የኢትዮዽያ አየር መንገድ ለኢትዮዽያውያን ብሎም ለአፍሪቃ ኩራት ስለመሆኑ እምብዛም አያከራክርም። በብልሹ አሰራሩ በሚታወቀው የኢህ አዴግ መራሹ መንግስት መተዳደሩም ቢሆን አየር መንገዱን ከዕድገት ግስጋሴ አላቆመውም። በየአመቱ የተሳፋሪዎች ቁጥር ሀያ በመቶ እየጨመረ ትርፉም እየዳጎሰ ነው። እየበረታ የመጣው የሰራተኞችና የድርጅቱ ውዝግብ ግን የኋላ ኋላ አየር መንገዱን ወደ ውድቀት ያመራዋል የሚሉም አሉ። የድርጅቱ አመራሮች ግን ትርክታቸው ለየቅል ነው። ተከታዩ የቻላቸው ታደሰ ዘገባ ጉዳዩን አብራርቶ ይነግራችኋል አድምጡት
በሚቀጥለው ዓመት ሰባኛ የልደት በዓሉን የሚያከብረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ ዓለምን በማዳረስ ረገድ ምንጊዜም ግንባር ቀደሙ አምባሳደር ነው፡፡ በሀገሪቱ ገቢና ወጭ ንግድ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ገና አፍሪካዊያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ሲማቅቁ የተቋቋመው አየር መንገዱ በሶስቱም መንግስታት የኢትዮጵያዊያንና ሌሎች አፍሪካዊያን ማንነት መገለጫ ሆኖ ኑረዋል፡፡ የፓን-አፍሪካኒዝም ተልዕኮ ግንባር ቀደም አስፈፃሚ ስለመሆኑም አያከራክርም፡፡
የዓለም ዓቀፉ ስታር አሊያንስ አባል የሆነው አየር መንገዱ በአገልግሎት ብቃቱና ጥራቱ ብሎም በበረራ ደህንነት ታሪኩ ዝነኛ ስም አለው፡፡ ሙሉ በሙሉ በመንግስት የልማት ድርጅትነት የተያዘው አየር መንገድ ባሁኑ ወቅት እጅግ አስገራሚ በሆነ የዕድገት ጎዳና ላይ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታትም በየዓመቱ ከ20 በመቶ በላይ እያደገ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዕድገቱ በአፍሪካ ግንባር ቀደሙ አየር መንገድ ለመሆን ችሏል፡፡
እጅግ ፈታኝ በሆነው የአቬይሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ዕድገቱ የሚደገፍ ቢሆንም ፍጥነቱ ግን አደጋ ይጋብዛል ብለው የሚሰጉ ወገኖች ቀላል አይደሉም፡፡ በውስጥ አስተዳደሩም ቅሬታዎች ሲንፀባረቁ ኑረዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ታሪካዊ ወቅት የአየር መንገዱ ዕድገት ጉዞ፣ የገጠሙትን ፈተናዎችና የሚቀርቡበትን ትችቶች መፈተሽ ተገቢ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ራዕይ- 2025” የተሰኘውን የ15 ዓመት የዕድገት መርሃ ግብሩን ከአምስት ዓመት በፊት ቀርፆ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በፈጣን ዕድገት ውስጥ ይገኛል፡፡ የአየር መንገዱ የ“ራዕይ- 2025” ዕቅድ አራት ዋና ዋና ምሰሶዎችን ማለትም ጥራትና ብዛት ያላቸው አውሮፕላኖች ግዥ፣ የመሰረተ-ልማት ማስፋፊያ፣ የሰው ሃይል ልማት እና የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማስፋፊያዎችን ያካትታል፡፡
ዕቅዱን መተግበር ከጀመረ ጀምሮም በቅርቡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3.5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱንም ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ በታሪኩ ከፍተኛው ትርፍ መሆኑ ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመትም 3.1 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
የአየር መንገዱ ዕድገት ግን በትርፍ መጠን ብቻ ሳይሆን በመዳረሻዎች፣ በመንገደኞችና በአውሮፕላን ብዛትና ጥራትም ከፍተኛ እመርታ ማሳየቱ ዕድገቱ ሁለገብ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከአፍሪካ አህጉር የድሪም ላይነር አውሮፕላን ባለቤት በመሆንም ቀዳሚ ሁኗል፡፡ መቼም ድሪም ላይነሮቹም በአቬይሽን የልዕልና ማማ ላይ እንዳስቀመጡት እሙን ነው፡፡ በዕቅዱ 63 አውሮፕላኖች እንዲኖሩት አቅዶ በአሁኑ ወቅት ግን የ77 አውሮፕላኖች ባለቤት ለመሆን እንደቻለ ይናገራል፡፡ እኤአ በ2025ም የ120 አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን በዓለም ዙሪያ 18 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን ለማጓጓዝ አቅዷል፡፡ አየር መንገዱ በአፍሪካ በዓመት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተሳፋሪዎች ካሏቸው አራት አየር መንገዶችም አንዱ ነው፡፡ የደንበኞቹ ብዛትም በየዓመቱ የ20 በመቶ እያደገ መሆኑን ይናገራል፡፡ አሃዙ ከመዳረሻዎችና አውሮፕላኖች መብዛት አንፃር መታየት ያለበት ቢሆንም፡፡ በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና እስያ አህጉሮች መዳረሻዎቹን በፍጥነት እያስፋፋ ያለው አየር መንገዱ በአሁኑ ጊዜ የ91 መዳረሻዎች ባለቤት በመሆኑ ዕቅዱ 10 ዓመት ቀድሞ ተሳክቶለታል፡፡
እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር ሙሉ በሙሉ በመንግስት ባለቤትነት የተያዘው አየር መንገዱ የባለቤትነት ድርሻዎችን ለውጭ ኩባንያዎች በመሸጥ ፋንታ ከማላዊ አየር መንገድ 49 በመቶ፤ ከቶጎው ስካይ ኤይር ላይንስ ደግሞ የ40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ መግዛቱ ነው፡፡ በማዕከላዊ አፍሪካም ተመሳሳዩን ለማድረግ እያሰበ መሆኑን ይናገራል፡፡ በአንድ በኩል አፍሪካ አህጉርን በኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም ለማስተሳሰር እየተጋ መሆኑን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እየከሰሩ ያሉ አፍሪካዊያን አየር መንገዶችና የአፍሪካን ገበያ እየለቀቁ ያሉት የአውሮፓ አየር መንገዶች የሚፈጥሩትን ክፍተት የገልፍ አየር መንገዶች ሳይቆጣጠሩት ተሽቀዳድሞ ለመሽፈን ያለውን ፍላጎትም ያረጋግጣል፡፡ በዚህም አፍሪካዊያንን እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን ከቀሪው ዓለም ጋርም ሊያገናኛቸውና እውነተኛ የፓን-አፍሪካን አየር መንገድ መሆኑን በተግባር ለማሳየት ደፋ ቀና እያለ ስለመሆኑ ማስረጃ ይሆናል፡፡
አየር መንገዱ በአፍሪካ ዝነኛ የሆነውን ዘመናዊ የአቬሽን አካዳሚም ባለቤት ሲሆን በአሁኑ ጊዜም አራት ሲህ ሰልጣኞችን በአንድ ጊዜ ማሰልጠን እንዲችል በ55 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በከፍተኛ ደረጃ እያስፋፋው መሆኑን ይገልፃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ አንድ ሺህ ሶስት መቶ አብራሪዎች፣ የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሻያኖች፣ የበረራ አስተናጋጆችና የማርኬቲንግ ባለሙያዎች እየሰለጠኑበት ነው፡፡ አካዳሚውም የገቢ ምንጬን ያሰፋልኛል ብሎ ተስፋ ጥሏል፡፡
የአየር መንገዱን ስኬታማነት ልዩ የሚያደርጉት ሦስት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው በተከታታይ ፈጣን ዕድገት ላይ እያለም እንኳ በተከታታይ አትራፊ መሆኑ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በፈጣን ዕድገት ውስጥ ያለ ተቋም ግዙፍ ኢንቨስትመንት ስለሚያፈስ ትርፋማ መሆን ይከብደዋል፡፡ ታሳቢ የሚያደርገው ከፈጣን ዕድገቱ በኃላ የሚመጣውን ትርፍ ነውና፡፡ ለአብነትም የኳታርን አየር መንገድ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሁለተኛው በያዝነው በጀት ዓመት የአየር መንገዱ ተፎካካሪዎች የሆኑት የደቡብ አፍሪካ፣ የኬንያና የግብፅ አየር መንገዶች ከፍተኛ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው እየገለፁ ያሉበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም ኬንያ ኤርዌይስ በዚህ ዓመት ብቻ 293 ሚሊዮን ዶላር መክሰሩን ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ኤርዌይስ 223 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የግብፅ አየር መንገድ ደግሞ 350 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደገጠማቸው ሲያስታውቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በትርፍ ተንበሽብሻለሁ ይላል፡፡
ሦስተኛው አየር መንገዱን ልዩ የሚያደርገው ነገር በኢህአዴግ መራሹ-መንግስት ሙሉ ይዞታ ስር የሚገኝ የልማት ድርጅት ሆኖ ሳለ ተከታታይ ዕድገት ማስመዝገቡና ዓለም ዓቀፍ ዝናውን ማስቀጠሉ ነው፡፡ ይህንን ለማለት የሚያስደፍረው መንግስት ተጠያቂነትና ግልፅነት በጎደለው መንገድ በይዞታው ስር ያሉ የልማት ድርጅቶችን ሲመራቸው ስለምናይ ነው፡፡ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናቱን ለአየር መንገዱ ቦርድ ሰብሳቢነት ከመሾሙ አንፃር አየር መንገዱ እስካሁን ለችግር አለመጋለጡ የአመራሮቹን ጥኝካሬ ያሳያል፡፡
መቼም ጊዜው የዓለም ዓቀፍ ሽብርና የአውሮፕላን በረራ ደህንነት አሳሳቢ የሆኑበት ቢሆንም አየር መንገዱ በደህንነት ጥበቃ መልካም ዝናውን አላጎደፈም፡፡ ወደ ሰሜን አሜሪካ የሚበረውም ጥብቁን የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን ምርመራ፣ ቁጥጥርና መመዘኛ ስላሟላ እንደሆነም እሙን ነው፡፡
ሆኖም ግን የአየር መንገዱ የዕድገት ጉዞ አልጋ ባለጋ አይደለም፡፡ መፃዒ ዕጣ ፋንታውም ከባድ ፈተና የተጋረጠበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
አምና በምዕራብ አፍሪካ በተከሰተው የኢቦላ ወረርስኝ ሳቢያ ወደ አፍሪካ የሚደረጉ ዓለም ዓቀፍ በረራዎች በመቀነሳቸው አየር መንገዱ በየወሩ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያጣ እንደነበር በወቅቱ ሪፖርተር ጋዜጣ የአየር መንገዱን ማኔጅመንት ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ መልካሙ ዜና ግን ከተፎካካሪ አየር መንገዶች በተቃራኒው ትርፋማነቱ እምብዛም ሳይጎዳ መቅረቱ ነው፡፡ በእርግጥ በርካታ አየር መንገዶች ወደ ምዕራብ አፍሪካ የሚያደርጉትን በረራ ባቆሙበት ሰዓት እንኳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተደጋጋሚ ሲበር ተስተውሏል፡፡ ኢቦላ ለሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ኪሳራ አንዱ ዋነኛ ምክንያት እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባለፀጋዎቹ የገልፍና ቱርክ አየር መንገዶች ዋና ትኩረታቸውን ወደ አፍሪካ ማዞራቸው ሌላኛው ፈተና ሆኖበታል፡፡ የአየር መንገዱን አመራሮች በእየዕለቱ ከእንቅላፋቸው የሚያባንናቸውም ወደ አዲስ አበባ በብዛት በሚበሩት የገልፍ አየር መንገዶች ህልውናችን አደጋ ውስጥ ይገባል የሚል ስጋት እንደሆነ ግልፅ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ባለሙያዎቹንም የሚያማልሉበት እኝሁ አየር መንገዶች ናቸው፡፡
ሌላኛው ፈተና ደግሞ በርካታ አፍሪካዊያን ሀገሮች አኤአ በ1988 ዓ.ም ከተደረሰው አህጉራዊ መግባባት (Yamoussoukro Declaration) በተቃራኒ በመንግስት የሚደጎሙት አየር መንገዶቻቸው ከገበያ እንዳይወጡባቸው በመስጋት ለአፍሪካዊያን አየር መንገዶች በራቸውን ጥርቅም አድርገው መዝጋታቸው ነው፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ የአህጉሪቱን ሰማንያ በመቶ መንገደኛ የሚያጓጉዙት ከአፍሪካ ውጭ ያሉ አየር መንገዶች መሆናቸውን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓን-አፍሪካኒዝም ራዕይ ላይ በረዶ ይቸልሳል፡፡ ስለሆነም የአየር መንገዱ አመራሮች አፍሪካዊያን በሮቻቸውን እንዲከፍቱ ሲማጠኑ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በብዙ ዘርፎች በውጭ ኩባንያዎች ላይ በሩን በከረቸመበት ወቅት አየር መንገዱ እንዲህ ዓይነት ጥሪ ማቅረቡ ለነፃ ገበያ ፉክክር ዝግጁነቱን ያሳያል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአየር መንገዱ በረራ ደህንነት ታሪክ አኩሪ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ ባለፈው ዓመት በለንደን ሂትሮው አየር ማረፊያ ውስጥ በአንድ ድሪም ላይነር አውሮፕላኑ ላይ መጠነኛ የእሳት ቃጠሎ ቢታይም በኃላ ላይ ግን መንስዔው ከኤሌክትሪክ ሲስተም ጋር የተያያዘ እንጂ የደህንነት ችግር እንዳልሆነ ተረጋግጧል፡፡
ከዓመታት በፊት የተከሰተው የኮሞሮሱ አስከፊ አደጋም ቢሆን የሽብር ጥቃት እንደሆነ ከታመነበት ቆይተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሊባኖስ ሰማይ ላይ የፈነዳው አውሮፕላን ጉዳይም ተድበስብሶ ቢቀርም የአደጋው ምክንያት ግን ከአየር መንገዱ በረራ ደህንነት ጋር የሚያያዝ እንዳለሆነ በሰፊው ይታመናል፡፡ ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ሰማይ ላይ አንድ ረዳት አብራሪ አውሮፕላኑን መጠለፉ ግን የአየር መንገዱ ውስጣዊ አስተዳደራዊ ችግሮችን ያመለክታል የሚሉ ታዛቢዎች ቀላል አይደሉም፡፡ የስዊዘርላንድ መንግስት በአብራሪው ላይ ያደረገውን ምርመራ ገና ይፋ ባያደርግም፡፡
አየር መንገዱ ከመልካም ስምና ፈጣን ዕድገቱ ጀርባ ትችቶችንም ያስተናግዳል፡፡ ብዙ ጊዜ በሀገር ውስጥ በረራዎቹ ላይ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ ለአብነትም በአንድ ወቅት በቅንጅት ጉድለት ምክንያት ለውጭ ዜጎች ቅድሚያ ለመስጠት ሲባል የሀገሬው ተሳፋሪዎች አማካይ መንገድ ላይ ተገደው እንዲወርዱ የተደረገበትን አጋጣሚ የዚህ ጥንቅር አዘጋጅ ሳይቀር በዓይኑ አይቷል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ቢሆኑ አየር መንገዱ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንደሚያያቸው ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ “አየር መንገዱ ኢትዮጵያዊነት መንፈሱ ተሸርሽሮ የውጭ ዜጎች አምላኪ እየሆነ ይሆን?” ብለው የሚጠይቁ ታዛቢዎች ቀላል አይደሉም፡፡ በርካታ ዲያስፖራ ላላት ሀገራችን ይህ ቅሬታ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
የካበተ ልምድ ያላቸው በርካታ አብራሪዎቹና ቴክኒሻኖችም በክፍያ ማነስና በሌሎች አስተዳደራዊ ምክንያቶች ሳቢያ ስራቸውን እንደሚለቁ ይነገራል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታትም የሰው ሃይል እጥረቱ ከዕድገቱ ጋር ባለመመጣጠኑ የውጭ ሀገር አብራሪዎችንና የበረራ አስተናጋጆችን መቅጠሩን ከባለሙያዎች ስራ መልቅቅ ጋር የሚያያይዙት በርካቶች ናቸው፡፡ ማኔጅመንቱ ግን በዘመነ-ግሎባላይዜሽን የተለመደ ትዕይንት መሆኑንና ስራ የሚለቁትም በጣም ትንሽ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ በእርግጥ ምን ያህል ባለሙያዎች በክፍያና አስተዳደራዊ በደል ሳቢያ ስራ እንደሚለቁ አስተማማኝ ማስረጃ ማግኘት ያስቸግራል፡፡
የአየር መንገዱን ፈጣን ዕድገትም ጤናማ ያልሆነና በሰራተኞቹ ላይ ከመጠን ያለፈ ጫና የሚያሳድርና አየር መንገዱን ከማይወጣው ቀውስ ውስጥ የሚከት ነው በማለት የሚተቹት ጥቂት አይደሉም፡፡ አየር መንገዱ ትርፍ ላይ ብቻ ማተኮሩ በብሄራዊና አህጉራዊ አርማነቱ ላይ በረዶ እንዳይቸልስበት ስጋት ያላቸው ታዛቢዎች ትርፍን ከብሄራዊና አህጉራዊ አርማነቱ ጋር እንዲያጣጥም ያሳስባሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በማኔጅመንቱ ውስጥ መከፋፈልና አለመስማማት መኖሩ ቢዘገብም ስራ አስኪያጁ ግን በተደጋጋሚ ጉዳዩን ያስተባብላሉ፡፡
አየር መንገዱ የሀገሪቱ ምስቅልቅል ፖለቲካ ሰለባ መሆኑም አልቀረም፡፡ ከአወዛጋቢው የ1997ቱ ምርጫ ማግስት ጀምሮ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች መንግስት ከአየር መንገዱ በሚያገኘው ግዙፍ ገቢ በሀገር ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ለመጨፍለቅና የጭቆና መረቡን ለመዘርጋት እየተጠቀመበት መሆኑን በመጥቀስ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን በአየር መንገዱ ከመብረር እንዲታቀቡ ጥሪ ሲያደርጉ ይደመጣሉ፡፡ ሆኖም የብሄራዊና አህጉራዊ ኩራት በሆነው አየር መንገድ ላይ እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ ብዙዎችን ውልውል ውስጥ እንዳስገባቸው መገመት አይከብድም፡፡
በጠቅላላው አየር መንገዱ በብዙ መልኩ መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለ ይመስላል፡፡ ታሪካዊ ዝናውንና ዕድገቱን ጠብቆ ለመቀጠልም በጥንቃቄ መጓዝ ይኖርበታል፡፡ አሁን ሀገሪቱ አለኝ የምትለው ብቸኛ አስተማማኝ ተቋሟ እሱ ብቻ ነውና፡፡