በዋዜማ ሪፖርተር
ዋዜማ ራዲዮ- ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከደረሰው የሰዎች ግድያና ንብረት ውድመት ምክንያት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሊቀመንበር እስክንድር ነጋና ሰው በመግደልና ግጭት በመፍጠር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኘው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) አባል ጃዋር መሀመድ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 22 2012 በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ችሎት ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ቀረቡ፡፡
የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራዳ ተረኛ ችሎት የቀረቡት አቶ እስክንድር ነጋ ፖሊስ ምርመራዬን ስላልጨረስኩ ተጨማሪ የ 14 ቀን የምርመራ ግዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቆ ነበር ፡፡
በባለፈው የምርመራ ጊዜ መርማሪ ቡድኑ የሰራውን ለችሎት አስረድቶ የቀሩ ምስክሮችን ቃል መቀበል የ14 ሰው አስክሬን ምርመራ ውጤት߹ ከ6 ክፍለ ከተሞች ውጪ ሪፖረት አልመጣለኝም߹የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ምርመራ ውጤትን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ነኝ እንዲሁም አቶ እስክንድርን በቁጥጥር ስር ስናውል ከእጅ ስልካቸው ውጪ ላፕቶፕም ሆነ ዲስክ ቶፕ ስላላገኘን ማጣራት ስለሚቀረኝ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ለችሎት ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ በቸልተኝነት ያለ አግባብ ደንበኛችን እንዲቀጡ እያደረገ ነው። ለ28 ቀናት ደንበኛችን እስር ላይ ናቸው። የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ያሉ ሲሆን ጠበቆቹ አክለውም ችሎት ለመዘገብ የመንግስት ሚዲያዎች ሲገቡ የግል ሚዲያዎች መከልከል የለባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
ግራቀኙን የሰማው ፍርድ ቤት ፖለስ የጠየቀውን የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ዝቅ በማድረግ 9 ቀናትን የፈቀደ ሲሆን በሚዲያዎች በኩል ጠበቆች ላነሱት አቤቱታ ማንም የተከለከለ ሚዲያ የለም የተከለከለ ካለ ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል ብለው ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሀሴ 1 2012 ሰጥተዋል፡፡
ጃዋር መሀመድ
የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ አስክሬን በመቀማት እና ሁከት በመፍጠር ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ጃዋር መሃመድ ላይ የ 12ቀን የምርመራ ግዜ ተፈቅዷል።
አመፅ እንዲፈጠር ብሄርን ከብሄር፣ ሀይማኖትን ከሀይማኖት ግጭት እንዲፈጠር በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች ትእዛዝ በመስጠት በንብረት እና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ ወንጀል ና (ኦ ኤም ኤን) አመፅ በመቀስቀስም በአዲስ አበባ ብቻ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት የተጠርጠሩት አቶ ጃዋር ፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር ፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው የምርመራ ግዜ የተጠርጣሪውን ቤት በድጋሚ ፈትሻለሁ ߹ከ25 በላይ ሰዎችን ቃል ተቀብያለሁ 17 የምርመራ ቡድን ወደ ኦሮሚያ ክልል ልኪያለሁ ሲል የተሰሩ ስራዎች ብሎ ለችሎት ያስረዳ ሲሆን በቀጣይ ምስክሮችን መስማት߹ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ምርመራ ውጤትን መቀበል ߹ ወደ ክፍለ ሀገር የላኩዋቸው የምርመራ ቡድኖች ሪፖረት እንዲሁም ሰነዶችን ማስመርመር ስለሚቀረኝ የ 14 ቀን የምርመራ ግዜ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች ፖሊስ ተመሳሳይ ጉዳይን ነው ለጊዜ መጠየቂያነት ያቀረበው ምንም አዲስ ስራ አልተሰራም ስለዚህ የጠየቀው ጊዜ ውድቅ ይደረግበት ሲሉ ችሎትን ጠይቀዋል፡፡
አቶ ጃዋር በበኩላቸው “የኔ ወደዚህ አገር የመጣውት በሰላም ልታገል ነው… እስሩ ፖለቲካዊ ነው… ምርጫን ያሸንፈናል ብለው ነው ያሰሩኝ። ከ1000 በላይ የጦር መሳሪያን ከተለያዩ ኦሮሚያ ክልል ተቀብዬ ለመንግስት ያስረከብኩ ሰው ነኝ። እኔ ወንበዴ አደራጅቼ የማስበጠብጥ አይደለሁም፡፡ እኔን ከፖለቲካ ለማራቅ እና ብቻቸውን ምርጫ ለማድረግ ነው፡፡ እኔ ከምርጫ ቀርቼ የአገር ሰላምና ፀጥታ የሚመለስ ከሆነ እኔ እስር ቤት ልቀመጥ፡፡ እስሩ የፖለቲካ መሆኑን በልደቱ አያሌው ፣ በእስክንድር ነጋ እና እኔ የተጠረርንበት ተመሳሳይ ነው ይህ እኛን ከፖለቲካ ለማረቅ የተደረገ ነው” ሲሉ ለችሎት ተናግረዋል፡፡
ግራቀኙን የሰማው ፍርድ ቤት ሁለቱንም ወገኖች የፖለቲካ ይዘት ያለው ክርክር እንዳያቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቶ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ዝቅ በማድረግ 12 ቀናት በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሀሴ 5 2012 ሰጥቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]