ወደ ውጪ ለመላክ ካቀደው የሰንዴ ምርት 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል ድርሻ የኦሮሚያ ክልል ነው። ክልሉ የተጣለበትን ኮታ ለማሟላት አርሶ አደሮች ምርታቸውን በርካሽ እንዲሸጡለት እያግባባ ነው። አርሶ አደሮቹ በሀገር ውስጥ ገበያ ከሚሸጥበት ዋጋ ቀንሰው ለመሸጥ ፈቃደኛ አልሆኑም። የኦሮሚያ ክልል መንግስትና አርሶ አደሮቹ አሁንም በውዝግብ ላይ ናቸው። ዋዜማ ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክታዋለች። አንብቡት
ኢትዮጵያ በዚህ አመት ለወጪ ገበያ ለማቅረብ ካቀደችው ስንዴ የኦሮምያ ክልል 3.1 ሚሊየን ኩንታሉን እንዲያቀርብ ይጠበቅበታል።ክልሉም ይህን የተጣለበትን ኮታ ለማሟላት ስንዴ አብቃይ ለሆኑ ዞኖች ኮታ ሲያከፋፍል ፣ ዞኖች ደግሞ ለየወረዳዎች በማከፋፈል ክልሉ የተጣለበትን ኮታ እንዲሰበስቡ ለማድረግ ሲንቀርሳቀስ ሰንብቷል።
በየወረዳው የስንዴ ማሳ ካላቸው አርሶ አደሮች ጋር ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ስብሰባዎች መደረጋቸውን ዋዜማ አረጋግጣለች። የአርሲ ዞን ከ20 በላይ የሚሆኑ የወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊዎችና የአርሶ አደር ተወካዮችን በቅርቡ በአሰላ ከተማ ሰብስቦ እንደነበር ሰምተናል። የየወረዳዎቹ የግብርና አመራሮችና የአርሶ አደር ተወካዮች ደግሞ በየቀበሌው ከአርሶ አደሮች ጋር መክረዋል።
ሌላኛው በስንዴ ምርት የሚታወቀው የባሌ ዞን ደግሞ የምርት ስብሰባ ወቅቱ ከአርሲ ዞን ስለሚዘገይ የምክክር ስብሰባው አሁን እየተካሄደ ነው።
በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ እንደተንፀባረቀው አርሶ አደሮቹ ስንዴውን ለመንግስት ማቅረብ ላይ ቅሬታ ባይኖራቸውም ለእያንዳንዱ ኩንታል ስንዴ የተቀመጠው ዋጋ ላይ ግን ተደጋጋሚ ቅሬታን እያቀረቡ መሆኑን ተገንዝበናል።
ዋዜማ እንደሰማችው ከሆነ እያንዳንዱ አርሶ አደር ለነጋዴዎች አንዱን ኩንታል ስንዴ 3200 ብር እንዲሸጡ ነው የተወሰነባቸው።ነጋዴዎች ደግሞ ለዩኒየኖች ይሄኑ አንድ ኩንታል ስንዴ በ3,330 ብር እንዲያቀርቡ ነው መንግስት ዋጋ የተመነው። ለውጭ ገበያም የማቅረቡ ሂደትና የዋጋ ትመና ከዚህ ሂደት በኋላ የሚመጣ ነው።
ሆኖም አርሶ አደሮቹ ለአንዱ ኩንታል ስንዴ የተቀመጠው ዋጋ የሚያከስረን ነው በማለት ነው ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን አርሶ አደሮቹ ለዋዜማ ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ አርሶ አደር እንደገለጹት “ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ ኩንታል ስንዴን በ4500 ብር ነበር ለነጋዴ የምናስረክበው : እኛ ስንዴ ሽጠን ከገበያ የምንገዛቸው ሌሎች እቃዎች ዋጋቸው ውድ ነው። ከአንድ ኩንታል ላይ 1200 ብር ቀንሳችሁ አቅርቡ መባላችን በፍጹም ተገቢ አይደለም “ ብለዋል።
ሌላኛው የአርሲ ዞን ጢዮ ወረዳ አርሶ አደር እንዲሁ ለዋዜማ ሲያስረዱ ” በ2013/2014 አ.ም የምርት ዘመን ላይ ለአንድ ኩንታል ማዳበሪያ 1500 ብር ነበር የምከፍልው ፣ ለ2014/2015 አ.ም የምርት ዘመን ግን አንድ ኩንታል ማዳበሪያን 5000 ብር ነው የገዛሁት ፣ ታዲያ ለአንድ ኩንታል ማዳበሪያ በአንድ አመት ውስጥ ተጨማሪ 3500 ብር ከፍዬ እንዲሁም ሌሎች የኑሮ ወጪዎች እያሉብኝ አንዱን ኩንታል ስንዴ ከ4500 ብር አውርጄ መሸጥ አያዋጣኝም” ብለዋል።
በተፈጠረው የዋጋ ውዝግብ ሳቢያም በዞኑ ስንዴን እንደልብ አዘዋውሮ መሸጥ ችግር እየሆነ እንደመጣ ያነጋርናቸው አርሶ አደሮች ነግረውናል። ስንዴን በጭነት መኪና ይዞ የሚንቀሳቀስ ካለም “ስንዴን ለመንግስት እንጂ ለገበያ መሸጥ አይቻልም” በሚል እየተወረሰ እንደሆነም ሰምተናል።
በርከት ያለ ምርት ያላቸው አርሶ አደር ቤተሰቦች በቤተሰብ ኮታ ተሰጥቶን መንግስት ባቀረበው ዋጋ ለመንግስት አቅርበን ቀሪውን በገበያ ዋጋ ለነጋዴ እናቅርብ ቢሉም አነስተኛ ምርት የሚያመርቱት አርሶ አደር ቤተሰቦች ደግሞ በቤተሰብ ኮታ ቢሰጥ ያለንን ምርት በሙሉ በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ ስለምንገደድ አያዋጣንም እንዳሉ ከተደረጉ ስብሰባዎች ተረድተናል።
በርካታ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለመያዝ የመረጡ ሲሆን በዚህ ሳቢያ የየወረዳ እና ቀበሌ ጸጥታ አካላት የቤት ለቤት ፍተሻ አድርገን የተደበቀ ስንዴ እናወጣለን እያሉ ማሳሰቢያ እንደሰጡ አረጋግጠናል።
በገቢ ችግር ምክንያት ያላቸውን ምርት መንግስት ባቀረበው የአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ 3200 ያቀረቡ አርሶ አደሮች ቢኖሩም የዚህ የመጨረሻው ተጠቃሚ የሆኑት ግን ነጋዴዎች ሆነዋል ብለውናል ምንጮቻችን። አንዳንድ ነጋዴዎች በኩንታል 3200 ብር የተረከቡትን ስንዴ የተወሰውን ለመንግስት ዩኒየኖች አቅርበው ቀሪውን ከፍተሻ ጣብያ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር አንዱን ኩንታል ስንዴ ወደ ከተሞች አምጥተው ለዱቄት ቤቶች በ5000 ብር እየሸጡ ነው።
ለወጪ ንግድ ይቀርባል በተባለው የስንዴ ዋጋ ምክንያት ከፍተኛ የገበያ መዛባት እየፈጠረ ነው። በአዲስ አበባ የአንድ ኪሎ የዳቦ ዱቄት ዋጋ ከ60 እስከ 70 ብር ደርሷል።
በሀገሪቱ በድርቅ በጦርነትና ግጭት ምክንያት 12 ሚሊየን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ የኦሮምያ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊዎችን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በተለይ የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ሊመልሱልን አልቻሉም። [ዋዜማ]