ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል ከእርሻ መሬት ዓመታዊ ግብር ጋር ተዳብለው በሚመጡ ሌሎች ክፍያዎች ከአቅም በላይ ለሆነ ወጪ መዳረጋቸውን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ።
አንድ የእርሻ መሬት ዓመታዊ ግብር መሬቱ መጠኑ ምንም ያህል ቢሆን 1 መቶ ብር እንደሆነ የሚገልጹት አርሶ አደሮቹ፣ አብረው ከሚመጡ ሌሎች ክፍያዎች ጋር ሲደመር ግን ወደ 6 ሺሕ ብር አካባቢ የሚጠጋ ገንዘብ ለመክፈል መገደዳቸውን ለዋዜማ አስረድተዋል።
በዚሁ ምክንያት አብዛኛው አርሶ አደር መሬቱን ለሌላ ሁለተኛ ወገን ሰጥቶ እንደሚያሳርስ የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ፣ ለማዳበሪያና ለምርጥ ዘር ግዢ የሚከፍሉት ክፍያ፣ ከእነዚሁ ደባል ክፍያዎችና ከዓመታዊ ግብሩ ጋር ሲደመር እህል ሸምቶ ከሚኖረው ማኅበረሰብ ጋር ብዙም ልዩነት እንደሌላቸው ያስረዳሉ።
ከእርሻ መሬት ዓመታዊ ክፍያ ጋር አብረው ተዳብለው የሚመጡት እነዚሁ ከሃያ በላይ ክፍያዎች በተለያዩ ስሞች የታተሙ የክፍያ ደረሰኞች መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ፣ አብዛኞቹ ክፍያዎች ከእነርሱ ህይወት ጋር ምንም አይነት ተያያዥነት የሌላቸውና የማይመለከታቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ከእርሻ መሬት ግብር ጋር አብረው ከሚመጡት ክፍያዎች መካከል ለስፖርት፣ ለቀይ መስቀል ማኅበር፣ ለኦሮሚያ ልማት ማኅበር፣ ለሚሊሻ ጽ/ቤት፣ ለባሕላዊ ፍርድ ቤት፣ ለወጣቶች መዋያ፣ ለቡሳ ጎኖፋ፣ ለሴቶች ሊግ፣ ለጤና መድኅን፣ ለመንገድ፣ ለጸጥታ የሚሉ እንዳሉበት ዋዜማ የተመለከተቻቸው የክፍያ ደረሰኞች ያመለክታሉ።
አርሶ አደሮቹ ከላይ ለተዘረዘሩት የአገልግሎት መስኮች ክፍያ ቢፈጽሙም እንኳን፣ አብዛኞቹ አገልግሎቶች በቀበሌ ደረጃ መዋቅር የሌላቸው መሆናቸውንና ለከፈሉት ክፍያም የሚያገኙት አገልግሎት አለመኖሩን በአጽንዖት ያነሳሉ።
ይህ አይነቱ የእርሻ መሬት የግብር አከፋፈል ስርዓት በቀደመው ጊዜ ብዙም እንደማይታወቅ የሚያስረዱት አርሶ አደሮቹ፣ ራሱ መንግሥት በሚያሳትማቸው የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኞች “ህጋዊ ዝረፊያ” የሚፈጸምበት መንገድ ነው ሲሉ ስለ ሁኔታው ያብራራሉ።
ይህን የሚያስፈጽሙት በቀበሌ ደረጃ ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች መሆናቸውን የሚገልጹት አርሶ አደሮቹ፣ ከእነርሱ ጋር አብረው የሚንቀሳቀሱ የታጣቁ የመንግሥት ኃይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት ይህን ግብር ሲሰበስብ በአካባቢው ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው አማጺ ቡድን ለምን ለመንግሥት ግብር ትከፍላላችሁ በማለት አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸው ዋዜማ ከአርሶ አደሮቹ አንደበት መስማት ችላለች።
በአንዳንድ አካባቢዎች ራሳቸው ታጣቂዎቹ “ግብር መክፈል ያለባችሁ ለእኛ ነው” በማለት ከሕብረተሰቡ ግብር እንደሚሰበስቡ የሚገልጹት ምንጮች የመንግሥት ኃይሎች በበኩላቸው ታጣቂዎቹን ረድታችኋል በማለት እስርና ድብደባ በሰላማዊ አርሶ አደሮች ላይ እንደሚፈጽሙባቸው አስረድተዋል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አንድ አርሶ አደር “ቀን ቀን የመንግሥት ሰዎች ግብር ክፈል ይሉኛል ሌሊት ደግሞ ታጣቂዎች ለምን ከፈልክ ብለው ሌላ ጫና ውስጥ ይከቱኛል” ሲሉ ቃላቸውን ለዋዜማ ሰጥተዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አንድ አርሶ አደር ደግሞ ክፍያውን የመፈጸም አቅም ስለሌላቸው ይዞታቸውን የተሻለ አቅም ላለው ሰው ኮንትራት ወይም የእኩል ሰጥተው እንደሚያሳርሱ የተናገሩ ሲሆን ይህም የሆነው በዓመት ያን ያህል ክፍያ የመክፈል አቅም ስለሌላቸው እንደሆነ አብራርተዋል።
ዋዜማ ለአብነት ያኸል ይህን ትበል እንጂ፣ በመላው የክልሉ አካባቢዎች ከእርሻ መሬት ዓመታዊ ግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ያለው አሰራር ተመሳሳይ መሆኑን ማጣራት ችላለች።
አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት ለከፈሉት ክፍያ ከመንግሥት ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት ቢያገኙ መልካም እንደነበር የሚናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንኳን በወቅቱ ለማግኘት ያለው ፈተና ቀላል አይደለም ሲሉ ያለውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
ዋዜማ በአርሶ አደሮቹ ቅሬታ ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የኦሮሚያ ግብርናና ገቢዎች ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ባለመሳካቱ ሃሳባችውን ማካተት አልተቻለም። [ዋዜማ]