ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከተመሠረተ ሰባት ዓመት አልፎታል፡፡ የሳይንስ አካዳሚው የፕሬስ ክንፍ መጽሐፍት ማሳተም የጀመረው ግን በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነው፡፡ በዚህም ተግባሩ ጉለሌ የሚገኘው የሳይንስ አካዳሚ፣ የ6ኪሎው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ብቸኛ ሚና ሆኖ ለዓመታት የቆየውን ሥራ ተጋርቷል ማለት ይቻላል።
አካዳሚው የመጽሐፍ ኅትመቱን አሀዱ ያለው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥራ ነው፡፡ ይህ የብላቴን መጽሐፍ የተመረቀው የሳይንስ አካዳሚው በራሳቸው በብላቴን ጌታ ኅሩይ ስም የሰየመውን የሥነ ጥበባት ማዕከል መርቆ የሚከፍትበት ዕለት ነበር፡፡ ነገሩ አጋጣሚ ብቻ አይመስልም፡፡ ይልቅ መጽሐፉን ያሰናዱት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ረቂቁን ያገኙበት መንገድ ነው ግጥምጥሞሽ የሚመስለው፡፡
ፕሮፌሰሩ በ1994 ዓ.ም ሐምቡርግ በነበሩበት ወቅት ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሣ ከፍራንክፈርት አንድ ግሩም የሆነ ሰነድ ቅጂ ይልኩላቸዋል፡፡ ይህ ብዙ ስራ ይፈልግ የነበረው ሰነድ የአሁኑን መጽሐፍ ሐሳብ እንዲጸነስ ምክንያት ሆነ፡፡ የዚሁ ሰነድ ዋና ቅጂ ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የልጅ ልጅ ወይዘሮ እምዬ ተክለማርያም ዘንድ ተገኘ፡፡ የመጀመሪያውን ረቂቅ ለፕሮፌሰር ባሕሩ ያቀበሉት ዶክተር አስፋወሰን ዐሥራተ ካሳም በመጽሐፉ ታሪክ መሪ ተዋናይ ሆነው የምናገኛቸው የደጃዝማች ካሣ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ [ይህን ሙሉ መሰናዶ በድምፅ ተሰናድቶ ከግርጌ ያገኙታል]
የታሪክ ተመራማሪው ባሕሩ ዘውዴ በመጽሐፉ መግቢያ እንደሚነግሩን የቅጂ ቅጂውን ይዘው እንደነገሩ አቀናብረው በኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ መድረክ ላይ አቀረቡት፡፡ የተሟላ ነገር ስላላገኙ ነገሩን በዚያው ለመርሳት ነበር ሐሳባቸው፡፡ ኾኖም ሰነዱን እንዲህ በቀላሉ መርሳት አልቻሉም፡፡ “እንዲህ ያለ ሰነድ እጄ ገብቶ ታሪክ ለማወቅ ከፍ ያለ ጉጉት እያደረበት ለመጣው አንባቢ ሳላቀርብለት ብቀር ሕሊናዬ ይወቅሰኛል” አሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ዘለግ ያለ ጊዜ የወሰደ የምርምር ሥራ ዉስጥ በመግባት ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በአዲስ መልክ ማሰናዳትና መረጃ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡
ረቂቁ ሙሉ ባይሆንም አንባቢ “ከመጽሐፉ ጉድለቶች ይልቅ የሚያገኘው ጥቅም ሚዛን ይደፋል ብዬ ተስፋ አደረኩ” የሚሉት ፕሮፌሰሩ ተስፋቸው መስመሩን የምናየው ጥቂት ገጾችን ማገላበጥ እንደጀመርን ነው፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ “የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮጳና መካከለኛው ምሥራቅ” (1903 ዓ.ም) በሚል ርዕስ ለኅትመት ያበቁት ይህ ድርሳን ከዚህ ቀደም ለአንባቢያን ካበረከቷቸው የምርምር ሥራዎች በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነገሩ ላይ ላዩን ሲታይ ተራ የጉዞ ማስታወሻ ይመስላል፡፡ ሲነበብ ግን ታሪክ ነው፤ ብሔራዊ ክብር ነው፣ ፖለቲካ ነው፤ የርዕዮት ዓለምና የአስተሳሰብ ሽኩቻ ነው፤ ቁጭት ነው፤ የራስ ትዝብት ነው፤ የምጣኔ ሀብት ግርታ ነው፤ የኋላ ቀረን እንጉርጉሮ ነው፤ አገራዊና ግለሰባዊ ፍልስፍናም አለበት፡፡ የማንነት መጠይቅም ታጭቆበታል፡፡
ይህ በ302 የገጽ ብዛት የተቀነበበውን መጽሐፍ ለማሳተም እንደ መነሻ የሆነው ደግሞ በ20ኛው ምዕተ ዓመት መባቻ ላይ የዚያ ዘመን የኢትዮጵያ ሹማምንት ወደ አውሮጳና እና መካከለኛ ምሥራቅ አገራት ለጉብኝት ባቀኑበት ጊዜ በጉዞው ሒደት ላይ የተሰተዋሉትን ኹነቶች ግርምት በዝርዝር ዘግቦ የያዘው የኅሩይ ወልደ ሥላሴ ዜና መወዕል ነው፡፡ በዘመኑ ብርቱ ብዕረኛ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የጉዞውን አጠቃላይ ውጣ ውረድ በሚያስገርም ጥልቀት እና ስፋት በተባው ብዕራቸው ለቀሪው ትውልድ አኑረው አልፈዋል፡፡
ለአገር ጉብኝትም ሆነ በሌላ የሕይወት አጋጣሚ ባሕር ተሻግሮ በሚታየው እንግዳ ቁምነገር ተነሽጦ ነገሩን በጽሑፍ ለማስቀረት የመሞከር ልማድ በቀደሙትም ሆነ በአሁኑ የሀገራችን ልሒቃን ዘንድ እምብዛም የተለመደ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ስንፍና ሰፊው ሕዝባችን ስለ ሰፊው የተቀረው ዓለም ጠባብ ግንዛቤ እንዲኖረው ሳያደርገው አልቀረም፡፡ አልያም ደግሞ ቀሪውን ዓለም በአንዳች ዝንፈት እንዲመለከተው አድርጎታል፡፡ ይህ ዛሬም ድረስ የሚታይ ነው፡፡
ሌላው የዚህ መጽሐፍ ፋይዳ ምልከታው ከዉስጥ ወደ ዉጭ መሆኑ ነው፡፡ በሀገራችን ትልልቅ የትምህርት ተቋማት ቤተ መጽሐፍት መደርደሪያ ላይ የተሰለፉትን የጉዞ ማስታወሻዎችን ለመቃኘት ብንሞክር አብዛኞቹ ከሌላው ዓለም በመጡ አገር አሳሾች ልፋት እና ጥረት ለፍሬ እንደበቁ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ስለቀሪው ዓለም የምናውቀው እዚያው በኖሩ አውሮፓውያን ነጭ ዐይን እንጂ በኢትዮጵያዊ ጠይም መነጽር አልነበረም፡፡ ሁኔታው ሁለት ጽንፍ የያዙ ሕዝባዊ አመለካከቶችን ሳይፈጥር አልቀረም፡፡ አንድም ከውጭ የሚመጣውን ሁሉ በጥርጣሬ ማየትና ሲልም በእርኩስነት መፈረጅ፣ ወይም በሌላው ጽንፍ ኾኖ ውጩን የማምለክና ፍጹም አድርጎ የመመልከት አባዜን አውርሶናል፡፡
እንዲህ ዓይነት የኋላ ታሪክን መሠረት ያደረገ፣ ከውስጥ ወደ ዉጭ በሆነ እይታ በሀገር ሰው የተከተበን ዜና መዋዕል የድርሳን ግርማ አላብሶ ለኅትመት ማብቃት የሚኖረው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ከመጸሐፉ ጀርባ አድናቆታቸውን ካኖሩት የታሪክ ፕሮፌሰሩ አቶ ሺፈራው በቀለ እንረዳለን፡፡ ፕሮፌሰር ሺፈራው ከመቶ ዓመት በላይ ሳይታወቅ የቆየን ሰነድ ለኅትመት የመብቃቱን ጉዳይ ካመሰገኑ በኋላ እንዲህ ይላሉ፤
“ወቅቱ ዝመና የጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡…በዚያ ወቅት ኢትዮጵያዊያን አውሮፓን እንዴት እንዳዩት የምንረዳበት ትልቅ ሰነድ ነው፡፡…በዚያ ዘመን አውሮፓ መሄድ ማለት አንድ ያልታወቀ ዓለም መሄድ ማለት ነበር (a journey of Discovery) ፡፡ …የአውሮፓዊያንና የኢትዮጰያዊያንን የባህል ልዩነቶችና ግጭቶች እናይበታለን፤ ስለ ብሔራዊ ክብርና ስለ ሉአላዊነት የነበረውን አስተያየትም እናገኝበታለን፡፡
ድርሳኑ ገና ከበራፍ የሚቀበለን በልዑካኑ መሪ ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ጠጣር መልዕክት ነው፡፡
በምኒልክ እስከ ዘርአ ያ[ዕ]ቆብ፣ከፋሲል እስከ [ኢ]ያሱ፣ከሣህለ ሥላሴ እስከ ምኒልክ ያልነበረ ሥራት ማግባት እንደምን ይመቻል ትለኝ እንደሆነ እምናመልከው አምላክ ተለዋጭ አይደለምና ሃይማኖት በዬጊዜው መለወጥ አይገባም እንጅ አናኗርን ግን በዬጊዜው ማሻሻል ይገባል፡፡እነዚህ ሁሉ አቅኒዎች በሚቻላቸው ሥራ ሁሉ የጎደለውን እዬሞሉ ከአውሮፓና ከእስያ ሕግን እየተቀበሉ ሠሩ እንጅ አባቶቻችን አልሠሩትምና አንቀበልም አላሉም፡፡ምኒልክም ኢትዮጵያን የገዛበት በማክዳ ልጅነቱ ሲሆን እንደ አያቱ ሰው ልሰዋ እንደናቱ በአሕዛብ ሥራት ልገዛ አላለም፤ከዚህ በሚሻለው ለእስራኤል በተጻፈው ሥራት ገዛ እንጅ፡፡ዘርአ ያዕቆብም ከሱ በፊት ያልነበረውን የሮማውያን ሥራት ፍትሐ ነገሥትን ተቀብሎ ያገዛዝ ሥራት አድርጎ አጸና እንጅ ከምኒልክ እስካሁን የነበረውን እኔ አለውጥም አላለም፡፡
ይህ ሥነ ልቦናዊ ቅኝት ብዙ የሚነግረን መልዕክት አለው፡፡ ሀገርን ማዘመን አካባቢያዊ እውነታን በመናድ ግብር ፈጽሞ ሊገለጽ አይገባም፡፡ አንዱ በሌላኛው ኪሳራ መቀለስ እንደሌለበት ከደጃዝማቹ ምልከታ እንረዳለን፡፡
በደጃዝማች ካሳ ትንታኔ መሠረት ሥልጣኔ ማለት አውሮፓዊ እምነትን እና አመለካከትን እንደወረደ ማጥለቅ ሳይሆን አላስፈላጊውን ነቅሰው እየጣሉ በጎ በጎውን እየወሰዱ በየጊዜው የሚለወጡበት ተካታታይ ሂደት ነው፡፡ ሀገር በቀል ማንነትን ከሥሩ ነቅሎ በመጣል ፋንታ የጎደለውን እየሞሉ ወግ እና ሥርዓትን ጠብቆ ሚዛናዊ በሆነ ሐዲድ ላይ ዝንፍ ሳይሉ መንጎድ የዘመናዊነት መገለጫ እንደሆነ ከምልከታቸው መረዳት ይቻላል፡፡
የአድዋው ገድል የፈጠረው ግርማ ሞገስ የምዕራብዊያንን ትኩረት እንዴት እንዳስገኘ ዋቢ የሚሆነን በደጃዝማች ካሳ የሚመራው ልዑካን አባለት በኢንግሊዙ ንጉስ ጆርጅ 5ኛ ባዓለ ንግሥ ላይ እንዲታደሙ በክብር መጋበዛቸውን ስናይ ነው፡፡ አፍሪካዊያን በባርነት በሚዋትቱበት በዛን የጽልመት ዘመን የእኛ መሪዎች አውሮፓዊያን ነገስታት ጎን አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲቆሙ ያስቻላቸው ገና ትኩሳቱ ያልበረደው የያኔው የነፃነት ድል እንደነበረ እሙን ነው፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት ጉዞ ከሀገረ እንግሊዝ በተጨማሪ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንን እና ግብጽን ያካለለ ሲሆን በሁሉም የጉዞ ሒደት ላይ የተስተዋሉት ትዝብቶች በብላቴን ጌታ ዜና መዋእል ውስጥ ተካተዋል፡፡
ኅሩይ የሀገራቸውን ገመና በአውሮፓዊያኑ ሥልጣኔ መነጽር ባስተዋሉ ቁጥር ቁጭታቸውን በእየአጋጣሚ ከመግለጽ አይቆጠቡም፡፡ በአንድ አጋጣሚ ጣሊያን ሀገርን ሲጎበኙ በኢንዱስትሪው አማካኝነት የሚከናወነውን ድንቅ ሥራ ተመልክተው ቆም ብለው በመደመም ይህንን ቁምነገር አኑረው ነበር፡
ለሀገራችን ለኢትዮያ የልብስና የእርሻ መኪና በግድ ያስፈልጋል፡፡ ኑርአችን ሁሉ ሸማ ለብሰን ነው እንጅ እንደ አውሮፓች የበግ ጠጉርና ሐር ዘውትር አንለብስምና አገራችን ጥጥ ለማብቀል የተመቸ ነውና ስለዚህ የሸማ መኪና ያስፈልገናል፡፡ምግባችንም እህል ነው እንጅ እንደ አውሮፓች ሥጋና ዓሣ አትክልት ሁልግዚ አናገኝምና አገራችንም አሳምሮ እህል ያበቅላልና ስለዚህ የእርሻ መኪና ያስፈልገናል፡፡ይህንንም አስቀድሞ መንግሥት ገዝቶ ፋብሪካውን ቢያቆም መኳንንቱና ያገር ባለፀጎች ሁሉ እንደ ኩባንያ ገንዘብ እያዋጡ አንድ አንድ መኪና እየገዙ ፋብሪካ ያቆሙ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ያገኙበት ነበር፡፡
ኅሩይ እንደዚህ ያካፈሉን ቁጭት አፈር የለበሰውን የብዙ ኢትዮጵያውያንን የዘመናዊነት ህልምን የሚቀስቅስ ነው፡፡
የኅሩይ የዘመናዊነት አተያይ ሁለንተናዊ ነው፡፡ የዘመናዊነት መለኪያ አንዱ ከሆነው ሴኩራሊዝም ወይም በፖለቲካ እና በሃይማኖት መካከል የልዩነት ግምብ በሚያቆም መንግሥታዊ ሥርዓት ጋር ቅራኔ እንደሌላቸው በእየአጋጣሚው በሚያኖሩት ቁምነገር አጽንዖት ሰጥተው ያስገነዝባሉ፡፡ በኅሩይ መለኪያ ምድራዊውን ውጣውረድ ለመፍታት ዕጣፋንታ ወይም መለኮታዊ ኃይል የሚኖረው ሚና ምንም ነው፡፡ ላይ ታች በመባተል በጥረት ግረት በወረዛ ግምባር የሚገኝ ስኬት በፈጣሪ ፊት አያጎድልም፡፡ የፈጣሪ ቅያሜ የተሰጠንን መክሊት ለምድራዊ ዓላማ ማዋል ሲሳነን እንደሆነ ፍልስፍና ቀመስ በሆነ ምልክታቸው እንዲህ አደርገው ይነግሩናል፡፡
እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ብሎ ቤት ሳይሠሩ፣ አጥር ሳያጥሩ፣ እህል ሳይዘሩ መንደር ለመንደር ሲዞሩ ቢሞቱ እግዚአብሔርን መፈታተን ነው፡፡ ንጉሥም እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ብሎ ጋሻ ጦሩን፣ሰይፉን፣መድፉን ጠመንጃውን ሳያዘጋጅ ቢቀመጥ ድንገት ጠላት መጥቶ እርሱን ገድሎ መንግሥቱን ቢወስድበት እግዚአብሔርን መፈታተን ነው፡፡አመ እግዚአብሔር ኢዓቀበ አገር ከንቶ ይተግሁ እለ ይሔልው ማለት ጉልበታችሁን ተማምናችሁ እግዚአብሔርን አትርሱ፡፡
=============
የታሪክ ሊቃውንት አበክረው እንደሚያስገነዝቡት ከሆነ የኋላ ታሪክ የሚመረመረው በትናንት የታሪክ ኡደት ላይ የተደነቀሩ እንቅፋቶች ዳግም ቢከሰቱ የሚታለፉበትን መላ ለማግኘት ወይም የትናንትናውን ውድቀት ላለመድገም ነው፡፡ ያለፈውን ድክመት ይፋ ማድረግ ፋይዳው ለዛሬ ነው፡፡
በኅሩይ ወልደሥላሴን ዜና መዋዕል የትናነት ማንነታችን፣ ሥነ ልቦናችን እና ውጣ ውረዶቻንን አጽመ ታሪክ እናገኝበታለን፡፡ የድርሳኑ ፋይዳ ግን በዚህ እውነታ ላይ ብቻ የሚቀር አይደለም፡፡ አጽመ ታሪኩን መሠረት አድርጎ ለዛሬው ትውልድ የሚያተርፍ ቁምነገር ከውስጡ መዝዞ የማውጣቱ ሥራ የታሪክ ሊቃውንቱ ድርሻ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ፕሮፌሰር ባሕሩ በዚህ ረገድ አንድ ተጨማሪ ቁምነገር አበርክተዋል።