eth econ

 

የኢትዮዽያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትርክት የብዙሀኑን ቀልብ በገዛበት በአሁኑ ጊዜ ስለምን የኢኮኖሚ በረከቱ ለብዙሀኑ ድሀ ዳቦ መግዛት ተሳነው የሚለው ጥያቄ ከአንድ በላይ መልስ ያለው ይመስላል። መዝገቡ ሀይሉ የክርክሩን አንድ ደርዝ ተመልክቶታል። አድምጡት

 

Social Progress Index በመባል የሚታወቀው የማኅበረሰብ እድገት ጠቋሚ ጥናት ኢትዮጵያ ከ133 አገሮች መካከል 126 ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አሳየ።

ይህ የማሕበረሰብ እድገት ጠቁዋሚ ጥናት ከሌሎች ጥናቶች በተለየ ማኅበረሰባዊ እድገትን ለማሳየት እንደመስፈሪያ የሚጠቀምባቸው መንገዶች በአብዛኛው የአንድ አገር ኢኮኖሚ በነዋሪዎቹ ሕይወት ላይ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ መለካት ነው።በመኾኑም በሌሎች መለኪያዎች ላይ ያልተለመዱትን የመሰረታዊ አቅርቦቶች መሙአላት እንዲሁም የትምህርት እድል እና የፖለቲካ መብት መከበርን እንደመለኪያ ይጠቀማል።

ይህ የማኅበራዊ እድገት አመካች ጥናት በዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ የአገሮችን ደረጃ ከመወሰን የሚለየው ሩቅ የኾኑ የኢኮኖሚ እድገት ምልክቶችን ብቻ ከመለካት ይልቅ የአንድን ማኅበረሰብ አኑዋኑዋር በመቀየር በኩል የሚታዩትን ውጤቶች በማጥናት ላይ ያተኩራል።
ከዚህም የተነሳ የአንድ አገር የነፍስ ወከፍ ገቢ በጣም ያደገ እንኩዋን ቢኾን እነኚህን የመሰሉ በማኅበረሰቡ ኑሮ ላይ ለውጥ የሚያመጡ ነገሮች አቅርቦት ኹኔታ የአገሮችን ደረጃ ይወስናል ማለት ነው።

የኢኮኖሚ እድገት እና ለውጥ ዋነኛው የመሪዎቻችን አጀንዳ መኾኑ አሁን የተከሰተ ጉዳይ አይደለም። አገሪቱ ትዳክርበት የነበረው የድኅነት መጠን ጥሩ ልብ ላላቸው ቅን መሪዎች በርግጥም ዋነኛ ጉዳያቸው ኾኖ ቢገኝ አያስገርምም። ያንኑም ያህል ብልጣብልጥ የፖለቲካ ግባቸውን ለመምታት ይህንኑ ቁስላችንን የሚጠቀሙበት መሪዎችም መከሰታቸው የታሪካችን አንዱ እውነት ነው። አሁን አሁን ይኸው ዋነኛ የፖለቲካ መዘወሪያ የኾነው ጉዳይ “ልማት” በሚል ስም ተደጋግሞ ሲጮህ ተደጋጋሚነቱ ምክንያት ለብዙዎች አታካች የኾነ ወሬ እየኾነ መጥቱአል። ይህ ተደጋጋሚ ጩኸት ለብዙዎች አስፈላጊ የኾነውንም እድገት እና ለውጥ እንደ ርእሰ ጉዳይ አንስቶ መወያየት የማይመረጥ ነገር አድርጎባቸዋል።

እድገት እና ለውጥ የመምጣቱ አስፈላጊነት ለማንም አከራካሪ አይደለም። እንኩዋን እንደኢትዮጵያ ላለች ሕዝቡዋን መመገብ የተሳናት ደሃ አገር ይቅርና ለበለጸጉትም አገሮች ቢኾን የበለጠ ማደግ እና የሕዝባቸውን ችግር መቅረፍ ወቅት የማይገድበው የሁልጊዜ መወያያ ነው።

ጥያቄ የሚፈጠረው የእድገትን ምንነት እና እንዴት እንደግ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሲሞከር ነው። በዘመናችን አንቱ ከተባሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል በግምባር ቀደምነት የሚነሱት አማርትያ ሴን የተባሉ ምሁር ተጠቃሽ በኾነው ስራቸው “Development as Freedom” ላይ ለነዚህ ጉዳዮች በሰጡት ብያኔ ተደጋግመው ይነሳሉ።ግለሰባዊ ነፃነትን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ለማያዛምዱት ለብዙ የዘርፉ ባለሞያዎች ፈተና በኾነው በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ ሴን እንዲህ ብለው ነበር። “ነፃነት የእድገት ዋነኛ መዳረሻ ብቻ ሳይኾን እድገትን ለማምጣት የሚያስፈልግ ዋነኛ መሳሪያም ጭምር ነው።” ይላሉ።

የኢኮኖሚ እድገት ነፃነት ያለውን አስፈላጊነት በተመለከተ የአማርትያ ሴንን የመሰለ አቅዋም ያላቸው ብዙ ምሁራን የመኖራቸውን ያህል፤ ተፃራሪም አላጡም። ሰብአዊ ነፃነት ከአገር ኢኮኖሚ እድገት ጋር ምንም አይንት ግንኙነት የለውም ብለው ከሚከራከሩት አንስቶ እንዲያውም እንዲህ ያለ ነፃነት መፍቀድ ለእድገት እንቅፋት ይፈጥራል ብለው የሚያምኑ ተከራካሪዎችም አልጠፉም።
በዋነኝነት በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አንስቶ በምስራቅ እስያ የተፈጠረውን እድገት ተኮር የመንግስት ቅርጽ ለኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ አድርገው የሚያቀርቡ ወገኖች ለዚህ ክርክር ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። ራሱን ለዚህ ዓላማ በሚመች መንገድ ያዋቀረ መንግስት በጠንካራ ክንድ የሚያንቀሳቅሰው ይኸው የኢኮኖሚ አኪያሄድ በነዚህ የምስራቅ እስያ አገራት የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ረድትዋል በሚል ለክርክሩ እንደዋነኛ ማስረጃ ያቀርባሉ።

የኢትዮጵያም መንግስት እከተለዋለሁ የሚለው ሥርዓት ይህንኑ “ልማታዊ መንግስት” በሚል ስያሜ የተቀዳ የመንግስት ሥርዓት ነው። ራሱን ለቀረው ዓለም የሚያስተዋውቅበት ማንነቱም ይኸው ነው። በአደባባይ ዲሞክራሲ አያስፈልገንም ብሎ ባያውጅም በሰብአዊ መብት አያያዝ እና በዲሞክራሲ ላይ ችግር እንዳለበት የምዕራቡ ዓለም ያውቃል። ይህም እየታወቀም ቢኾን ግን የምዕራቡን ዓለም ድጋፍ ለማግኘት መታያው ይኸው የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ቁርጠኝነት ያለው መንግስት መኾኑን ማሳየት ነው።

የፋይናንሻል ታይምስ ዘጋቢ ካትሪና ሜንሰን ይህን ከሰምና ወርቅ ባህላችን ጋር የተመሳሰለባትን የኢኮኖሚ እድገት ወሬና የኢትዮጵያን መንግስት አምባገነን ባህርይ ታዝባዋለች። “የኢትዮጵያ አያዎ” ወይም the Ethiopian Paradox ብላ ርእስ በሰጠችው ጽሑፉዋ ይህን የምዕራቡ ዓለም ሙሉ በሙሉ የተቀበለው የሚመስለውን የኢትዮጵያን መንግስት ስኬት በዋነኛው የገንዘብ ምንጭ በዓለም ባንክ ሳይቀር ጥርጥር እንዳሳደረም ትጠቁማለች።

የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ የሚወቀስበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ለተቃዋሚዎች ቦታ ያለመስጠቱን በኢኮኖሚ እድገት እና የዲሞክራሲ እድገት በሚወስደው ጊዜ ለመሸፈን ቢሞክርም ይህ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኢኮኖሚ እድገት እየተሰጡ ካሉ ትርጉሞች ጋር ሲጋጭ ይታያል። ሕዝቡ ነፃነት በተነፈገበት እና ዲሞክራሲ በሌለበት አገር የኢኮኖሚ እድገት አይታሰብም ከሚለው አንስቶ የግለሰብ ነፃነት የእድገት አንዱ መለኪያ መኾን አለበት እስከሚሉት ድረስ ይህ የኢትዮጵያ መንግስት “ለሰብዓዊ መብት አይገደኝም ልማታዊ መንግስት ነኝ” የሚለው ክርክሩ የማያዋጣ የሚኾንባቸው አጋጣሚዎች እየተፈጠሩም ነው።
“የኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ ቢኾንም ለማኅበራዊ እድገት ማሳያነት በቂ አይደለም” ከሚል ሐሳብ በመነሳት ሌላ ተጨማሪ የዕድገት መለኪያ መንገድ እንደሚያስፈልግ የሚያምኑ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች የማኅበራዊ እድገት ጠቁዋሚን የመሰለ የተለየ መለኪያ በመጠቀም የአገሮችን እድገት መለካት ጀምረዋል። እነዚሁ ባለሙያዎች እንደሚሉት የነፍስ ወከፍ ገቢንና የአገሮችን የምርት እና የገቢ መጠን በመለካት ብቻ የኢኮኖሚ እድገቱን ውጤት ማወቅ አይቻልም። በነፍስ ወከፍ ገቢና በምርት መጠን ከፍ ያለ ውጤት ማስመዝገብ አስፈላጊ የኾኑ የማኅበራዊ እድገት ጉዳዮችን ሊሸፍንም ይችላል።
ስለዚህም የተለመዱትን የቁጥር መስፈሪያዎች አሙዋልቶ በማሳየት ፈጣን እድገት እያመጣ እንደኾነ ለሚሙዋገተው የኢትዮጵያ መንግስት ይህን መሰሉን መለኪያ ሙሉ በሙሉ ችላ ካላለው በስተቀር ሊያልፈው የማይችለው ፈተና እንደሚያመጣበት አያጠያይቅም።