ዋዜማ- የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የዞን አደረጃጀቱን መልሶ ለማዋቀርና ስያሜውንም ለመቀየር የሚያስችለው ጥናትና ውይይት እያደረገ መሆኑን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
የዚህ የአስተዳደራዊ መዋቅር ማሻሻያ አንድ አካል የሆነው የወረዳና ቀበሌ አደረጃጀት ለውጥ ተጠናቆ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገንዝበናል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወረዳ ደረጃ የነበረውን 28 የጽ/ቤት መዋቅር ወደ 15 ማጠፉንና አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ማዋቀሩን ዋዜማ ካገኘችው ሰነድና ከታማኝ ምንጮቿ ሰምታለች።
በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም በተናጥል የነበሩት ግብርናና አርብቶ አደር፣መሬት አሥተዳደር፣ማኅበራት ማደራጃ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤቶች በምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ስር እንዲመሩ መወሰኑን ዋዜማ ተረድታለች።
በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በተናጥል የነበሩት የጸጥታ እና የሚሊሻ ጽ/ቤቶች አሁን ላይ በአንድ መዋቅር ስር እንዲተዳደሩ መወሰኑን ፣ ቀድሞ ለየብቻ የነበሩት የውሃና ኢነርጂ እንዲሁም ማዕድን ጽ/ቤቶች በአንድ መዋቅር ስር እንዲሆኑ መደረጉን ምንጮቿ ለዋዜማ አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም በተናጥል የነበረው የትራንስፖርት ጽ/ቤትና መንገዶች ባለሥልጣን መዋቅር አሁን ላይ በአንድ ጽ/ቤት ስር መዋቀሩን ዋዜማ ካገኘችው ሰነድ የተመለከተች ሲሆን በተጨማሪም የንግድ፣የኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጽ/ቤቶች በአንድ ጽ/ቤት ስር እንዲመሩ መደረጉን ዋዜማ ሰምታለች።
የሴቶች እና ሕጻናት፣ባሕልና ቱሪዝም፣ሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ እንዲሁም ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤቶች የሕዝብ አደረጃጀት ጉዳይ በሚል በአዲስ ጽ/ቤት ስር እንዲተዳደሩ መወሰኑን ምንጮች ለዋዜማ ጠቁመዋል።
ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት፣ወሳኝ ኩነት እንዲሁም የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤቶች በአዲሱ መዋቅር መሠረት በአሥተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊው ስር እንዲመሩ መወሰኑንም ምንጮች ተናግረዋል።
የዓቃቤ ሕግ፣የፖሊስ፣የትምሕርት፣የጤና፣የገንዘብ፣የገቢዎች እና የአደጋ ስጋት ጽ/ቤቶች በአዲሱ የመዋቅር አሰራር ስር አለመካተታቸውንና ከዚህ ቀደም በነበሩት የተናጥል ጽ/ቤት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ዋዜማ ከደረሳት ሰነድ ተመልክታለች።
በሌላ በኩል በክልሉ ከዚህ ቀደም በቀበሌ ሊቀ መንበር፣ በምክትል ሊቀመንበርና በጸጥታ ዘርፍ ብቻ ሲመራ የነበረው የቀበሌ ሥራ በአዲሱ መዋቅር መሠረት የፓርቲ፣የማኅበራዊ ጉዳዮች፣የኢኮኖሚ፣ሚሊሻ ጽ/ቤቶችን አካቶ በሰባት ካቢኔ መዋቀሩን ሰነዱ ያመለክታል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አራት ተጨማሪ መዋቅሮች በቀበሌ ደረጃ ያልነበሩና እንደ አዲስ የተዋቀሩ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ማለትም የቀበሌ ሊቀ መንበሩ፣ ምክትል ሊቀመንበሩና የፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊው የቀበሌው የሥራ አስፈጻሚ አባል እንደሚሆኑ ምንጮች አክለዋል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም ከአንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች ውጪ ለቀበሌ ሰራተኛ ደመወዝ የማይከፍል ሲሆን በአዲሱ አደረጃጀት መሰረት ለእነዚህ ከላይ ለተጠቀሱት ሰባት የቀበሌ አመራር ካቢኔዎች፣ ከ 10 ሺሕ ብር ያላነሰ የተጣራ ደመወዝ ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው ሰነዱ ላይ ተገልጿል።
የክልሉ መንግሥት ይህን ማድረግ ያስፈለገው በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ የሥራ ጫናዎችን ለመቀነስና ታች ላለው ማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።
ሰፊው ማኅበረሰብ አቀፍ ሥራ የሚሰራው በቀበሌ መዋቅሮች ደረጃ በመሆኑና መዋቅሩን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጮች አስረድተዋል።
ይህን ውሳኔ ለመወሰን ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀ ሰፊ ጥናት መካሄዱን የገለጹት ምንጮች፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዞንና በየወረዳው ዝግ ስብሰባዎች ሲደረጉ እንደነበር፣ ከነሐሴ 25/2016 ዓ.ም ጀምሮም በይፋ ወደ ሥራ እንደሚገባ ዋዜማ ሰምታለች።
በክልሉ ዞን የሚለውን መዋቅር በአዲስ መልክ “ክላስተር” በሚል አደረጃጀት ለማዋቀርና መምሪያዎችን ለማጠፍ ጥናትና ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ዋዜማ ከታማኝ ምንጮቿ ሰምታለች። [ዋዜማ]