(ዋዜማ ራዲዮ) ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንዳለው በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ዝርዝር ህጉ ሳይወጣ ሃያ ዓመታት አልፏል፡፡ ይህ ህግ ለዓመታት ሲጓተት ኖሮ በኦሮሚያ ህዝባዊ አመፅ በተቀሰቀሰበትና መንግስት በፌደራል ተቋማት በሙሉ የብሄረሰብ ተዋፅዖን ለማመጣጠን የሚረዳ ፖሊሲ ሊቀርፅ እንደሆነ ባስታወቀበት ሰሞን ኦሮሚያ ክልል ግብረ ኃይል አቋቁሞ ጉዳዩን እያጠናው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ለመሆኑ ልዩ ጥቅም የተባለው ድንጋጌ ምን ምን ጥቅሞችን ሊያካትት ይችላል? ህጉ እስካሁን ሳይወጣ ለምን ዘገየ? አሁንስ ለምን ለማውጣት ታሰበ? ምንስ አንድምታዎች ይኖሩታል?
ቻላቸው ታደሰ ዝርዝር ዘገባ አዘጋጅቷል
በህገመንግስቱ አንቀፅ 49 (5) ላይ አዲስ አበባ በጅኦግራፊያዊ አቀማመጧ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ ክልሉ በከተማዋ ላይ “ልዩ ጥቅም” (special interest) እንደሚጠበቅለት ቢገልፅም ዝርዝር ህጉ ስላልወጣ ላለፉት ሃያ ዓመታት ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ህገመንግስትና የተሸሻለው የአዲስ አበባ መተዳደሪያ ቻርተርም (በአንቀፅ 62 ንዑስ አንቀፅ 2) በተመሳሳይ ይህንኑ ልዩ ጥቅም አካተዋል፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ልዩ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ክልሉ በአዲስ አበባ ላይ ያለው ጥቅም የሚከበረው በህጋዊ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ፣ ጅኦግራፊያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ምክንያቶች ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በፌደራሊዝም ጥናት ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆኑት ፕሮፌሰር ዳንዔል አላዛር በእውነተኛ ፌደራሊዝም ውስጥ አንድ ከተማ ብቻ የስበት ማዕከል መሆን እንደሌለበት ይመክራሉ፡፡ አዲስ አበባ ግን ብቸኛዋ የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ባህል ማዕከል ነች፡፡ ኦሮሚያ ክልልም ዋና መቀመጫውን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ያዛወረውም ሆነ የክልሉ ልዩ ጥቅም አንገብጋቢ ጉዳይ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ህገመንግስቱ ለክልሉ ያስጠበቀለት ልዩ ጥቅም የጋራ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን፣ አግልግሎት አቅርቦትንና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን የሚመለከት ነው፡፡ በማህበራዊ አግልግሎቶች ላይ ያለው ልዩ ጥቅምም ከተማዋ የኦሮሞን ባህልና ማንነት የምታንፀባርቅ እንድትነ የሚያስችል እንደሆነ ታስቦ ነው፡፡ ለምሳሌ በከተማዋ በኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ ትምህርት የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩ ማድረግን ሊያካትት ይችላል ይላሉ የህግ ባለሙያዎች፡፡ በ1997ቱ ምርጫ ማግስት በከተማዋ እምብርት ላይ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ተገንብቶ ስራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ ባይሆንም የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ግን ቋንቋው በአዲስ አበባ ሁለተኛ የስራ ቋንቋ እንዲሆን እስከማድረግም ሊደርስ እንደሚችል ግምቱ አለ፡፡
አዲስ አበባ ንፁህ መጠጥ ውሃ የምታገኘው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ገፈርሳ እና ለገዳዲ ውሃ ማጣሪያዎች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንፃሩ ግን እንደ አቃቂ እና በሰቃ የመሳሰሉ የኦሮሚያ ወንዞች በአዲስ አበባ ፋብሪካዎች ዝቃጭ መበከላቸውን የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች አሉ፡፡ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ልዩ ጥቅሙን መሰረት አድርጎ ለሚደርስበት የተፈጥሮ ሃብት ብክለት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ ወይም ሌላ ማካካሻ ሊጠይቅ እንደሚገባም የሚከራከሩ ወገኖች አሉ፡፡
በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ረገድ ደግሞ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና መቀመጫ ከመሆኗም ጋር ይያያዛል፡፡ በአስተዳደራዊና ፀጥታ አጠባበቅ ዘሪያ የሚነሳው ልዩ ጥቅም አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን ፌደራል መንግስቱንም ሊያካትት ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ አስተዳደራዊ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስቱ ነውና፡፡ ከዚህ አንፃር ኦሮሚያ ክልል ጥቅሙን በሚነኩ በፌደራል መንግስቱ በሚወጡ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይም የመሳተፍ መብት እንዲኖረው ሊጠይቅ እንደሚችል አንዳንድ የህገመንግስት ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡ የኦሮሚያን ጥቅም የሚነካ ፖሊሲ ሲባል እንደ አወዛጋቢው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዓይነት ፖሊሲዎች ማለት መሆኑ ነው፡፡
የልዩ ጥቅምን ትርጓሚ በጣሙን የሚለጥጡት የብሄሩ መብት ተሟጋቾች ክልሉ በአዲስ አበባ ምክር ቤት እንዲሁም አዲስ አበባ በፌደራሉ ምክር ቤት ካላት መቀመጫዎች የተወሰነ ኮታ የማግኘት መብት ሊኖረው እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡ የአንቀፁ ትርጓሜ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በአዲስ አበባ መስተዳድር ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸው እስከማድረግ ሊደርስ እንደሚችልም የሚሞግቱ የመብት ተቆርቋሪዎች እንዲሁ ጥቂት አይደሉም፡፡
የብሄሩ መብት ተሟጋቾችም ሆኑ አንዳንድ የህግ ባለሙያዎች የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም የከተማዋን ገቢ እስከመጋራትም ሊደርስ እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ሦስቱ ዋና ዋና የአዲስ አበባ መስተዳድር ገቢ ምንጮች ከተለያዩ ገቢዎች የሚሰበሰብ ቀረጥ፣ የውስጥ ብድር እና ከፌደራል መንግስቱ የሚገነው ድጎማ ናቸው፡፡ በእርግጥ አዲስ አበባ በውስጧ ከሚገኙት በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል መንግስቱ ባለቤትነት ከተያዙት ኢንተርፕራይዞችና ቅጥር ሰራተኞች ገቢ ግብር የመሰብሰብ ስልጣን ስለሌላት ራስን በራስ የማስተዳደር መብቷ የተገደበ ከመሆኑም በላይ የገቢ ምንጯን እንዳመናመነው የፌደራሊዝም ተመራማሪው ዶክተር አሰፋ ፍስሃ ይገልፃል፡፡ ፌደራል መንግስቱም ለዚህ የሚሆን ማካካሻ አይሰጣትም፡፡ ያም ሆኖ ግን ከተማዋ ገቢ የመሰብሰብ አቅሟ ውስን ስለሆነ እስካሁንም የገቢ ምንጯን አሟጣ እንዳልተጠቀመች ያስረዳል፡፡
የሀገሪቱ ህገመንግስት የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅሞች በሙሉ ዘርዝሮ አላስቀመጠም፡፡ ይልቁንስ ሦስቱን ዋና ዋና ጥቅሞች በጥቅሉ ከዘረዘረ በኋላ “ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች” የሚል ሃረግም አካቷል፡፡ “ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች” የተባሉት ገና ያልተፍታቱ ጉዳዮች ቢሆኑም ከአስተዳደራዊ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችና ተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር ዝምድና ያላቸው ጉዳዮችን በሙሉ ሊያካትቱ ስለሚችሉ የክልሉ ልዩ ጥቅም እንደ ሁኔታው እጅጉን ሊሰፋም ሆነ ሊጠብ እንደሚችል አመላካች ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የልዩ ተጠቃሚነቱ ወሰን በተሟላ ሁኔታ የሚታወቀው በህገመንግስት ትርጓሜ (constitutional interpretation) ወይም ዝርዝር ህጉ ሲወጣ ብቻ ነው፡፡
እዚህ ላይ መወሳት ያለበት ከሌሎች ሀገሮች በተለየ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ህገመንግስቱን የመተርጎም ስልጣን የሌላቸው መሆኑ ነው፤ ልዩ ህገመንግስተዊ ፍርድ ቤትም የለም፡፡ ህገመንግስቱን የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው ፖለቲካዊ ተቋም ለሆነው ፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ወደ ህገመንግስት ትርጉም የሚያመራ ከሆነ ትርጓሜው ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ የፀዳ ሊሆን እንደማይችል ጠቋሚ ነው፡፡ የጉዳዩ ባለቤት የሆነችው አዲስ አበባ ግን በፌደሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ምንም ውክልና የላትም፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ከህገመንግስታዊ አሰራር ይልቅ በተለምዶ የሚሰራው በገዥው ፓርቲ ውስጣዊ አሰራር ደንብ መሰረት መሆኑን ፌደራላዊ ስርዓቱን በጥልቀት ያጠኑት እነ ፕሮፌሰር ጆን ያንግ፣ ፕሮፌሰር ሳራ ቮግ፣ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋም እና ኢትዮጵያዊያኖቹ እነ ዶክተር አሰፋ ፍስሃና ዶክተር ፀጋዬ ረጋሳ በተለያዩ ጥናቶቻቸው መስክረዋል፡፡ ያ ማለት የክልሉ ገዥ ድርጅት ኦህዴድ ለኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ተገዥ መሆን ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ እስካሁን የኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ ውዝግብ ያለተካረረው ሁለቱም በኢህአዴግ የሚመሩ በመሆናቸው እንጂ አንዳቸው በተቃዋሚ ፓርቲ ቢመሩ ኖሮ ግን ሁኔታው የተለየ መልክ እንደሚኖረው መገመት አይከብድም፡፡
የሀገሪቱ ህገመንግስት ህግ የማውጣት ስልጣንን የሰጠው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፤ በተሸሻለው የአዲስ አበባ ቻርተር ላይም የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅም የሚመለከተው ዝርዝር ህግ በከተማዋ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መካከል በሚደረስ ስምምነት ወይም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጣ ህግ እንደሚወሰን ይገልፃል፡፡ ይህም ህገመንግስቱ ሁለቱ አካላት ጉዳዩን በስምምነት እንዲጨርሱ ዕድል እንደሰጣቸው ያሳያል፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና አዲስ አበባ መስተዳድር በጉዳዩ ላይ የጋራ ውይይት አድርገው ስለማወቃቸው ምንም ፍንጭ የለም፡፡
አዲስ አበባ የፌደራሉ መንግስቱ መቀመጫ ከመሆኗም በላይ ተጠሪነቷም ለፌደራሉ መንግስት በመሆኑ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም የፌደራል መንግስቱን ጥቅም በቀጥታ ይነካል፡፡ ያ ማለት ደግሞ ዝርዝር ህጉን የማውጣቱ ኃላፊነት በዋነኛነት የፌደራሉ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሆን ይነግረናል፡፡ ፌደሬሽን ምክር ቤትም ቢሆን ጉዳዩን አጥንቶ ለተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ህገመንግስቱ ይፈቅድለታል፡፡
በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደሚታሰበው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ህገመንግስታዊውን ልዩ ጥቅሙን በተመለከተ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ ከሰባት ዓመታት በፊት ልዩ ጥቅሙን ለማስከበር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደሞከረ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ህግመንግስት ላይ ጥልቅ ምርምር በማድረግ የሚታወቀው ዶክተር ፀጋዬ ረጋሳ ኦሮሚያ ክልል አንቀፁ ህገመንግስታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ሆኖም ፌደሬሽን ምክር ቤት ህመንግስታዊ ውዝግብ (constitutional dispute) ባልተነሳበት ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሃሳብ እንደማይሰጥ በመግለፅ ጥያቄውን ወደ ጎን ገፍቶታል፡፡ በእርግጥ ህገመንግስታዊ ትርጓሜ የሚሰጠው አንድ ህግ፣ ደንብ ወይም አሰራር ከህገመንግስቱ ጋር ይጋጫል ወይስ አይጋጭም የሚል ውዝግብ (dispute) መኖሩ ሲያረጋጥ ብቻ እንደሆነ በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በልዩ ጥቅሙ ላይ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎችም አሉ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግን ለክልሉ ውሳኔ ሃሳብ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ እንደቀረ ጉዳዩን የሚከታተሉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፌደራል መንግስቱ ጉዳዩ መፍትሄ ሳያገኝ እየተንከባለለ ብቻ እንዲቆይ ፍላጎት እንዳለው ነው፡፡
ምንም እንኳ ጎልቶ ባይሰማም የአዲስ አበባ አንዳንድ ክፍለ ከተማዎች ከአጎራባች የኦሮሚያ ከተማዎችና ዞኖች ጋር በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሲወዛገቡ እንደኖሩ የሚሳዩ ጥናቶች አሉ፡፡ መፍትሄ ሳይሰጣቸው እንዲሁ ተሸፋፍነው ቀሩ እንጂ፡፡ ይህም የክልሉ ልዩ ጥቅም ዝርዝር ህግ አለመውጣቱ በከተማዋና ኦሮሚያ ክልል መካከል የተቀናጀ ልማትና አወንታዊ አግድሞሽ ግንኙነቱ የተቃና እንዳይሆን ማድረጉን ያሳያል፡፡ የከተማዋም ሆነ የኦሮሚያ አጎራባች ዞኖችና ከተማዎች ዕድገት አቅጣጫም ግልፅ እንዳይሆን እንዳደረገው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድርም ቢሆን አዋሳኝ የኦሮሚያ ከተሞችን ያማከለ መሪ ዕቅድ ማውጣቱ ከፈረሱ ጋሪውን የማስቀደም ያህል እንደሆነ የሚስማሙበት ታዛቢዎች በርካቶች ናቸው፡፡
አሁን ጎልቶ እየተሰማ ያለው የኦሮሚያ ክልል የተናጥል እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሆኖም በስራ ላይ ያሉት ህጋዊ ማዕቀፎችም ሆኑ የህግ ባለሙያዎች ጉዳዩ ኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ በሚያቋቁሙት የጋራ ጥምር ግብረ ኃይል ተጠንቶ መፍትሄ ቢሰጠው እንደሚሻል ይመክራሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ስለመታሰቡ ግን ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ክልሉ ቀደም ሲል ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብም ከአዲስ አበባ ጋር አልመከረበትም፡፡ በሌላ በኩል ግን የኦሮሚያ ክልል ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ ላይ አድርጎ የከተማዋን ትሩፋቶች ሲቋደስ ከተማዋ በተራዋ ከኦሮሚያ ክልል ማግኘት የሚገባት ጥቅሞች ይኑሩ አይኑሩ እምብዛም ውይይት ሲደረግበት አይታይም፡፡
የልዩ ተጠቃሚነቱ ጉዳይ ሲንከባለል ኖሮ እንደገና በዚህ ጊዜ እንደ አዲስ ለምን ሊነሳ ቻለ? የሚለውም አነጋጋሪ ነው፡፡ መንግስት በማስተር ፕላኑ ላይ የተነሳውን ህዝባዊ አመፅ ለመቀልበስ ኃይል ቢጠቀምም በተጓዳኝ ግን ከህዝብ ፍቃድ ውጪ ተፈፃሚ እንደማይሆን ደጋግሞ መግለፁን እንደ ጊዜ መግዣ የሚያዩት ታዛቢዎች እንዳሉ ሁሉ የአቋም ለውጥ ነው የሚሉም አልጠፉም፡፡
ሃሳቡ በክልሉ ተነሳሽነትም ይምጣ ወይም በፌደራል መንግስቱ ግፊት ጉዳዩ ከተነሳበት ጊዜ አንፃር ሲታይ ግን ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው አስመስሎታል፡፡ በአንድ በኩል ክልሉ በህዝባዊ አመፅ እየተናጠ ባለበት ወቅት መነሳቱ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ ቅሬታ ለመፍታት ፅኑ ፍላጎት እንዳለው በማሳየት ህዝባዊ አመፁ ጋብ እንዲልለት ለማድረግ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳ የኦሮሞ ህዝብ ከሀገሪቱ ትሩፋት ተጠቃሚ አልሆነም የሚሉት ምሁራን፣ ብሄርተኞችና የመብት ተሟጋቾች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በርካታ ቢሆኑም የዚህ ጥያቄ በአመርቂ ሁኔታ መመለስ ግን እንደ አንድ አወንታዊ እርምጃ አድርገው ሊወስዱት እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የልዩ ጥቅም አዋጁን በማስቀደም በአዋጁ ሽፋን ማስተር ፕላኑን ለመተግበር የተዘየደም ሊሆን ይችላል፡፡
በጠቅላላው “የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ይሰረዝ”፣ “የኦሮምኛ ቋንቋ ለኢትዮጵያ በታቀደው የእንግሊዙ ቢቢሲ ሬዲዮ ስርጭት ይካተት” እና “ኦሮምኛ የፌደራል መንግስቱ ሁለተኛ የስራ ቋንቋ ይሁን” ከሚሉት ጥያቄዎች ሌላ “ኦሮሚያበአዲስ አበባ ላይ ያላት ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅም ስራ ላይ ይዋል” የሚሉ ግፊቶች ጎልተው መምጣታቸው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እጅጉን እየጎለበት ለመምጣቱ ማሳያዎች ስለመሆናቸው ዋቢ መጥቀስ አያስፈልገውም፡፡ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ገፍተው ለመጡት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽም ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በተለይም ከኦሮሞ ልሂቃን ጋር የሚኖረውን ቀጣይ ግንኙነት የሚወስን ይመስላል፡፡