Military Business

 

የኢትዮዽያ መከላከያ ሰራዊት በኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ተሳታፊ እየሆነ መምጣት የማታ ማታ የሲቪል መንግስቱን ህልውና በጠመንጃ ያዡ ሰር እንዲወድቅ ያደርገዋል። ድርጅታዊ አንድነት የሚጎድለው ገዢው ፓርቲም ለህልውናው ሲል መለዮ ለባሹን የኢኮኖሚው ተዋናይና ተጠቃሚ በማድረግ ይደልለዋል። ፖለቲካዊ ቀውስ ሁለቱንም ተዋናዮች ተያይዞ ከመውደቅ የሚያድናቸው አይመስልም። ቻላቸው ታደስ ክፍል ሁለት ዘገባ አሰናድቷል። አድምጡት

 

የሀገራችን ጦር ሰራዊት ለራሱ ፍጆታም ሆነ ለሽያጭ የሚውሉ ዘመናዊ ጦር መሳሪያዎችን ማምረቱ ተገቢና የሚደገፍ ነው፡፡ መቼም ሀገራችን በተስፋፊዋ ሱማሊያ በ1960ዎቹ መጨረሻ በተወረረችበት ጊዜ ከአሜሪካ የተገዛው ጦር መሳሪያ ታግዶ ህልውናችን አደጋ ውስጥ መግባቱ አይረሳም፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ለጦር ሰራዊት የሚመደብ በጀት ከአንድ ሀገር አጠቃላይ ምርት ሁለት ፐርሰንት በላይ እንዳይበልጥ በመሆኑ ጦር ሰራዊቱ የራሱን ወታደራዊ ምርቶች እያመረተ የመንግስትን ባጀት ጠባቂ ባይሆን የሚያስወቅስ ተግባር አይደለም፡፡ በሌሎች ሀገራትም የተለመደ ነው። ሆኖም ዋናው ጥያቄ ወታደራዊ ኢንዲስትሪዎቹ ለሲቪሉ ህዝብ ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን ሳይቀር የሚያቀርቡ ነጋዴዎች መሆናቸው ጦር ሰራዊቱን የጥቅም ግጭት ውስጥ በማስገባት የማይገባው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳ እንዲኖረው አይገፋፉትም ወይ? የሚለው ነው፡፡ መልሱ ቢያንስ በመርህ ደረጃ “አዎ ይገፋፉታል” ይሆናል፡፡

አሜሪካን ጨምሮ ባደጉት ሀገሮች የግል ፋብሪካዎች ሳይቀሩ ከወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ጋር ሽርክና መስርተው ጦር መሳሪያ እያመረቱ ለጦር ሰራዊቱ እንደሚያቀርቡ ይታወቃል፡፡ በእኛ ሀገር ግን በተቃራኒው ወታደራዊ መሳሪያዎችንም ሆነ ለሲቪሉ ህዝብ ፍጆታ የሚውሉት ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን በወታደራዊ ሞኖፖሊ ስር የመጠቅለል አዛማሚያ መታየቱ የኋላ ኋላ እጅግ ከባድ አደጋ ያስከትላል የሚለውን ስጋት የሚጋሩ ብዙ ናቸው። ድርጊቱ ነፃ ገበያን መፃረሩ ብቻ ሳይሆን ጦር ሰራዊቱ በቀጥታ በወገንተኛ ፖለቲካ ውስጥ ያገባኛል እንዲል ያደርገዋልና፡፡ ዴሞክራሲና ህገመንግስታዊነት ባለሰፈነባት ሀገር መሆኑ ደግሞ አደጋውን ያጎላዋል፡፡

ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጅማሮ ተሰፋቸው ባይሟጠጥም፤ በህገመንግስቱ መሰረትም የጦር ሃይሉ ሙሉ ታዛዥነት ለሲቪሉ መንግስት ቢሆንም የሀገሪቱ ፖለቲካ አሁንም ለጦር ሰራዊት ጣልቃ ገብነት የተጋለጠ ስለመሆኑ ምሁራን በስፋት የመወያያ አጀንዳ ያደረጉት ከአቶ መለስ ህልፈት ጀምሮ ነው፡፡

 

በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ኢትዮጵያዊ ምሁራን ፕሮፌሰር ተኮላ ሃጎስና የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመተንተን የሚታወቁት ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ናቸው፡፡ በተለይ ፕሮፌሰር ተኮላ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር ብቸኛው መፍትሄ ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግስት መሆኑን እስከመጠቆም ደርሰዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ተኮላ የመፈንቅለ መንግስት አቀንቃኝ ባይሆኑም ፕሮፌሰር መሳይም በቅርቡ ባስነበቡት አንድ መጣጥፍ “መንግስት አሁን እያደረገ ያለው ነገር በሙሉ መፈንቅለ-መንግስትን የሚጋብዝ ነው” ይላሉ፡፡

ታዋቂውን ምሁር ሬኒ ሌፎርትን ጨምሮ ሌሎችም የቅርብ ታዛቢዎች የጦር ሰራዊቱ አንፃራዊ ነፃነት ስለመጎናፀፉ የሚናገሩት በአቶ መለስ ህልፈት ማግስት የህወሃት የፖለቲካ የበላይነት ቀንሷል ብለው በማመናቸው ነው፡፡ ይህን መካድ ባይቻልም በሌላ በኩል ግን ጦር ሰራዊቱ ራሱ ፖለቲካዊ ሚና ለመጫወት ምን ዓይነት ጥንካሬዎችና ውስንነቶች እንዳሉበት መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው ማንኛውም ጦር ሰራዊት የፖለቲካ ማህበራዊ መሰረት (social base) ስለሌለው የከባድ ሚዛን ፖለቲካ ተዋናይ ለመሆን ቢያንስ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን ማሟላት ያስፈልገዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጦር ሰራዊቱ የኢኮኖሚያዊ ኢምፓዬር ባለቤት መሆን ያስፈልገዋል፡፡ በኢኮኖሚያዊ አቅሙ የተራቆተ ማንኛውም ጦር ሰራዊት ከባድ ሚዛን ፖለቲካዊ ተዋናይ ለመሆን ይቸግረዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የካበተ ወታደራዊ ተቋማዊ ልምድና ባህል ያስፈልገዋል፡፡ ልክ እንደ ታይላንድ፣ ግብፅ፣ ናይጀሪይ፣ ቱርክ ወይም በርማ ጦር ሰራዊት ዓይነት፡፡

ሆኖም በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት እዚህ ግባ የሚባል ልምድ የለውም፡፡ ኢህአዴግ በ1983 ዓመተ ምህረት አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ማግስት ነባሩን ግዙፍ ጦር ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ስለበተነው የአሁኑ ጦር ሰራዊት ከድሮው የወረሰው ተቋማዊ እሴትም ሆነ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ልምድ እንደሌለውም ይታወቃል፡፡ መቼም አቶ መለስ ሙሉ ለሙሉ ሊቆጣጠሯቸው የሚችሏቸውን መኮንኖች በአመራር ላይ አስቀምጠው መሄዳቸው እሙን ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ተንሳይን ከጠቅላይ ኤታማዦርነት ያነሱበት ሁኔታም ይህንኑ ያስታውሰናል፡፡

በሶሰተኛ ደረጃ ደግሞ ጠንካራ ሀገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና (domestic and regional geo-political consciousness) ያስፈልገዋል፡፡ የሀገራችን ጦር ሰራዊት አመራር ግን ሀገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም ዓቀፋዊ ጅኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማራመድ የሚያስችለው ብቃት ያለው ስለመሆኑ መናገር ያዳግታል፡፡ የሀገሪቱ ጦር ሰራዊት በዓለም ዓቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች መልካም ዝና ቢኖረውም ይህ ዓለም ዓቀፍ ልምድ ግን የአመራሩን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ብቃትና ንቃተ ህሊና ስለማዳበሩም ሆነ በጠቅላላው ጦር ሰራዊት ላይ እሴት ለመጨመር በሚያስችል ደረጃ ተቋማዊ (institutionalized) ስለመደረጉ አስተማማኝ ማስረጃ ማየት አልተቻለም፡፡

በአራተኛ ደረጃ ጠንካራ ተቋማዊ አንድነት (institutional cohesion)፣ ዴሞክራሲያዊ ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ ወታደራዊ ኢንዶክትሪኔሽን (military indoctrination) ሊኖረው ይገባል፡፡ ሆኖም የሀገራችን ጦር ሰራዊት ተቋማዊ አንድነቱን የሚጎዱ በሰራዊት ምልመላ፣ በማዕረግ ዕድገት አሰጣጥ፣ በአመራሩ ተዋፅኦ፣ ጥራትና ብቃት ዙሪያ የሚታዩ ድክመቶች እንዳሉበት በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣል፡፡ የተጠቃኘበት ኢንዶክትሪኔሽንስ ሰራዊቱን ለህገመንግስቱ ብቻ ወገንተኛ እንዲሆን የሚያበቃው ነው? ወይንስ ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት የሚያስጠብቅ ነው? የሚለው አጠራጣሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በነገራችን ላይ አቶ መለስ በህወሃት ክፍፍል ወቅት የጦር ሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች በፓርቲው ግምገማ እንዲሳተፉ ማድረጋቸው ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎቹ ግዙፍ ሃብት እያካበቱ ቢሆንም የጠቅላላው ወታደር ኑሮ ስለመሻሻሉ ግን ምንም የሚታይ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ በአመራሩና በተራው ወታደር መካከል ቅራኔ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ከዓለም ዓቀፍ ሰላም ማስጠበቅ ተልዕኮ የተመለሱ ወታደሮች ተገቢው ክፍያ አልተፈፀመልንም ብለው ለአጭር ጊዜም ቢሆን ማመፃቸው ይህንኑ ስጋት ያጠናክራል፡፡ በተለይ ቅራኔዎች ብሄረሰባዊ ይዘት ከያዙ የሰራዊቱን መፈረካከስም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

በእርግጥ ጦር ሰራዊቱ የተመሰረተበት ወታደራዊ ፍልስፍና “ተከላካይነት” (defensive) እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሀኖም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወዲህ “የአጥቂነት” (aggressive) ባህሪ መላበስ ጀምሯል፡፡ በሱማሊያ የሚያደርገው ድንበር-ዘለል የአጥቂነት ዘመቻም በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ነው፡፡ በሉዓላዊቷ ኤርትራ ላይ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲም በሃይል የመንግስት ለውጥ (regime change) ማምጣትን የሚጨምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ የሚተገበረው በጦር ሃይሉ ነው፡፡

እንግዲህ ጦር ሰራዊቱ ይህን በመሰሉ ውስጣዊ ሁኔታዎች ውስጥ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጦር ሰራዊቱን ወደ ፖለቲካ ጎትተው ሊያስገቡት የሚችሉ ሶስት ውጫዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛ መጠነ-ሰፊ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ሁለተኛ በኢህአዴግ ውስጥ የሚፈጠር ድርጅታዊ ቀውስ እና በሶስተኛ ደረጃም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በድጋሚ የሚቀሰቀስ ጦርነትን ማንሳት ይቻላል፡፡

በድርጅት ደረጃ ሲታይ አቶ መለስ እንዳሰቡት ኢህአዴግን ውህድ ፓርቲ ሳያደርጉት በመቅረታቸው ድርጅቱ ለውስጣዊና ዉጫዊ ቀውስ እንደተጋለጠ እሙን ነው፡፡ ድርጅቱ በባህሪው ውስጠ-ዴሞከራሲ ስለሌለውና በአወቃቀሩም የብሄር-ተኮር ድርጅቶች ግንባር በመሆኑ በተለይም ደግሞ የድርጅቱ የጡት አባት አቶ መለስ በሌሉበት ሁኔታ ራሱን ለማደስና የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ ያለው ዕድል የተሟጠጠ ይመስላል፡፡ በግንባሩም ውስጥ የስልጣንና ሃብት ክፍፍልን ማዕከል ያደረጉ ፖለቲካዊ ቀውሶች የመነሳት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ድርጅቱም እስካሁን የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ህይወት ስለተቆጣጠረ ውስጣዊ ቀውሶቹ በቀጥታ ለሀገራዊ መጠነ-ሰፊ ቀውስ ምክንያት የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ቀውሶች ደግሞ ጦር ሰራዊቱን ወደ ፖለቲካ የመሳብ አቅም ይኖራቸዋል፡፡

የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ሁኔታ በአምባገነኖችና ወታደራዊ ገዥዎች የተጠነሰሱትን የምስራቅ እስያ ልማታዊ መንግስታት ፈለግ መከተል እንደሆነ ምሁሩ ሬኒ ሌፎርትና ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ያስረዳሉ፡፡ በእርግጥ ልማታዊ መንግስት ወታደራዊ መልክ ያለው ጠንካራና ጥብቅ ተዋረዳዊ አደረጃጀትን ይጠይቃል፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ግን ኢህአዴግ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ የሚያዘነብለው እውነተኛ ልማታዊ መንግስትን መስርቶ የሀገሪቱን ልማት ለማፋጠን ነው? ወይስ ስልጣን ለማራዘም ነው? የሚለው ነው፡፡ ሆኖም የትኛውም ዓላማ ቢኖረው እስካሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ልማታዊ መንግስትን የሚያስተናግድ ድርጅታዊ፣ መንግስታዊ፣ ሀገራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሌሉ ብዙ ታዛቢዎች ይገልፃሉ፡፡

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥበብ ብቻ ሳይወሰን በዘንድሮው ብሄራዊ ምርጫ እንኳ የፌደራሉን ፓርላማና የክልል ምክር ቤቶችን መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር መድፈሩ ስልጣንን በብቸኝነትና በማናቸውም መንገድ ተቆጣጥሮ የመቆየት ፍላጎቱን ያሳያል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታም ስለማሽቆልቆሉ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ የሚገልፁት ነው፡፡

ሁኔታውም አሁን ካሉትም በላይ በሰላማዊ ትግል ተስፋ የቆረጡ በርካታ ነፍጥ ያነገቡ አማፂያን እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ያኔ ደግሞ ሲቪሉ አመራር ከምንጊዜውም በበለጠ ወታደራዊ መዋቅሩንና ወታደራዊ መፍትሄዎችን የሙጥኝ ማለቱ አይቀርም፡፡

በአንፃሩ ግን ቀደም ብለው ከተነሱት ነጥቦች አንፃር ሲታይ ድርጅታዊና ሀገራዊ ቀውሶች ቢከሰቱም ጦር ሰራዊቱ ራሱ ከቀውሱ ነፃ የመሆን ዕድሉ አናሳ ነው፡፡ ስለሆነም ቀውሶችን ተቋቁሞ የስርዓቱ መድህን ላይሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል መጠነ-ሰፊ ድርጅታዊና ሀገራዊ ቀውሶች ከመፈጠራቸው በፊት ለወታደሩ ፖለቲካዊ መደላድሉን ማጠናከር የተፈለገው፡፡

ከዚህ በኋላ ሲቪሉ መንግስት የጦር ሰራዊቱን አኮኖሚያዊ ኢምፓዬርና ፖለቲካዊ ሚና ለመገደብ ፍላጎትም አቅምም አይኖረውም፡፡ ሆኖም ግን ጦር ሰራዊቱ ራሱ ካሉበት ውስጣዊ ውስንነቶችና ከኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ጋር ካለው ጥብቅ ቁርኝት አንፃር ሲቪል መንግስቱን በሃይል ገልብጦ ስልጣን ሊይዝ ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል፡፡ ይልቁንስ ሀገራዊና ድርጅታዊ ቀውሶች ባንዣበቡ ቁጥር የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በመልካም ፍቃዱና በልማታዊ መንግስት ሽፋን ሰራዊቱን ወደ ፖለቲካ በመሳብና ጥምር የሲቪልና ወታደራዊ አገዛዝ (civilian-cum-military) በማስፈን ስልጣኑን ለማራዘም ሊሞክር ይችላል፡፡ ምዕራባዊያን አጋሮችም ቢሆኑ በዋናንት የሚፈልጉት የኢትዮጵያን መረጋጋት (stability) ስለሆነ ግብፅ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ ተቃውሞ ላይኖራቸው ይችላል፡፡

መቼም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትና የህወሃት ክፍፍል በፊት ለጦር ሰራዊት ግንባታ እምብዛም ትኩረት ያልሰጡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከህልፈታቸው በፊት ጦር ሰራዊቱ የኢኮኖሚ ኢምፓዬር እንዲገነባ መሰረቱን ሲጥሉለትም ሆነ ፖለቲካዊ ፍላጎቱ እንዲነቃቃ ሲያደርጉት ይህን ሁሉ ታሳቢ አድርገው ይሆናል፡፡

ቻላቸው ታደሰ ለዋዜማ ሬዲዮ