ዋዜማ ራዲዮ- የእንግሊዝ መንግስት የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይልን አሰልጥኗልና አስታጥቋል በሚል ሲወጡ የከረሙት ዘገባዎች የተሳሳቱ ናቸው ሲል አስተባበለ።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ለዋዜማ በላከው መግለጫው እንግሊዝ በሶማሌ ክልል ከ 2013 እስከ 2015 ድረስ ድጋፍ ያደረገችው ህፃናትና ሴቶች ተኮር ለሆነ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ስልጠና ነበር። ድጋፉ ለትምህርት ለጤናና ለንፁሕ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ላይ ያተኮረ ጭምር የነበረ ሲሆን የክልሉን ልማትና ስላም ለማጠናከር ያለመ ነበር።
ድጋፉ በ 2015 የፈረንጆች አቆጣጠር ማብቃቱን የኤምባሲው ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ድጋፉ ሲደረግ የነበረው በእንግሊዝ አለማቀፍ ተራድኦ ድርጅት (DFID )በኩል ሲሆን በተደጋጋሚ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን እንግሊዝ ለሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ድጋፍ እንዳደረገች ተደርጎ መቅረቡ ስህተት መሆኑን አስገንዝቧል።
የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ ዓለማቀፍና የሀገራችን የመገናኛ ብዙሀን ከአምስት ዓመት በፊት በእንግሊዝ የልማት ተራድዖ ድርጅት የወጣ ሪፖርትን ዋቢ አድርገው እንግሊዝ ለሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል ድጋፍ አድርጋለች የሚል ዘገባ አቅርበው ነበር።
ባለፉት አመታት በሶማሌ ክልል የልዩ ሀይል አባላት በተደጋጋሚ በፈፀሙት የስብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ የእንግሊዝ መንግስት ለፀረ ሽብር ዘመቻ ያደረገውን የቁሳቁስ ድጋፍና ስልጠና በመጠቀም እንደነበር የመገናኛ ብዙሀን ሲዘግቡ ነበር።
የእንግሊዝ የዓለማቀፍ ልማትና ተራድዖ ሀላፊ ፔኒ ሞርዳንት ስሞኑን በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት ሀገራቸው በተለያዩ መስኮች የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች ብለዋል።
የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስትር ጋቪን ዊልያምሰን ወታደራዊ ተቋማት የፆታ ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል አሰራር ለማስተዋወቅ በተሸኘው ሳምንት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራትን ጎብኝተዋል። ከኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ሞቱማ መቃሳ ጋርም ተወያይተዋል።